የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ከሜዳ እስከ ፖለቲካ

0
148

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ)በ2026 የሚያዘጋጀው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ብዙዎች እየተናገሩ ነው:: ይህ ውድድር ከዚህ ቀደም ከለመድናቸው የዓለም ዋንጫዎች በብዙ መልኩ የተለየ እና የላቀ ሆኖ እንዲቀርብ ታስቦ እየተዘጋጀ ይገኛል:: ውድድሩን ሦስት ሀገራት ማለትም አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ የሚያስተናግዱት ይሆናል::

ዝግጅቱ በሰሜን አሜሪካ ምድር የእግር ኳስን ትኩሳት ወደ አዲስ ከፍታ ያሸጋግረዋል ተብሎም ይጠበቃል:: ውድድሩ ሰኔ አራት 2018 ዓ.ም የሚጀመር ሲሆን የመክፈቻው ጨዋታ በሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው ኢስታዲዮ አዝቴካ ይደረጋል:: በአጠቃላይ 104 ጨዋታዎች በ16 ከተሞች የሚካሄዱ ይሆናል:: በአሜሪካ በ11 ከተሞች ሲደረግ በሜክሲኮ በሦስት እና በካናዳ በሁለት ከተሞች ጨዋታዎች እንደሚደረጉ የፊፋ ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል::

ጨዋታውን ይበልጥ ፈጣን፣ ፍትሐዊ እና ማራኪ ለማድረግ በማሰብ የፊፋ ባለሥልጣናት በርካታ አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል:: ከውድድሩ አወቃቀር ለውጥ ባሻገር፣ ሆን ተብሎ የሚደረግ የጊዜ ማጥፋትን ለመከላከል እጅግ ጥብቅ የሆኑ የሜዳ ላይ ህጎች ጸድቀዋል:: ከእነዚህም መካከል ግብ ጠባቂዎች የግብ ምት ሲመቱ እንዲሁም ተጫዋቾች ኳስ ከውጭ ወደ ሜዳ ሲወረውሩ በአምስት ሴኮንዶች ውስጥ ማስጀመር ይኖርባቸዋል:: ይህን በተሰጠው ጊዜ ውስጥ አለማድረግ የኳስ ቁጥጥርን ለተጋጣሚ ቡድን አሳልፎ የሚሰጥ ሲሆን፣ የግብ ምት ከዘገየ ደግሞ ለተጋጣሚ የማዕዘን ምት (ኮርነር) እንዲሰጥ ያስገድዳል::

በተጨማሪም ተቀይሮ የሚወጣ ማንኛውም ተጫዋች በዐስር ሴኮንዶች ውስጥ ሜዳውን ለቆ መውጣት አለበት:: ይህን ሳያደርግ ቢዘገይ ግን ተቀይሮ የሚገባው ተጫዋች ወዲያውኑ መግባት ስለማይፈቀድለት ቡድኑ ለአንድ ደቂቃ ያህል አንድ ተጫዋች ጎድሎበት እንዲጫወት ይገደዳል:: በጨዋታ ላይ ጉዳት ገጥሟቸው የህክምና እርዳታ ያገኙ ተጫዋቾችም ወደ ሜዳ ከመመለሳቸው በፊት ቢያንስ ለአንድ ደቂቃ ከሜዳ ውጭ መቆየት አለባቸው::

የዳኝነት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተም ትልቅ ለውጥ ተደርጓል:: በጨዋታ ወቅት ተጫዋቾች ዳኛውን ከበው ማውራትም ሆነ ማብራሪያ መጠየቅ አይችሉም፤ ይህ መብት የተሰጠው ለቡድኑ አምበል ብቻ ሲሆን አምበል ያልሆነ ተጫዋች ዳኛውን ለማነጋገር ቢሞክር በቀጥታ ቢጫ ካርድ (ማስጠንቀቂያ) ይሰጠዋል:: የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (VAR) አጠቃቀምም ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ መልኩ ሁለተኛ የቢጫ ካርድ ውሳኔዎችን እንዲሁም በስህተት የተሰጡ የማዕዘን ምቶችን መለስ ብሎ ማየት እና ማረም እንዲችል ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቶታል:: በአጠቃላይ እነዚህ የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ አዳዲስ ሕጎች የእግር ኳስን ፍጥነት ከመጨመር ባለፈ ተመልካቹ ያለመቆራረጥ የተሻለ መዝናኛ እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል::

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ኒው ጀርሲ በሚገኘው ሜትላይፍ ስታዲየም ይከናወናል:: ፊፋ ለሁሉም ተሳታፊ ሀገራት የገንዘብ ሽልማት የሚያበረክት ሲሆን ውድድሩን በማሸነፍ ለሚያጠናቅቀው ብሄራዊ ቡድን 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ ይበረከትለታል:: ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለሚጨርስ 33 ሚሊዮን ዶላር፣ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቅ 27 ሚሊዮን ዶላር፣ አራተኛ ደረጃን የሚይዝ 19 ሚሊዮን ዶላር ይሸልማል:: ከ33ኛ እስከ 48ኛ ደረጃን ይዘው የሚጨርሱ ብሄራዊ ቡድኖች እኩል የዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚበረከትላቸው የስካይ ስፖርት መረጃ አስነብቧል::

ሀያ ሦስተኛውን የዓለም ዋንጫ ልዩ የሚያደርገው የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር መጨመሩ ነው:: ከ1998 እ.አ.አ የፈረንሳይ ዓለም ዋንጫ ጀምሮ እስከ  ኳታሩ ውድድር ድረስ 32 አገራት ሲሳተፉ እንደነበር አይዘነጋም:: በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ግን ይህ ቁጥር ወደ 48 ከፍ እንዲል ተወስኗል:: ይህ ውሳኔ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ላይ የመሳተፍ  ዕድል እንዲያገኙ ረድቷቸዋል:: በተለይም እንደ አፍሪካ እና እስያ ያሉ አህጉራት የተሻለ ውክልና እንዲያገኙ ያስችላቸዋል::

አፍሪካ ቀድሞ ከነበራት አምስት ውክልና  አሁን ወደ ዘጠኝ  ከፍ ማለቱ  በእግር ኳሱ ደካማ ለሆኑ ሀገራት ትልቅ ተስፋን ይሰጣል:: አልጄሪያ፣ኬፕ ቨርዴ፣ ኮት ዲቩዋር፣ ግብፅ፣ጋና፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቱኒዚያ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ሀገራት ናቸው:: ሞሮኮ በኳታር የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ በመድረስ ያሳየችው አስደናቂ ብቃት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ትልቅ ህልም እንዲያልሙ አድርጓቸዋል::

በኢራን፣ በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል ያለው የወቅቱ የዓለም ፖለቲካዊ ውጥረት በውድድሩ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ከወዲሁ ተገምቷል:: በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ጦርነት አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ ባላት ቀጥተኛ ተሳትፎ በውድድሩ ላይ የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተሰግቷል:: ፊፋ እና የአሜሪካ መንግሥት ግን በስታዲየሞች እና በደጋፊዎች አካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ የደህንነት ችግሮችን ለመከላከል ከወዲሁ ከፍተኛ በጀት መድበው እየሠሩ  እንደሚገኙ የፊፋ ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል::

የኢራን ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ላይ የሚኖረው ተሳትፎና የአሜሪካ ቪዛ አሰጣጥ ሂደት በፖለቲካዊ ውጥረት ምክንያት ሊስተጓጎል እንደሚችል ስጋቶች አሉ:: በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ሰፊ ጦርነት የአየር ጉዞን እያስተጓጎለ ይገኛል:: ይህም ለደጋፊዎች እና ለቡድኖች ጉዞ ትልቅ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ተብሏል:: አሜሪካ ይህንን ስጋት ለመቀነስ ከአሁኑ የፀጥታ መዋቅሯን በማጠናከር ላይ እንደምትገኝ ዘ ኒወርክ ታይምስ ዘግቧል::

የፖለቲካዊ አለመረጋጋቱ በተጫዋቾች ስነ ልቦና ላይም ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል:: በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ የሚስተዋሉ ግጭቶች ሀገራት ርስ በርስ እንዳይገናኙ ወይም ውጥረት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ:: ሆኖም ፊፋ ስፖርት ለሰላም በሚለው መርሁ ፖለቲካዊ ልዩነቶች በሜዳ ላይ እንዳይንፀባርቁ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል::

ከሁለት ወራት በኋላ በሚጀመረው ግዙፉ የእግር ኳስ ድግስ የውድድሩ ቅርጽም ተቀይሯል:: ፊፋ 48ቱን ሀገራት በ12 ምድቦች በመከፋፈል በእያንዳንዱ ምድብ አራት ሀገራት እንዲመደቡ አድርጓል:: ይህም ማለት እያንዳንዱ ሀገር ቢያንስ ሦስት የምድብ ጨዋታዎችን ያደርጋል:: ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ ሀገራት እንዲሁም ስምንት ምርጥ ሦስተኛ አሸናፊዎች ወደ ቀጣዩ  ዙር እንደሚያልፉም የፊፋ መረጃ ያሳያል:: በአጠቃላይ  በ39 ቀናት ውስጥ  104 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል:: ይህ ረጅም የውድድር ጊዜ ለተጫዋቾች አካላዊ ብቃት ፈታኝ ሊሆን ይችላል ነው የተባለው:: ለአዘጋጅ ሀገራቱ ግን ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝላቸዋል::

የፊፋ ዋና መሥሪያ ቤት በከፊል ወደ ማያሚ መዛወሩ ውሳኔዎችን በፍጥነት ለማሳለፍና ዝግጅቱን በቅርበት ለመከታተል ያስችላል:: በ11 የአሜሪካ ከተሞች የሚገኙ ስታዲየሞች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጥቶባቸው በዘመናዊ መንገድ እየታደሱ ነው:: አስተናጋጅ ሀገራቱ በከተሞቻቸው መካከል ያለውን ሰፊ ርቀት እና የሰዓት ልዩነት ለመቋቋም ከፍተኛ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ:: የደጋፊዎችን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍም በምድብ ጨዋታዎች ወቅት ሀገራት በቅርብ ርቀት ባሉ ከተሞች እንዲጫወቱ የማድረግ እቅድ ተይዟል:: ይህ በጉዞ ምክንያት የሚመጣን ድካም ከመቀነሱም በላይ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ይላል፤ የስካይ ስፖርት መርጃ ::

ሜክሲኮ ለሦስተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን በማስተናገድ የመጀመሪያዋ ሀገር ናት:: ካናዳም ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን በጋራ የማዘጋጀት ዕድል በማግኘቷ ስፖርቱን በሀገሯ ለማስፋፋት ትልቅ እድል ይሰጣታል :: የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ዓለማችን እስካሁን ካየቻቸው የስፖርት ትዕይንቶች ሁሉ በግዝፈቱም ሆነ በድምቀቱ ቀዳሚ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ::

ሦስቱ የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ያላቸውን የንግድ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዚህ ውድድር አማካኝነት ይበልጥ ለማጠናከር አልመዋል:: በተለይም ስደት እና የድንበር ጉዳዮች አነጋጋሪ በሆኑበት በዚህ ወቅት እግር ኳስን እንደ ድልድይ በመጠቀም ሕዝቦችን ማቀራረብ ትልቅ ግብ ተደርጎ ተወስዷል:: የካናዳ እግር ኳስ በቅርብ ዓመታት እያሳየ የመጣው እድገት እና በአሜሪካ የእግር ኳስ ሊግ መስፋፋት ውድድሩ በሰሜን አሜሪካ የሚኖረውን ተቀባይነት ይበልጥ ያሳድገዋል:: ሜክሲኮ ደግሞ ያላትን ጥልቅ የእግር ኳስ ባህል እና ልምድ ለውድድሩ ድምቀት ትጠቀምበታለች ተብሎ ይገመታል::

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለተመልካቾች አዳዲስ ልምዶችን፣ ለተጫዋቾች ሰፊ መድረክን፣ ለአዘጋጆቹ ደግሞ ታሪካዊ አሻራን ጥሎ እንደሚያልፍ ይታመናል:: እያንዳንዱ የእግር ኳስ አፍቃሪም ይህንን ግዙፍ ትርኢት ለመታደም ቀኖችን መቁጠር ጀምሯል:: በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያለው ውጥረት ቢቀጥልም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስፖርቱ የሰላም መልእክተኛ ሆኖ እንዲሚያገለግል ተስፋ አድርጓል:: ፊፋም ማንኛውንም የደህንነት ስጋት ለመመከት ከዓለም አቀፍ የደህንነት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጿል:: የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካ  እና በኢኮኖሚ ያለውን ትስስር የሚያሳይ ታላቅ መድረክ ሆኖ በታሪክ ገጾች ላይ ይሰፍራል ተብሎ ይጠበቃል::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here