አፓርታይድ

0
144

አፓርታይድ (Apartheid) የሚለው የአፍሪካንስ ቃል “መለየት” ወይም “የዘር መለያየት” ማለት ሲሆን፣ በደቡብ አፍሪካ ከ1948 እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ በነጮች በቁጥር አናሳ መንግሥት የጸና፣ የዘር መድሎን በህግ ያስቀመጠ የጭቆና ስርዓት እንደነበር ቢቢሲ በታሪክ ገጹ አስፍሯል። ይህ ስርዓት የአፍሪካውያንን፣ ከነጭ እና ከጥቁር የተወለዱ (Coloureds) እና የህንድ ተወላጆችን ሰብአዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች በማፈን፣ በነጮች የበላይነት ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለመ ነበር።

የአፓርታይድ ስርዓት መሰረቱ የአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ ቢሆንም በ1948 የብሔራዊ ፓርቲ (National Party) ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት የዘር መለያየቱ በይፋ ተጠናክሮ ህግ ሆነ። በዚህ ስርዓት መሰረት ህዝቡ እንደ ዘሩ ተለይቶ በየደረጃው በሚኖሩ አካባቢዎች እንዲኖር ተገዷል፣ ይህም “የባንቱስታን” ወይም “ሆምላንድ” በመባል የሚታወቁ ለጥቁሮች ብቻ የተመደቡ ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎችን ፈጠረ። ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በትውልድ ሀገራቸው ለመዘዋወር “ፓስፖርት” ወይም “Pass laws” የሚባሉ የመታወቂያ ሰነዶችን መያዝ ግዴታ ነበረባቸው።

በአፓርታይድ ዘመን የነበሩ የህግ ገደቦች ጥብቅ ነበሩ። ነጮች እና ጥቁሮች በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ፣ በባህር ዳርቻዎች አልፎ ተርፎም በመጸዳጃ ቤቶች አንድ ላይ መጠቀም አይችሉም ነበር። በአንድ አፓርታይድ የተከለከሉ ጥቁሮች ከነጮች ጋር እንዳይጋቡ ወይም የፍቅር ግንኙነት እንዳያደርጉም ተከልክለው ነበር። ይህም በህዝቡ መካከል ጥልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልዩነትን ፈጠረ።

የአፓርታይድ ስርዓት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። በ1960 የተፈጸመው የሻርፕቪል እልቂት እና በ1976 የተነሳው የሶዌቶ የተማሪዎች አመጽ ስርዓቱን ለማናጋት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። እነዚህ አመጾች በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) እና እንደ ኔልሰን ማንዴላ ባሉ መሪዎች የተመሩ ነበሩ። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በተለይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፓርታይድን በማውገዝ ማዕቀብ በመጣል ስርዓቱ እንዲዳከም አድርገዋል።

ከበርካታ ዓመታት ትግል እና ዓለም አቀፍ ጫና በኋላ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ስርዓቱ መፈራረስ ጀመረ። እ.አ.አ በ1994 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያው ሁሉን አቀፍ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ኔልሰን ማንዴላ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት በመሆን የአፓርታይድ ስርዓትን በይፋ አፈረሱ። ምንም እንኳን አፓርታይድ ህጋዊ ማብቂያ ቢያገኝም ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠባሳ በደቡብ አፍሪካ ዛሬም ድረስ ይታያል።

ታሪካዊው የሻርፕቪል እልቂት (Sharpeville Massacre) በአፓርታይድ ታሪክ ውስጥ እጅግ ወሳኝና የትግሉን አቅጣጫ የቀየረ ክስተት ነው። ይህ ጭፍጨፋ የተፈጸመው መጋቢት 21 ቀን 1960 እ.አ.አ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የዘር መድሎ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ ያሳየ እና የትጥቅ ትግል እንዲጀመር ምክንያት የሆነ ክስተት ነው።

የክስተቱ መነሻ በወቅቱ የነበረው አፋኝ “የይለፍ ሕግ” (Pass Laws) ነበር። ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ወደ ነጮች አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ማንነታቸውን የሚገልጽ እና በፖሊስ የሚታይ ሰነድ መያዝ ግዴታቸው ነበር። ይህን ሕግ ለመቃወም የፓን አፍሪካኒስት ኮንግረስ (PAC) ባቀረበው ጥሪ መሠረት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መታወቂያቸውን ባለመያዝ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ “እሰሩን” የሚል የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ። በሻርፕቪል ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት የተሰበሰቡት ሰልፈኞች ቁጥር ወደ 7,000 የሚጠጋ ሲሆን ድባቡ ሰላማዊ እና ዘፈን የተቀላቀለበት ነበር። ይሁን እንጂ ሁኔታው ሳይታሰብ ወደ አስከፊ ግጭት ተቀየረ። ፖሊሶች በሰላማዊው ሕዝብ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው 69 ሰዎች ሲገደሉ ከ180 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። አብዛኞቹ ተጎጂዎች ጥይት ያረፈባቸው በጀርባቸው ላይ ነበር፤ ይህም የሚያሳየው ፖሊሶች የተኮሱት ሕዝቡ አደጋ ለማድረስ ሲመጣ ሳይሆን ከጥቃቱ ለመሸሽ እየሮጠ ባለበት ወቅት መሆኑን ነው። ይህ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ውግዘትን አስከተለ ይላል የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ኦፊሴላዊ ድረ-ገጽ (gov.za) ላይ ያኘነው መረጃ።

የ1976ቱ የሶዌቶ የተማሪዎች አመጽ በአፓርታይድ ታሪክ ውስጥ የወጣቶች የቆራጥነት ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ እና የሥርዓቱን መሠረት ያናወጠ ትልቅ ክስተት ነው። ይህ አመጽ የተቀሰቀሰው ሰኔ 16 ቀን 1976 ዓ.ም ሲሆን መንግሥት በጥቁር ትምህርት ቤቶች ውስጥ “አፍሪካንስ” የተባለውን የነጮች ቋንቋ እንደ ዋና የማስተማሪያ ቋንቋ እንዲሆን ያስገደደውን አዋጅ ለመቃወም ነበር።

በዕለቱ በሶዌቶ (Soweto) መንደር የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች “አፍሪካንስ አያስፈልገንም” እና “እኩል ትምህርት እንፈልጋለን” የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ በሰላማዊ መንገድ ወደ ኦርላንዶ ስታዲየም ማምራት ጀመሩ። ተማሪዎቹ ይህን ቋንቋ “የጨቋኞች ቋንቋ” አድርገው ስለሚቆጥሩት፣ በትምህርታቸው ላይ መጫኑን አጥብቀው ተቃውመዋል። ይሁን እንጂ ሰላማዊው ሰልፍ ባልታሰበ ሁኔታ ወደ ደም መፋሰስ ተቀየረ። የፖሊስ ኃይሎች ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ከተጠቀሙ በኋላ በቀጥታ በተማሪዎቹ ላይ ጥይት መተኮስ ጀመሩ።

በዚህ ጥቃት ወቅት የ13 ዓመቱ ሄክተር ፒተርሰን (Hector Pieterson) በፖሊስ ጥይት ተመትቶ መገደሉ የአመጹ ምልክት ሆነ። የፒተርሰን አስከሬን በሌላ ወጣት ታቅፎ ሲሮጥና እህቱ በአጠገቡ ስታለቅስ የሚያሳየው ፎቶግራፍ በዓለም ዙሪያ በመሰራጨቱ የአፓርታይድ መንግሥት ምን ያህል ጨካኝ እንደሆነ ለዓለም በድጋሚ አጋለጠ። በዚያ ቀንና በቀጣዮቹ ቀናት በተነሳው ግርግር በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል።

የሶዌቶ አመጽ ያስከተለው ውጤት እጅግ ከፍተኛ ነበር። የአፓርታይድ መንግሥት ተማሪዎችን በመግደሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውግዘትና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲበረታበት አድርጓል። በሀገር ውስጥም ቢሆን ይህ አመጽ ብዙ ወጣቶች የነፃነት ትግሉን እንዲቀላቀሉና የፀረ-አፓርታይድ ንቅናቄው አዲስ የትግል መንፈስ እንዲያገኝ ረድቷል። መንግሥትም ቢሆን የተማሪዎቹን ግፊት መቋቋም ስላልቻለ የአፍሪካንስ ቋንቋ የግዴታ ትምህርት እንዲሆን ያወጣውን አዋጅ ለመሰረዝ ተገዷል።

ሰኔ 16 ቀን በደቡብ አፍሪካ “የወጣቶች ቀን” (Youth Day) ተብሎ በታላቅ ክብር ይከበራል። ይህ ክስተት የደቡብ አፍሪካ ወጣቶች ለነፃነታቸው የከፈሉትን መስዋዕትነትና በትምህርት መብታቸው ላይ የነበራቸውን ጽኑ አቋም ሁሌም ያስታውሳል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ለ27 ዓመታት በእስር ያሳለፉት ጊዜ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድ የኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን መረጃ ያመላክታል። ይህ ረጅም የእስር ዘመን በሦስት ዋና ዋና ቦታዎች የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዱ ምዕራፍ በማንዴላ ጥንካሬ እና በዓለም አቀፉ የፖለቲካ ለውጥ ላይ የራሱ አሻራ ነበረው።

ማንዴላ የታሰሩት እ.አ.አ በ1962 ዓ.ም ሲሆን በ1964 ዓ.ም በታዋቂው “የሪቮኒያ ችሎት” (Rivonia Trial) መንግሥትን ለመገልበጥ አሲረዋል በሚል የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ነበር። ሆኖም ፍርዱ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ተቀይሮ ወደ ሮቤን አይላንድ (Robben Island) ተላኩ። በሮቤን አይላንድ ለ18 ዓመታት በቆዩበት ወቅት ማንዴላ “46664” የሚል ቁጥር ተሰጥቷቸው በጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲኖሩ እና ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ተገደዋል። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም እስረኞችን በማስተማርና የፖለቲካ ክርክሮችን በማድረግ እስር ቤቱን “ማንዴላ ዩኒቨርሲቲ” ወደመባል ደረጃ አድርሰውት ነበር።

እ.አ.አ በ1982 ማንዴላ ወደ ፖልስሙር እስር ቤት (Pollsmoor Prison) ተዛወሩ። በእስር ቤቱ በነበሩበት ወቅት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ማንዴላ ይፈቱ” (Free Nelson Mandela) የሚል ከፍተኛ ጫና በመንግሥት ላይ ይበረታ ነበር። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ማንዴላ የትጥቅ ትግሉን ካወገዙ እንደሚፈቱ ቃል ገብቶላቸው የነበረ ቢሆንም እርሳቸው ግን “ሕዝቡ ነፃ ባልሆነበት ሁኔታ እኔ ነፃ ልሆን አልችልም” በማለት ጥያቄውን ውድቅ አደረጉ። ይህ ቁርጠኝነታቸው በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ክብርን አጎናጸፋቸው።

የመጨረሻዎቹ የእስር ዓመታት (ከ1988-1990) በቪክቶር ቨርስተር እስር ቤት (Victor Verster Prison) ያሳለፉ ሲሆን የነበሩበት ሁኔታ ከቀደሙት የተሻለ ነበር። በዚህ ወቅት ከአፓርታይድ መንግሥት ጋር ሚስጥራዊ ድርድሮችን መጀመር ችለው ነበር። በመጨረሻም እ.አ.አ የካቲት 11 ቀን 1990 ዓ.ም በፕሬዝዳንት ኤፍ. ደብሊው ደ ክለርክ ትዕዛዝ ማንዴላ ከእስር ተፈቱ። በዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ፊት በፈገግታና በድል አድራጊነት እጃቸውን ወደ ላይ አንስተው ሲወጡ የታየው ምስል የአፓርታይድ ሥርዓት ማብቂያ መቃረቡን ለዓለም ያበሰረ ታሪካዊ ትዕይንት ነበር።

ማንዴላ ከእስር ቤት ሲወጡ የነበራቸው ትልቁ ስኬት የደረሰባቸውን በደል በመርሳት ለሀገሪቱ ሰላምና እርቅ (Reconciliation) ቅድሚያ መስጠታቸው ነው። ይህ አቋማቸው ደቡብ አፍሪካ ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ ታድጓታል።

 

 

ሳምንቱ በታሪክ

የሰላም ስምምነቱ

የኢትዮጵያና የሶማሊያ የሰላም ስምምነት እ.አ.አ በኤፕሪል 1988 (መጋቢት 29 ቀን 1980 ዓ.ም) ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነት በምሥራቅ አፍሪካ ታሪክ ውስጥ እጅግ ግዙፍ እና ደም አፋሳሽ ከሆኑ ግጭቶች አንዱ ነው። የሶማሊያው መሪ ፕሬዝዳንት ሲያድ ባሬ “ታላቋ ሶማሊያ” የምትባል እና የኢትዮጵያን ኦጋዴን የምትጨምር ሀገር ለመመሥረት በነበራቸው ምኞት በሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም ሰራዊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አስገቡ። የሶማሊያ ጦር መጀመሪያ ላይ እስከ ድሬዳዋ እና ሐረር ደጃፍ ድረስ ዘልቆ በመግባት ሰፊ የኢትዮጵያን ግዛት ተቆጣጥሮ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ውስጥ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና በታጠቁ አማጺያን ጫና ምክንያት ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም “እናት ሀገር ወይም ሞት” በሚል መሪ ሀሳብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጥቁር አንበሳ እና የሚሊሻ ሰራዊትን በማሰለፍ ታላቅ የመከላከል ውጊያ አደረገ።

ይህ ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃም የኃያላን ሀገራትን ትኩረት ስቦ ነበር። ቀደም ሲል ሶማሊያን ሲረዳ የነበረው ሶቪየት ሕብረት (ሩሲያ) ድጋፉን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር ከፍተኛ የጦር መሣሪያ እና አማካሪዎችን ላከ። በተጨማሪም የኩባ ሰራዊት በኢትዮጵያ በኩል ተሰልፎ በውጊያው በቀጥታ መሳተፉ የጦርነቱን ሚዛን ለወጠው። በተለይም በካራማራ ተራራ ላይ የተደረገው ወሳኝ ውጊያ የሶማሊያ ጦር እንዲሸነፍ እና ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ አድርጓል። ጦርነቱ በመጋቢት ወር 1970 ዓ.ም በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ቢጠናቀቅም በሁለቱም ሀገራት ላይ የደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት እጅግ ከፍተኛ ነበር። ይህ ድል የኢትዮጵያን አንድነት ያስጠበቀ ቢሆንም በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ጥርጣሬ እና ውጥረት ለቀጣይ አሥር ዓመታት አባብሶት ቆይቷል።

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጦርነት- አፈንዲ ሙተቂ።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here