በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሞች እየተስፋፉና የነዋሪዎቻቸው ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የነዋሪዎች ቁጥር መጨመርም ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች ፍላጎት እንዲያድግ እንዲሁም የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት ኾኗል፡፡
የተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የምግብ ፍላጎትን ለማሟላት እንዲሁም የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ “የከተማ ግብርናን በተጠናከረ ሁኔታ እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ አነስተኛ የእርሻ መሬት ያላት ሲንጋፖር በዚህ ረገድ በዓለም ላይ በምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ ሲንጋፖር በሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እንዲሁም በቤት ውስጥ መደርደሪያዎች ላይ ሰብሎችን በማምረት የምግብ ፍላጎቷን ለማሟት እየጣረች ነው።
አፈር ሳያስፈልግ በውኃ እና በንጥረ-ነገሮች ብቻ ተክሎችን ማሳደግ፣ የመኪና ማቆሚያዎች እና የመንግሥት ቤቶች ጣሪያ ላይ አትክልቶችን ማምረት ለምግብ የሚውሉ የምርት ፍጆታዎችን ለማሟላት የምትከተላቸው አማራጮች ናቸው፡፡ ይህ ጥረቷም ዜጎች ከተማ ውስጥ የተመረቱ ትኩስ አትክልቶችን እንዲያገኙ አስችሏል።
የከተማ ግብርና አምራቹ በምግብ ሰብል ራሱን እንዲችል ከማድረጉ በተጨማሪ አምራቹ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ለገበያ መረጋጋቱ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ለሀገር ዕድገትም የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው፡፡
የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከመርዳቱ በተጨማሪም ለወጣቶች እና ለቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አዲስ የሥራ መስክ የሚከፍት፣ ነዋሪዎች እንዲገናኙ እና አብረው እንዲሠሩ ዕድል የሚሰጥ፣ የሙቀት መጠንን የሚቀንስ መልካም ርምጃ ነው፡፡ ይህ ተሞክሮ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ፈጣን የከተማ ዕድገት ላላቸው ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
ከዚህ በመነሳት ሀገራችን ኢትዮጵያም የከተማ ግብርናን መተግበር ጀምራለች፡፡ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እየታየ ያለው ተሞክሮም ዘርፉ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለምጣኔ ሀብታዊ ሽግግር ያለውን ትልቅ አቅም አመላካች ነው፡፡ የከተማ ግብርናን ፋይዳ የተረዱ አርሶ አደሮች በወተት፣ በአሳ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በችግኝ ማፍላት ሥራ ተሰማርተው ስኬታማ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ የግል ገቢያቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለወገኖቻቸው የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡
የሲንጋፖርም ኾነ የሀገራችን የከተማ ግብርናን የማስፋፋት ውጤት የሚያስገነዝበን ቁም ነገር ይህንን የከተማ ግብርናን የማስፋፋት ጥረት አጠናክረን መቀጠል ያለብን ስለመኾኑ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ባለችን ክፍት ቦታ የከተማ ግብርናን ልንተገብር ይገባናል፡፡ የሚመለከተው አካልም የከተማ ነዋሪው ያሉትን ክፍት ቦታዎች በመጠቀም አልምቶ ተጠቃሚ እንዲሆን በሥልጠና እንዲሁም ለልማቱ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማቅረብ፣ በማማከር… የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በተለይም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማዘመን፣ ባዶ ቦታዎችን ለልማት ለሚፈልጉ ወጣቶች በማመቻቸት የከተማ ግብርና ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ የላቀ ጥረት አለበት፡፡
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


