የተጫዋቾች የአካል ብቃት ፈተና

0
98

እግር ኳስ የጉልበት፣ የፍጥነት እና የጽናት ጨዋታ ነው:: የዘመናዊው እግር ኳስ ውበት የሚለካውም ተጫዋቾች ከመጀመሪያው ፊሽካ እስከ መጨረሻው ሴኮንድ ድረስ በሚያሳዩት ፉክክር ነው:: በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ የሚደረጉ አብዛኛዎቹ ጨዋታዎች በከፍተኛ ፍጥነት እና ስሜት ቢጀምሩም ጨዋታው  60ኛውን እና 70ኛውን ደቂቃ ሲሻገር ሜዳው ላይ ያለው ትዕይንት ሙሉ በሙሉ ይቀየራል:: የተጫዋቾች ጉልበት ይዳከማል፤ የጨዋታው ፍጥነትም በእጅጉ ሲቀንስ ይስተዋላል:: የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች ዘመናዊው እግር ኳስ የሚጠይቀውን የ90 ደቂቃ ጫና መቋቋም እየተሳናቸው ይገኛል:: ይህ የአካል ብቃት መዳከም ችግር በኢትዮጵያ ትልቁ የሊግ እርከን የዘወትር መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቀጥሏል:: በሊጉ የሚጫወቱ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ድካም ሳይሰማቸው እና በከፍተኛ ብቃት መጫወት የሚችሉት በአማካይ ከ60 እስከ 70 ደቂቃዎች ብቻ እንደሆነ ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የእግር ኳስ ባለሙያው  አቶ አማን ሞላ ተናግረዋል:: ከ60ኛው እና 70ኛው ደቂቃ በኋላ በተጫዋቾች ላይ ግልጽ የሆነ የጉልበት መዛል እና የትኩረት ማጣት ችግር እንደሚስተዋል የእግር ኳስ ባለሙያው ይናገራሉ:: “በፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ በእጅጉ ፉክክሩ ይቀዘቅዛል:: ቡድኖች ኳስ ይዘው ወደ ፊት የሚሄዱበት ፍጥነትም ይቀንሳል፤ ተጫዋቾች ኳስ ለማስጣል የሚያደርጉት ጫናም ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ ሙሉ በሙሉ ይቆማል ማለት ይቻላል” በማለት አቶ አማን ያስረዳሉ::

ሌላው ብዙ ተጫዋቾች ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ ሜዳ ላይ በጡንቻ መሳሳብ ጉዳት እየገጠማቸው ይገኛል:: ይህ የሆነውም የአካል ብቃታቸው ደካማ በመሆኑ ነው ሲሉ ባለሙያው አቶ አማን ተናግረዋል:: በተጨማሪም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የሚፈጸሙ ስህተቶች  እና መከላከል ሲቻል የሚቆጠሩ ግቦች የአካል ብቃት መዳከም ማሳያዎች ናቸው:: የአካል ብቃት ሲዳከም የአእምሮ ንቃት አብሮ ይቀንሳል:: በዚህም የተነሳ ከ75ኛው ደቂቃ በኋላ በታክቲክ እና በግል ስህተቶች የሚቆጠሩ ግቦች በሊጉ እጅግ ይበዛሉ:: በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ75ኛው ደቂቃ እስከ ተጨማሪ ደቂቃዎች ድረስ የሚቆጠሩ ግቦች አብዛኛዎቹ ከተከላካዮች የትኩረት ማጣት የሚመነጩ ናቸው::

በአውሮፓ ሊጎች አብዛኛውን ጊዜ በሳምንት አንድ ጨዋታ እንደሚካሄድ ያነሱት አቶ አማን በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግን ክለቦች በሁለት እና በሦስት ቀናት ልዩነት ወደ ሜዳ እንዲገቡ መገደዳቸው ሌላኛው ፈተና መሆኑን ያስረዳሉ:: ሊጉ በአንድ ከተማ መካሄዱ ጉዳት የገጠማቸው ተጫዋቾች ለማገገም ጊዜ እንዳያገኙ እና በሙሉ የአካል ብቃት ጨዋታውን እንዳይጨርሱ አድርጓቸዋል ተብሏል::

የተጫዋቾችን ትክክለኛ እድሜ እና ሌሎች መረጃዎችን በተገቢው መንገድ ሰንዶ አለማስቀመጥም ችግሩን የከፋ አድርጎታል:: “ሃያ አራት ወይም ሃያ ስምንት ዓመት የሚሆናቸው ተጫዋቾች እድሜያቸው ከዛ በላይ እንደሚሆን እንገምታለን:: ስለዚህ የአካል ብቃታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብለዋል አቶ አማን ሞላ::

የክለቦች ልምምድ አሁንም ድረስ በባህላዊ መንገድ የሚመራ ነው:: ምንም እንኳ ክለቦች የተጫዋቾችን የአካል ብቃት ችግራቸውን ለመቅረፍ የአካል ብቃት አሰልጣኞችን ቢቀጥሩም አካሄዱ ሳይንሳዊ መሰረት የጎደለው በመሆኑ የተፈለገውን ለውጥ እያመጣ አለመሆኑን ባለሙያዎች ይመሰክራሉ:: ታዲያ የአካል ብቃት ስልጠና ያለ ተገቢ የምግብ ስርዓት ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል አቶ አማን ይናገራሉ::

የተጫዋቾች የአመጋገብ ስርዓት ከፕሮፌሽናል ስፖርተኛ ይልቅ ወደ አብዛኛው ማህበረሰብ አመጋገብ ያደላ ነው:: “የአካል ብቃት አሰልጣኝ ብቻውን ውጤታማ አያደርግም:: የተሰራው እንቅስቃሴ ምን አይነት ምግብ ያስፈልገዋል የሚለውን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የሚጠቀሙ ክለቦች በእርግጠኝነት ከሌሎቹ ከፍ ሊሉ ይችላሉ” በማለት የስነ ምግብ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ የእግር ኳስ ባለሙያው አቶ አማን ሞላ ያሰምሩበታል::

ተጫዋቾች በመጀመሪያዎቹ አጋማሾች ጉልበታቸውን በአግባቡ ሳይቆጥቡ በስሜት መጫወታቸው  ሌላኛው ለችግሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ምክንያት ነው:: እንደ አቶ አማን ሞላ ገለጻ አንድ ተጫዋች መቼ መሮጥ እና መቼ ቦታ መያዝ እንዳለበት በአእምሮው አስልቶ ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር ቶሎ አቅሙ ይዳከማል:: “ኢኮኖሚካል ራን ካላደረገ ኳስ መድረስ ሳይችል ቀርቶ በከንቱ የሚሮጥ ከሆነ ያ ፊትነሱ ላይ ጉዳት ያመጣል” የሚሉት የእግር ኳስ ባለሙያው ልምድ ያላቸው አንጋፋ ተጫዋቾች ይህንን የጉልበት አጠቃቀም ስልት ስለሚያውቁበት የተሻለ ኳስ ሲያቀብሉ እንደሚታዩ ይገልጻሉ:: የአካል ብቃት መዳከም እና የትኩረት ማጣት ችግር ተጫዋቾች ቀላል ኳሶችን እንዲያበላሹ አድርጓቸዋል፤ እያደረጋቸውም ነው::

መጫዎቻ ሜዳዎች ለጨዋታ አመቺ ባለመሆናቸው ተጫዋቾች ኳስን ለመቆጣጠር ብቻ ተጨማሪ እና ያልተፈለገ ጉልበት እንዲያወጡ ያስገድዳቸዋል:: ይህ ደግሞ ለአካል ብቃት መዳከም የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የእግር ኳስ ባለሙያው ያብራራሉ:: አሰልጣኞች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሃያ ወይም ሰላሳ ደቂቃ ሲቀረው አዲስ ስልት በመንደፍ የደከሙ አንጋፋ ተጫዋቾችን በማስወጣት ከሃያ ዓመት በታች የሆኑ ወጣት እና ጉልበት ያላቸውን ታዳጊዎች ወደ ሜዳ በማስገባት የጨዋታውን ፍጥነት ለመቀየር የሚሞክሩት በዚህ ምክንያት መሆኑን አቶ አማን ሞላ ተናግረዋል:: “ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተሻለ ተቀያሪ ያስገባ ቡድን የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ግቦች ሲቆጠሩ የምናይበት ሁኔታ አለ” በማለት ያስረዳሉ::

ይህ የሚያሳየው አሰልጣኞች የጨዋታውን የመጨረሻ ደቂቃዎች ክፍተት የሚሸፍኑት በታክቲክ ብልጫ ሳይሆን ትኩስ ጉልበት ያላቸውን ወጣቶች በማስገባት መሆኑን ነው:: በሰባኛው ደቂቃ አካባቢ አብዛኛው የቡድን አባል ጉልበቱ ስለሚሟጠጥ የተደራጀ የማጥቃት ወይም የመከላከል ስራ ለመስራት አሰልጣኞች እጅግ ይቸገራሉ:: ተጫዋቾች ሙሉ 90 ደቂቃ በተመሳሳይ ብርታት እንዲጫወቱ ክለቦች ሰፊ የተጫዋቾች ስብስብ መገንባት ይጠበቅባቸዋል:: ክለቦች የተጫዋችን የአካል ብቃት አቅማቸውን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የአካል ብቃት አሰልጣኞች ብቻ ሳይሆኑ የስነ ምግብ ባለሙያዎችንም መቅጠር እና ዘመናዊ የህክምና ቁሶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል::

ተጫዋቾች ዘጠና ደቂቃ በሙሉ ብቃታቸው ለመጫወት ከክለብ ልምምድ ውጪ የራሳቸውን የአካል ብቃት እና አመጋገብ በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት እንዳለባቸው ይመክራሉ፤ ሜዳ ላይም ጉልበታቸውን በብልሀት መጠቀምን መልመድ ይኖርባቸዋል:: አላስፈላጊ ሩጫዎችን በመቀነስ አእምሮን በሚያሰራ እግር ኳስ ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልጋቸውም አቶ አማን ይጠቁማሉ:: የጨዋታ መርሃ ግብር አወጣጥ የተጫዋቾችን ጤንነት እና ማገገሚያ ጊዜ ያገናዘበ መሆን አለበት፤ ሜዳዎችን ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግ እና ተጫዋቾች ገና በልጅነታቸው ትክክለኛውን የአካል ብቃት መሰረት እንዲይዙ መስራት የአወዳዳሪው አካል እና የፌዴሬሽኑ የቤት ሥራ መሆኑን አቶ አማን ሞላ አስገንዝበዋል::

 

 

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here