በስፖርቱ ዓለም የአእምሮ ጤና የተዘነጋ እና በዝምታ የታለፈ ትልቅ አደጋ መሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልጽ እየታየ መጥቷል:: ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች፣ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ድረገጾች የሚፈጥሩት የማያባራ ጫና ስፖርተኞችን ወደ አደገኛ የስነልቦና ቀውስ እየገፋቸው መምጣቱን የታይም መጽሔት እና ኢኤስፒኤን ስፖርት መረጃ ያስነብባል::
የስፖርተኞች የአእምሮ ጤና ለዘመናት ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱ አይዘነጋም:: ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በርካታ ስመጥር ስፖርተኞች ስለሚገጥማቸው ከባድ የስነልቦና ጫና በግልጽ መናገር መጀመራቸው ጉዳዩ የዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮች ትልቅ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል:: የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያቶች እጅግ ውስብስብ እና ከስፖርተኞቹ አኗኗር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው መሆኑን የኢኤስፒኤን መረጃ ያስነብባል::
አንድ ስፖርተኛ ሁልጊዜ የተሻለ ለመሆን እና ድልን ለመቀዳጀት የሚያደርገው ጥረት ሳያውቀው ፍጹምነትን ወደ መፈለግ አባዜ እንደሚወስደው ታይም መጽሔት አስነብቧል:: ይህ የፍጹምነት ፍላጎት ስፖርተኛው በራሱ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲፈጥር እና ስህተት ላለመስራት ዘወትር እንዲጨነቅ ያደርገዋል:: በተጨማሪም ውድቀትን አሊያም መሸነፍን አጥብቆ መፍራት ሌላው የውስጥ ችግር እንደሆነ መረጃው ያስነብባል:: ብዙ ስፖርተኞች ሙሉ ማንነታቸውን እና በህይወት የመኖር ዋጋቸውን የሚያዩት ከሚያመጡት የሜዳ ላይ ውጤት ጋር ብቻ አያይዘው መሆኑ የሚደርስባቸውን የአእምሮ ጤና ችግር የከፋ አድርጎታል::
ታዲያ ስፖርተኞች ሲሸነፉ ወይም በቂ ውጤት ሳያመጡ ሲቀሩ እኔ ዋጋ የለኝም ወደሚል ጥልቅ የድብርት ስሜት ውስጥ ይገባሉ:: ሌላው ስፖርተኞችን ለአእምሮ ጤና መቃወስ ከሚዳርጉ ውስጣዊ ምክንያቶች መካከል አካላዊ ጉዳት እንደሚገኝበት የዘ ጋርዲያን መረጃ ያሳያል:: አንድ ስፖርተኛ ጉዳት አጋጥሞት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ሲርቅ ወደ ቀድሞ ብቃቴ መመለስ አልችልም የሚል ፍርሃት ያድርበታል:: ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ ለአእምሮ ጤና መቃወስ ችግር ይዳርገዋል ይላል መረጃው::
ደጋፊዎች፣ አሰልጣኞች እና የሚዲያ ተቋማት ዘወትር ማሸነፍን ብቻ መጠበቃቸው ስፖርተኞችን ለከፋ የአእምሮ የጤና ችግር የሚዳርግ ውጫዊ ምክንያት ነው:: በተለይም በዘመናችን የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል:: ስፖርተኞች በውድድር ላይ ትንሽ ስህተት ሲሰሩ በማህበራዊ ሚዲያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ስድብ፣ ዛቻ እና የዘረኛ ጥቃቶች ይሰነዝሩባቸዋል:: ይህ ዓይነቱ ጥቃት ስፖርተኞች ራሳቸውን እንዲጠሉ እና ከባድ ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል::
የችግሩ አደገኛነት ግን ስፖርተኞች ድክመታቸውን ላለማሳየት ሲሉ በዝምታ መሰቃየትን ከመረጡ መሆኑን የታይም መጽሔት ዘገባ ያስረዳል:: ብዙዎቹ ደግሞ ደካማ ተብዬ ከቡድን እገለላለሁ አሊያም ስፖንሰሮች ይሸሹኛል በሚል ፍርሃት ህመማቸውን ደብቀው ብቻቸውን እንደሚሰቃዩ መረጃው አስነብቧል:: ይህ የተዳፈነ ጭንቀት እና ድብርት በመጨረሻ ብዙዎችን ለአደንዛዥ እፅ፣ ለአልኮል እና ለተለያዩ ሱሶች እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል::
በዚህም ምክንያት ሙሉ በሙሉ በለጋ እድሜያቸው ከስፖርቱ ዓለም የጠፉ በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ስፖርተኞች መኖራቸውን መረጃዎች አመልክተዋል:: ለአብነት የቀድሞው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሮበርት ኢንኬ ለዓመታት ከከባድ ድብርት ጋር ይታገል እንደነበር የግል የታሪክ ማህደሩ ይነግረናል:: በተለይ የልጁን መሞት ተከትሎ ህመሙ ቢባባስም ለማንም ሳይናገር በዝምታ መታገሉ የጤና መታወክ አድርሶበታል:: በመጨረሻም ጫናው መቋቋም ሲከብደው እ.አ.አ በ2009 ራሱን ማጥፋቱ አይዘነጋም::
በአለማችን ላይ ከነበሩ ምርጥ አጥቂዎች አንዱ የነበረው ብራዚላዊው አድሪያኖ በአእምሮ ጤና ችግር ምክንያት የዓለም እግር ኳስ ያጣው ባለተሰጥኦ ነው:: አድሪያኖ አባቱ በድንገት ሲሞት ድብርት ውስጥ በመግባቱ ህመሙን ለማስታገስ ወደ ከባድ የአልኮል መጠጥ ሱስ እንደገባ ዘ ፕላየርስ ትሪቡን አስነብቧል:: የት ይደርስ ይሆን? የተባለለት የእግር ኳስ ኮከብ አሁን ላይ የትውልድ መንደሩን ሪዮ ቪላ ክሩሴይሮስ ጎዳናዎች በባዶ እግሩ ያካልላል:: የቀድሞው የዌልስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና ተጫዋች የነበረው ጋሪ ስፒድ ከፍተኛ ድባቴ እንደነበረበት ሳይታወቅ በድንገት ራሱን ሰቅሎ መሞቱ የስፖርቱን ዓለም ክፉኛ ያሳዘነ ክስተት እንደነበር ስካይ ስፖርት አስነብቧል::
በሌላ በኩል የጨለማውን ጊዜ አሸንፈው ወደ ብርሃናቸውን የፈነጠቁ እና ለሌሎች አርአያ መሆን የቻሉ በርካታ ታዋቂ ስፖርተኞች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም:: በኦሎምፒክ ታሪክ በርካታ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ክብረ ወሰን የያዘው አሜሪካዊው ዋናተኛ ማይክል ፌልፕስ እ.አ.አ 2012 ኦሎምፒክ በኋላ ከባድ ድብርት ውስጥ ገብቶ ራሱን እስከማጥፋት አስቦ እንደነበር በግልጽ ተናግሯል:: ነገር ግን ወደ ማገገሚያ ማዕከል በመግባት ህክምና በማግኘቱ ሙሉ በሙሉ ድኖ አሁን ላይ የአእምሮ ጤና ግንዛቤ ፈጣሪ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል:: አሜሪካዊቷ የጅምናስቲክስ ኮከብ ሲሞን ባይልስም በቶኪዮ ኦሎምፒክ በአእምሮ ጤና ችግር ምክንያት ከውድድር ራሷን ማግለሏ የሚታወስ ነው:: ሲሞን ባይልስ ለሁለት ዓመታት ያህል ህክምናዋን ከተከታተለች በኋላ በፓሪስ ኦሎምፒክ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ችላለች::
ስፔናዊው የቀድሞው የማሀል ሜዳ ሞተር አንድሬስ ኢኒየስታም የቅርብ ጓደኛው በድንገት በመሞቱ በአእምሮ ጤና መታወክ ችግር ህይወቱ አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር “The Artist: Being Iniesta” በተሰኘው የህይወት ታሪኩ መጽሐፉ ይገልጻል:: የሜዳ ቴኒስ ኮከቧ ናኦሚ ኦሳካም በሚዲያ ጫና ምክንያት ከገጠማት ከባድ ጭንቀት በሽታ ያገገመች ሌላኛዋ ተጠቃሽ ስፖርተኛ ነች::
እነዚህ ስፖርተኞች ከገቡበት ከባድ ቀውስ ሊያገግሙ የቻሉበት ዋናው መንገድ ዝምታን መስበር እና ችግሩ እንዳለባቸው አምነው በግልጽ መናገራቸው እንደሆነ ታይም መጽሄት ያስነብባል:: በተጨማሪ ከስፖርታዊ ውድድሮች እና ልምምዶች ርቆ ጊዜያዊ እረፍት መውሰድ አእምሮን ለማደስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው ጭምር መረጃው ይነግረናል::
ችግር ከመፈጠሩ በፊት ግን ስፖርተኞች የአእምሮ ጤና ቀውስ እንዳይገጥማቸው የአእምሮ ጤና ምርመራ እና የምክር አገልግሎት በቋሚነት ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው መረጃዎች አስነብበዋል:: ስፖርተኞች ስፖርት ሥራቸው እንጂ ሙሉ ማንነታቸው እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ መደረግ አለበት፤ አሰልጣኞች እና ማህበረሰቡ ስፖርተኛውን እንደ ሮቦት ሳይሆን ስሜት እንዳለው ሰው ማየት መልመድ አለባቸው፤ አእምሮ ራሱን እንዲጠግን በቂ የእንቅልፍ ሰዓት እና ከውድድር በኋላ በቂ የዕረፍት ጊዜ ማግኘት ወሳኝ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ይላል መረጃው::
ስፖርተኞች ማህበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙበትን ጊዜ መገደብ እና የሚሰነዘሩባቸውን ትችቶች እንዴት መቀበል እና ማለፍ እንዳለባቸው ተገቢ ስልጠና ሊሰጣቸው እንደሚገባ የጠቆመው ደግሞ ቢቢሲ ስፖርት ነው:: የአእምሮ ጤና ችግር የስፖርተኞች የድክመት ምልክት ሳይሆን ከፍተኛ ጫና ባለበት አካባቢ የመስራት ተፈጥሯዊ ውጤት መሆኑን አምኖ መቀበል እንደሚገባ የታይየም መጽሔት መረጃ አመልክቷል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


