“ወሬ ቢነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት”

0
81

ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን እና እናቶቻችን የምዕራባውያንን የፍልስፍና አዳራሾች አልረገጡም፤ የ”ክሪቲካል ቲንኪንግ” የማመዛዘን ትምህርትን በዩኒቨርሲቲ አልተማሩም። ነገር ግን የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ልዕልና ጣሪያ የሆነውን ይህንን ጥልቅ የፍልስፍና ጽንሰ-ሀሳብ  በአንዲት አጭር እና ምትሃታዊ አባባል ቀምረው ትተውልናል። “ወሬ ቢነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት!” ሲሉ።

ይህ አባባል ዝም ብሎ የቃላት ድርድር አይደለም። መረጃን  ወደ ዕውቀት፣ ዕውቀትን ደግሞ ወደ ጥበብ የመቀየር ጥልቅ የሳይንስ እና የፍልስፍና ሂደት ነው። ወሬ ጥሬ እውነታ ነው። ወሬኛው ያመጣው ያልተጣራ መረጃ ወይም የራሱ ትርክት ነው።

ሀሳብ መጨመር ማለት ግን ያንን ጥሬ መረጃ በማመዛዘን ሚዛን ላይ ማስቀመጥ፣ “ለምን? መቼ? እንዴት? ማንስ አለ? ዓላማውስ ምንድን ነው?” ብሎ መመርመር ማለት ነው። ታላቁ ግሪካዊ ፈላስፋ ሶቅራጥስ “ያልተመረመረ ህይወት ሊኖርበት አይገባም” እንዳለው ሁሉ የኛዎቹ ሊቃውንት ደግሞ “ያልተመረመረ ወሬ ሊታመንበት አይገባም” ማለታቸው ነበር።

ነገር ግን፣ ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስንመለከት የዚህች ሀገር ዘመናዊ ትውልድ ከዚህ የጠራ የአባቶቹ የስነ-ልቦና ከፍታ ላይ ክፉኛ ተንሸራትቶ ወድቋል። ዛሬ መዳፋችን ላይ ዓለምን የሚያህል የመረጃ ቋት (ስማርት ፎን) ይዘናል፤ ነገር ግን ጭንቅላታችን ውስጥ መረጃን የሚያላምጥ፣ የሚመረምር እና የሚያገናዝብ ‘የሀሳብ ማሽን’ ተበላሽቷል።

ትውልዱ “አሉ” የተባለውን ሁሉ እንደ ወረደ እንደ ፍጹም እውነት ይውጣል። “እንዲህ ነው” ሲሉት ወደ ቀኝ ይነዳል። “አይደለም እንደዚያ ነው” ሲሉት ደግሞ ተገልብጦ በጅምላ ወደ ግራ ይነጉዳል።

አንድ ሰው ብቻውን ሲሆን ሊያስብ፣ ሊያመዛዝን እና ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ማሰብ ያቆመ ትውልድ ከመንጋው ጋር ሲቀላቀል ማንነቱን ያጣል። ፈረንሳዊው የስነ-ልቦና አጥኚ እና ፈላስፋ ጉስታቭ ለ ቦን  እ.ኤ.አ. በ1895 በጻፈው እና ዓለምን ባስገረመው “ዘ ክራውድ፡ ኤ ስተዲ ኦፍ ዘ ፖፑላር ማይንድ” (The Crowd: A Study of the Popular Mind) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ይህንን አደገኛ አዝማሚያ በሚገባ አስቀምጦታል።

ለ ቦን እንደሚለው “አንድ ግለሰብ የመንጋው አካል ሲሆን የራሱን ንቃተ-ህሊና እና ምክንያታዊነት ያጣል፤ በምትኩ ስሜታዊ፣ አረመኔያዊ እና በሌሎች በቀላሉ የሚነዳ ፍጡር ይሆናል።”

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ይሄንኑ ነው። “አሉ” የሚለው ቃል የዘመናችን ትልቁ የጥፋት መሳሪያ ሆኗል። “እገሌ እንዲህ አለ፣ እገሌ እንዲህ አደረገ” የሚል ያልተጣራ እና ሀሳብ ያልተጨመረበት ወሬ በማህበራዊ ሚዲያ ሲለቀቅ ትውልዱ እውነታውን የማጣራት ትዕግስትም ሆነ አቅም የለውም። የስዊዘርላንዳዊው የስነ-አእምሮ ሊቅ ካርል ዩንግ አባባል እዚህ ላይ ትዝ ይላል። “ሰዎች ሀሳብ አይኖራቸውም፤ ሀሳቦች ግን ሰዎች  ይኖሯቸዋል” (People don’t have ideas; ideas have people) ብሎ ነበር።

ዛሬ ትውልዱ የራሱ የሆነ የተመረመረ ሀሳብ የለውም፤ ይልቁንም በሌሎች የፖለቲካ ነጋዴዎች እና አክቲቪስቶች በተጠነሰሰ የ”አሉ” ሀሳብ እንደ አሻንጉሊት እየተዘወረ ነው።

በስነ-ልቦናው ዓለም የኖቤል ተሸላሚ የሆነው ዳንኤል ካህነማን  “ቲንኪንግ፣ ፋስት ኤንድ ስሎው” በተሰኘው  መጽሐፉ ላይ የሰውን ልጅ አእምሮ በሁለት ይከፍለዋል። አንደኛው ፈጣን፣ ስሜታዊ፣ በደመ-ነፍስ የሚሠራ እና ጥረት የማይጠይቅ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የሰከነ፣ ትንታኔያዊ፣ ጥረት የሚጠይቅ እና ምክንያታዊ ነው።

የጥንት አባቶቻችን “ወሬ ቢነግሩህ” ሲሉ የአንደኛውን ፈጣን የመረጃ መቀበል ሂደት ማለታቸው ነው። “ሀሳብ ጨምርበት” ሲሉ ግን ሁለተኛውን  የትንታኔ እና የማመዛዘን የረቀቀ የአእምሮ ክፍል አነቃቃው ማለታቸው ነበር።

ነገር ግን ዛሬ ማህበራዊ ሚዲያው በፈጠረው የፍጥነት አባዜ ውስጥ ትውልዱ ማመዛዘንን  አጥፍቶታል። ሁሉም ነገር በስሜት እና በደመ-ነፍስ ብቻ ይመራል።

ለዚህም ነው እንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትራንድ ራስል “አብዛኛው ሰው ከማሰብ ይልቅ መሞትን ይመርጣል፤ በተግባርም ያደርገዋል” በማለት የተሳለቀው። ማሰብ (ሀሳብ መጨመር) ጉልበት ይጠይቃል፤ ከራስ አመለካከት ጋር መጋጨትን፣ እውነትን ፍለጋ መድከምን ይጠይቃል። ስለዚህ በርከት ያለው አዲሱ ትውልድ ከማሰብ ይልቅ ዝግጁ ሆኖ የቀረበለትን የ”አሉ” ትርክት መዋጥን እንደ ቀላል መንገድ መርጧል።

አብዛኛው የዘመኑ ትውልድ መረጃን የሚፈልገው እውነትን ለማግኘት ሳይሆን አስቀድሞ በውስጡ ያመነበትን የጥላቻም ሆነ የድጋፍ ስሜት የሚያጸድቅለት (ሚያረጋግጥለት) ነገር ለማግኘት ነው። ይህ በሳይንሱ “የማረጋገጫ አድልዎ” (Confirmation Bias) ይባላል። አንድ አክቲቪስት ወይም ፖለቲከኛ የትውልዱን የጎሳ ወይም የፖለቲካ ስሜት የሚኮረኩር “ወሬ” ይዞ አብዛኛው ወጣት ሀሳብ አይጨምርበትም፤ አይመረምርም። ወዲያውኑ “እውነት ነው” ብሎ ያሰራጫል። በተቃራኒው ደግሞ እሱ ከሚያምንበት ቡድን ሀሳብ ውጭ የሆነ እውነተኛ እና ተጨባጭ መረጃ እንኳን ቢመጣ “አይደለም! ውሸት ነው!” ብሎ በአንድ ድምጽ ይጮሃል።

ማህበራዊ ሚዲያው (Algorithms) ይህንን ስነ-ልቦናዊ ድክመት በሚገባ ስለሚረዳ ትውልዱን የራሱ ድምጽ ብቻ ወደሚሰማበት “የማስተጋቢያ ክፍል” ውስጥ ቆልፎበታል። አንተ የምትሰማው አንተኑ የሚመስሉ ሰዎችን ብቻ ነው፤ በዚህም ምክንያት የዓለም እውነት የአንተ መንደር እውነት ብቻ እንደሆነች አድርገህ እንድታስብ ትገደዳለህ። እዚህ ውስጥ የአመዛዝኖ ማሰብ ሞት ይታወጃል።

የማያስብ  እና በመንጋ የሚነዳ ትውልድ መጨረሻው ደም መፋሰስን ማስከተል ነው። ጀርመናዊቷ ፈላስፋ ሀና አረንት  “አይክማን ኢን ጀሩሳሌም” በተሰኘው መጽሐፏ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዶችን ያስገደሉት የናዚ የጦር መኮንኖች ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ ጭራቆች  ሆነው እንዳልነበር ተንትናለች። ይልቁንም “የማሰብ አቅማቸው ያቆመ፣ መንጋው እና መሪያቸው ያለውን ያለምንም ማመዛዘን የሚፈጽሙ ተራ ሰዎች ነበሩ። እሷ ይህንን “የክፋት ተራነት” ትለዋለች። ክፋት የሚመነጨው ከአጋንንትነት ሳይሆን ከማሰብ  እጦት ነው።

ማሰብ ያቆመ ትውልድ በቀላሉ ገዳይ ሊሆን ይችላል። ዛሬ በሀገራችን “እገሌ እንዲህ አለ” በሚል የፈጠራ ወሬ ብቻ የራሱን ወንድም የሚገድለው፣ ከተማ የሚያቃጥለው እና ሀገርን ወደ ቀውስ የሚገፋው ይሄው ሀሳብ የማይጨምር እና በመንጋ የሚነዳ የትውልድ ክፍል ነው። አብዛኛው የሃገራችን ዜጋ የአሻጥር ፖለቲከኞች እና የጥላቻ ነጋዴዎች ርካሽ የጦር መሳሪያ  ሆኗል። አእምሮውን በፈቃዱ ለሌሎች አሳልፎ ስለሰጠ፣ እንደ ሪሞት ኮንትሮል ከርቀት ይዘወራል።

ይህንን የሀገር የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ወደ ቀድሞ አባቶቻችን የጥበብ ከፍታ መመለስ ግድ ይለናል። በየደረጃው ያሉ ትምህርት ቤቶቻችን  ምን ማሰብ እንዳለባቸው ሳይሆን “እንዴት ማሰብ እንዳለባቸው” ለተማሪዎች ማስተማር አለባቸው። ማንበብ እንጂ ማመዛዘን ያልቻለ፤ የቃላት ክምችት እንጂ የአስተሳሰብ ልዕልና የሌለው፤ መረጃን እንጂ እውነትን መለየት ያቃተው ትውልድ የራሱንም ሆነ የሀገሩን መቃብር ከመቆፈር አይድንም።

ሁሉም ሰው ቆም ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይገባል። “ይህ የምሰማው ነገር እውነት መሆኑን በምን አረጋገጥኩ?፤ ምንጩስ ምንድን ነው?፤ የታመነ ነው?፤ ይህንን ወሬ የሚያሰራጨው አካል የተደበቀ አላማ (Motive) ምንድን ነው?፤ የእኔስ ስሜታዊ ድክመት በዚህ ወሬ ውስጥ እየተበዘበዘ ይሆን?፤ ተቃራኒው ሀሳብስ ምን ሊሆን ይችላል?” ብሎ መጠየቅ አለበት።

እነዚህ ጥያቄዎች የአንድ አሰላሳይ አሳቢ መነሻዎች ናቸው። ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሬኔ ዴካርትስ  “አስባለሁ፣ ስለዚህ አለሁ” እንዳለው የሰው ልጅ መለኪያው ማሰቡ ነው። ካላሰብን፣ ሌሎች ካሰቡልን፣ እኛም የለንም፤ እኛ የሌሎች ሀሳብ ማራመጃ መሣሪያ ብቻ ነን።

እውነተኛ ነጻነት የሚጀምረው ከአእምሮ ነጻነት ነው። የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ነጻነት ከነጻ እና ከሚያገናዝብ አእምሮ ውጭ ትርጉም የላቸውም። ስለዚህ ከመንጋው ማዕበል ተርፈን ራሳችንን እና ሀገርን ማዳን ከፈለግን የዚያች ጥንታዊት ኢትዮጵያ ፍልስፍና ጠባቂ መሆን አለብን። ወሬ ቢነግሩንም ሀሳብ መጨመር አለብን!

 

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዚያ  12  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here