የአርሴናል የሚያዝያ ወር እርግማን

0
71

የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን የመጨረሻው ምዕራፍ እየተቃረበ ይገኛል:: ፉክክሩም እንደ ኔት ፍሊክስ ተከታታይ ፊልም ይበልጥ አጓጊ እየሆነ መጥቷል:: ማንቸሰተር ሲቲ እንደባለፉት ሦስት ዓመታት ሁሉ የሚያዝያ ወር ሲገባ ከተኛበት ተነስቷል፤ በመድፈኞቹ ጆሮ ላይ መተንፈስ ሲጀምር የሰነበተው አሁን ማንቸሰተር ሲቲ ሊጉን መምራት ጀምሯል:: ኤምሬትስም መሸበር ከጀመረ ውሎ አድሯል:: ካባለፉት ስህተቶቹ መማር ያልቻሉት መድፈኞቹ ዘንድሮም አስቸጋሪው ዳገት ላይ ሲደረሱ ጉልበታቸው ሲዝል ታይተዋል::

የአርሴናል የ2025/26 የውድድር ዘመን ጉዞ አስደናቂ የሚባል ነበር፤ ቡድኑ በሚኬል አርቴታ ስር የተገነባውን ጠንካራ ስብስብ ይዞ ዘንድሮም ለዋንጫው ግንባር ቀደም ተፎካካሪ መሆኑን ማስመስከር ችሏል:: አርሴናል እስከ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ድረስ በሊጉ የነበረው ቆይታ እጅግ የተረጋጋ እና በማሸነፍ ስነ ልቦና የታነጸ ነበር:: ቡድኑ በ33 ጨዋታዎች 70 ነጥቦችን ሰብስቧል፤ 63 ግቦችን ደግሞ ከተጋጣሚ መረብ ላይ አሳርፏል:: ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የኋላ ክፍሉ 26 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠረበት::

የሚኬል አርቴታው ቡድን በተለይም በመከላከሉ ረገድ ያሳየው ጥንካሬ እና በቆሙ ኳሶች (Set-pieces) ላይ የነበረው አስፈሪነት የቡድኑን የማሸነፍ አቅም በእጅጉ አሳድጎት እንደቆየ የኦፕታ አናሊስት መረጃ አስነብቧል:: ዴቪድ ራያ፣ ዲክላን ራይስ፣ ዊሊያም ሳሊባ እና ጋብርኤል ማጋሌስን የመሳሰሉ ተጫዋቾች በግልም ሆነ በቡድን ያሳዩት ብቃት አርሴናልን የዘንድሮው የዋንጫ ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ተስፋን ፈጥሮ ነበር:: ነገር ግን የውድድር ዘመኑ ወደ ወሳኙ ምዕራፍ ሚያዝያ ወር ሲሸጋገር አርሰናል ላይ ያልተጠበቁ ፈተናዎች መደቀን ጀመሩ:: በቅርቡ ከሜዳው ውጪ በ32ኛ ሳምንት በኤምሬትስ በበርንማውዝ የደረሰበት ያልተጠበቀ ለጓርዲዮላው ቡድን ትልቅ ተሰፋ ሰጥቷል::

በኢትሃድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያደረገውን ጨዋታ መሸነፉ ደግሞ ይበልጥ አርሴናልን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ከቶታል:: ይህ ሽንፈት አርሴናል ለረጅም ጊዜ ይዞት የነበረውን ሰፊ የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ነጥብ ብቻ እንዲጠብ አድርጎታል:: ማንቸስተር ሲቲ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየ ያለው አቋም የፔፕ ጓርዲዮላን ታክቲካዊ ልህቀት እና የቡድኑን የማይበገር ስነ ልቦና በድጋሚ ያረጋገጠ መሆኑን ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል:: ሲቲ የውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ መጠነኛ መዋዠቆች የታየበት ቢመስልም ቀስ በቀስ ግን ሞተሩን በማሞቅ ወደ ዋንጫው ፉክክር ተመልሷል:: የማንቸስተሩ ከተማ  ክለብ ከበርንሌይ ጋር የነበረውን ተስተካካይ ጨዋታ  በማሸነፍ መሪነቱን ተረክቧል::

በ32ኛ ሳምንት ማንቸስተር ሲቲ በአርሴናል ላይ የተቀዳጀው ወሳኝ ድል ቡድኑ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ  ምን ያህል አደገኛ፣ ርህራሄ የሌለው እና አሸናፊ መሆኑን በተግባር ያሳየበት አጋጣሚ መሆኑን ያሆ ስፖርት ዘግቧል:: እርሊንግ ሀላንድ፣ ኒኮ ኦሬሊ እና ሪያን ቸርኪ ሜዳ ላይ የሚያሳዩት የኳስ ቁጥጥር እና የፈጠራ ብቃት ቡድኑ በማንኛውም ጊዜ ጨዋታዎችን የመቀየር አቅም እንዲኖረው አድርጎታል:: አሁን ላይ ሲቲ የራሱን እድል በራሱ እጅ ላይ አስገብቷል፤ ተስተካካይ ጨዋታውን በማሸነፍ  ከአርሴናል ጋር በነጥብ እኩል  በመሆን የዋንጫውን ጉዞ አሳምሯል::

የአርሴናል ባለፉት ሦስት ተከታታይ የውድድር ዘመናት (2022/23፣ 2023/24 እና 2024/25 እ.አ.አ)  የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እጅግ ተቃርቦ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በተፈጠሩ ስህተቶች ዋንጫውን ለማንቸስተር ሲቲ እና ለሊቨርፑል አሳልፎ መስጠቱ አይዘነጋም:: በ2022/23 የውድድር ዘመን አርሴናል ለ248 ቀናት የሊጉን አናት ተቆጣጥሮ ቆይቶ በመጨረሻው ሰዓት ሚዜ ሆኖ ማጠናቀቁ አይዘነጋም:: የሰሜን ለንደኑ ክለብ በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ከእ.አ.አ ከ1999-2001 ወዲህ ሦስት ጊዜ በተከታታይ ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀ የመጀመሪያው ክለብ ነው:: ቡድኑ  ባለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት ዋንጫዎችን ያጣባቸው ምክንያቶች የልምድ ማነስ፣ በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ የሚታይ የትኩረት ማጣት፣ የስብስብ ጥልቀት ማነስ እና ቁልፍ ተጫዋቾች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ናቸው::

አርሰናል ከሌሎች ጠንካራ ቡድኖች (Big Six) ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በተለይም ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ነጥቦችን መጣሉ ለዋንጫ ማጣቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የቢቢሲ መረጃ አመልክቷል:: የዘንድሮው የውድድር ዘመንም የዚሁ መጥፎ ታሪክ ድግግሞሽ እንዳይሆን የክለቡ ደጋፊዎች በከፍተኛ ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ:: አርሴናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ 22 ዓመታት አልፈውታል:: ይህ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀ የዋንጫ ጥማት በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ጉጉትን ከመፍጠሩም ባሻገር ወደ አስፈሪ ጫና ተቀይሯል:: ደጋፊዎች ዋንጫውን ከመናፈቃቸው የተነሳ እያንዳንዱ ስህተት በስታዲየም ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤን እየፈጠረ ይገኛል፤ ይህ የደጋፊው ትዕግስት ማጣት እና እንዳለፈው ዓመት ዋንጫውን ልናጣው ነው የሚለው ፍርሃት የተጫዋቾችን በራስ መተማመን ሲሸረሽር ይስተዋላል:: እንደ ብዙዎች የእግር ኳስ ተንታኞች እምነት አርሰናልን ዋንጫ እያሳጣው ያለው የተጫዋቾች አቅም ማነስ ሳይሆን የስነ ልቦና ችግር  ነው::

ይህንን ስጋት ይበልጥ የሚያጎላው ደግሞ አርሴናል በየዓመቱ ሚያዝያ ወር ላይ የሚያሳየው ያልተለመደ የአቋም መውረድ ነው::  አርሴናል ሚያዝያ ሲመጣ ለምን ይደክማል? የሚኬል አርቴታ የአጨዋወት ፍልስፍና ከፍተኛ ጉልበትን እና ያለማቋረጥ ጫና መፍጠርን (High-intensity pressing) የሚጠይቅ ነው:: ይህ የአጨዋወት ዘይቤ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ እና አጋማሽ ላይ እጅግ ውጤታማ ቢሆንም ወደ መገባደጃው ሲደረስ ግን በተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ የአካል ብቃት መዳከምን ያስከትላል:: ሌላው የተጫዋቾች አጠቃቀም (Squad Rotation) ጉዳይ ነው:: ፔፕ ጓርዲዮላ ቁልፍ ተጫዋቾቹን በተለያዩ ጨዋታዎች በማሳረፍ ጉልበታቸውን ለሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ይቆጥባል::

አርቴታ ግን በአብዛኛው በተመሳሳይ የመጀመሪያ አሰላለፍ የመጠቀም ልማድ አለው:: ይህ ደግሞ ተጫዋቾቹ በሚያዝያ ወር የድካም ጣሪያ ላይ እንዲደርሱ ያደርጋቸዋል:: ሦስተኛው እና ትልቁ ምክንያት ደግሞ የስነ ልቦና ጫና ነው:: ሚያዝያ ወር የፕሪሚየር ሊጉ እጣ ፈንታ የሚወሰንበት፣ እያንዳንዱ ነጥብ የወርቅ ያህል የሚፈለግበት ወቅት ነው:: አርሰናል ባለፉት ዓመታት በዚህ ወር ላይ ያሳለፈው መጥፎ ትዝታ (Trauma) በተጫዋቾቹ አእምሮ ውስጥ አሁንም ድረስ አለ:: ትንሽ ስህተት በተፈጠረ ቁጥር “እንደገና ያምናው ታሪክ ሊደገም ነው” የሚለው ፍርሃት የተጫዋቾችን እግር አሳስሮ ይዟቸዋል ይላል የያሆ ስፖርት መረጃ:: ይህ ድብልቅልቅ ያለ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ድካም መድፈኞችን በሚያዝያ ወር ከባድ ዋጋ አስከፍሏቸዋል::

በተቃራኒው ማንቸስተር ሲቲ በሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ለምን ይበረታል? ማንቸስተር ሲቲ የውድድር ዘመኑ መገባደጃ ሲደርስ ወደ አስፈሪ ቡድን የመቀየር ልማድ አለው:: ይህ በአጋጣሚ የሚፈጠር ሳይሆን በጥንቃቄ የታቀደ የፔፕ ጓርዲዮላ የስፖርት ሳይንስ እና የታክቲክ ስትራቴጂ ውጤት ነው:: ጓርዲዮላ የውድድር ዘመኑን እንደ ማራቶን እንጂ እንደ አጭር ርቀት ሩጫ አይመለከተውም:: ቡድኑ ከነሐሴ እስከ ታህሳስ  ከፍተኛውን ነጥብ እንዲሰበስብ ቢፈልግም የተጫዋቾቹ ትክክለኛው የአካል ብቃት ጣሪያ ላይ የሚደርሰው ግን በፀደይ ወራት (በሚያዝያ እና ግንቦት) ነው::

የሲቲ የስብስብ ጥልቀት ማንኛውንም ተጫዋች በሌላ በተመሳሳይ ጥራት ባለው ተጫዋች ለመተካት የሚያስችል በመሆኑ ተጫዋቾች ሳይደክሙ እና ጉዳት ሳይገጥማቸው የውድድር ዘመኑን በድንቅ ብቃት ያጠናቅቃሉ:: ውኃ ሰማያዊ ለባሾች የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ያላቸው ተደጋጋሚ ልምድ ከፍተኛ ጫና ባለባቸው ጨዋታዎች ላይ እንዳይደናገጡ ይልቁንም በተረጋጋ መንፈስ ጨዋታውን እንዲቆጣጠሩ አድርጓቸዋል:: ለ2025/26 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ይበልጥ እድል ያለው የትኛው ክለብ ነው?  ምንም እንኳን አርሴናል አሁንም በ70 ነጥብ የሊጉን አናት እየመራ ቢሆንም የፔፕ ጓርዲዮላው ስብስብ በ67 ነጥብ እና በአንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከኋላው እያሳደደው ይገኛል:: አሁን ላይ የዋንጫው እጣ ፈንታ በቀጥታ በውድድር ዘመኑ ለስድስት ቀናት ብቻ በሊጉ አናት ላይ ላሳለፈው ማንቸስተር ሲቲ እጅ ላይ ወድቋል::

በዚህ ዓመት 265 ቀናትን በሊጉ አናት ላይ ያሳለፈው አርሴናል የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አሁን የራሱን ጨዋታዎች ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ማንቸስተር ሲቲ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ነጥብ እንዲጥል መጸለይ ግድ ይለዋል:: ነገር ግን የሲቲን ታሪክ ለሚያውቅ ይህ ቡድን በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ላይ ምን ያህል ርህራሄ እንደሌለው እና ነጥብ የማይጥል እንደሆነ በሚገባ ይታወቃል:: ከስነ ልቦናዊ የበላይነት፣ ከቡድን ስብስብ ጥልቀት፣ ከአሰልጣኙ የዋንጫ ልምድ እና ከወቅታዊ አቋም አንጻር ማንቸስተር ሲቲ የ2025/26 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት (በዐስር ዓመታት ውስጥ ለሰባተኛ ጊዜ) እጅግ ሰፊውን እድል እንደያዘ የፖሊማርኬት ግምት ያስረዳል:: ይህ ድረገጽ ለማንችስተር ሲቲ 57 በመቶ ግምት ሲሰጥ ለአርሴናል ደግሞ 43 በመቶ የዋንጫ ግምት ሰጥቶታል:: ኦፕታ አናሊሰት ግን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ለአርሴናል የሰጠው 73 በመቶ ግምት አሁንም አልቀነሰም::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here