“የበረሃዉ ወርቅ”

0
53

በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ረገድ ትልቅ አቅም ካላቸው የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ዕጣን እና ሙጫ ተጠቃሽ እንደሆኑ ከኢትዮጵያ ደን ልማት (Ethiopian Forestry Development) ድረ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዕጣን እና ሙጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የገበያ ተፈላጊነት ያላቸው እና “የበረሃ ወርቅ” በመባል የሚታወቁ  እና ዘርፈ ብዙ  ጠቀሜታ እንደሚሰጡ መረጃው አክሏል። በአማራ ክልል በ11 ዞኖች ውስጥ የሚገኘው ይህ ሀብት በአግባቡ ከተያዘ የክልሉን ምጣኔ ሀብት ዕድገት ወደ ፊት የሚያራምድ ነው።

ቄስ ፈንታ ሰጤ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ደለሎ ፋና ቀበሌ ነዋሪ ናቸዉ። ቄስ ፈንታ የመተማ እና የቋራ ወረዳዎች ዕጣን አምራች ማህበራት የቴዎድሮስ ዩኒየን ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። ዩኒየኑ ከመተማ 17  እንዲሁም ከቋራ 19 ማህበራትን አቅፎ ይዟል። ዩኒየኑ  ከሁለት ሺህ 500 በላይ አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ለበኵር በስልክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ በፊት በዘፈቀደ የተበታተነውን ዕጣን እና ሙጫ የማምረት ሥራ ዩኒየኑ ወደ አንድ በማምጣት ተገቢውን እውቅና በማስገኘት ዛፎች እንዲጠበቁ እና የሚመረተው ዕጣን እና ሙጫ ምርት በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ በር የከፈተ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም ደኑን በባለቤትነት ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እና ክትትል ለማድረግ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።

አመልድ ኢትዮጵያ እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርጉ እንደነበርም  ያስታወሱት ቄስ ፈንታ  በዚህ ዓመት ግን በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት መቋረጡን ተናግረዋል። ተቋሙ በዘመናዊ መንገድ ለማምረት የሚያስችሏቸውን  የመሳሪያ ድጋፍ ሲያደርጉላቸው እንደቆዩም አስረድተዋል። ነገር ግን ዩኒየኑ በተቻለ መጠን እነሱን ሙሉ በሙሉ ተክቶ ተግባራትን ማከናወን ባይችልም ደኖችን መልሶ ለመተካት እና ጥብቅ የሆነ ጥበቃ እና እንክብካቤ ለማድረግ በትኩረት ለመሥራት ማቀዱን ነው ያስረዱት።

ነባራዊ የክልሉ የፀጥታ ችግር እንደልብ ተንቀሳቅሶ የደን ልማቱን ለማስከበር እና ሕገ_ወጦችን ተከታትሎ ለመያዝ ክፍተቶች እንዳሉም አመላክተዋል። ሆኖም ግን ሕግ በተከበረባቸው አካባቢዎች ጥፋተኞች በሕግ እየተጠየቁ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ነው።

አሁን ላይ መጋዝን ተዘጋጅቶ ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን የተናገሩት ቄስ ፈንታ፤ በዋናነት የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚያዚያ እና ግንቦት ምርት የሚሰበሰብባቸው ወራቶች ናቸው። ባለፈው ዓመት አንድ ኩንታል ዕጣን እና ሙጫ በ53 ሺህ 500 ብር የተሸጠ ሲሆን በዚህ ዓመት ከ70 ሺህ ብር በላይ ይሸጣል የሚል ግምት አላቸው።

ዩኒየኑ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ያለው እና ግብር ከፋይ በመሆኑ ማንኛውም አካል በሚወጣው ጨረታ መሳተፍ እንደሚችል ጠቁመዋል። ዘርፉ ለአምራቹም ሆነ ለመንግሥት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል። “አንድ ኩንታል ሰሊጥ የሚሸጠው በ15 ሺህ ብር ነው፤ አንድ ኩንታል ሰሊጥ ለማምረት ብዙ ድካም እና ልፋት ይጠይቃል፤ አንድ ኩንታል እጣን እና ሙጫ አምርቶ 70 ሺህ እና ከዛ በላይ ለመሸጥ ግን የሚያስፈልገው ሦስት የዕጣን ዛፎችን በጥንቃቄ እና በእንክብካቤ መያዝ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል::

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ጽ/ቤት የደን ጥበቃ ባለሙያ አቶ መኳንንት ደረበ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት በዞኑ በደን ከተሸፈነው 759 ሺህ 281 ሄክታር መሬት ውስጥ 231 ሺህ ሄክታሩ  በዕጣን እና ሙጫ ዛፍ የተሸፈነ ነው። 170 ሺህ 654 ሄክታር መሬት ላይ የተሸፈነው ዛፍ እጣን እና ሙጫ እየለማበት ይገኛል። 138 ሺህ 433 ሄክታር ላይ የሚገኘው የዕጣን ዛፍ በባለሀብቶች፣ በማህበራት እና በኢንተርፕራይዞች አሳታፊ የደን አሥተዳደር ተመስርቶ ምርት እየተሰበሰበ ነው።

በዘርፉ 20 ማህበራት፣ 19 ባለሀብቶች፣ አንድ ተቋም እና አንድ ኢንተርፕራይዝ ውል እና ፈቃድ ወስደው ተሰማርተዋል።

ባለፈው ዓመት (2018 ዓ.ም) አራት ሺህ 49 ኩንታል እጣን እና ሙጫ ተመርቷል:: በዚህ ዓመት ደግሞ አምስት ሺህ 15 ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው::  የዘርፉ ዋነኛ ችግሮች ሕገ_ወጥ እርሻ (ሞፈር ዘመት እርሻ መስፋፋት)፣ ሰደድ እሳት፣ የደን ጭፍጨፋ መስፋፋት እና መሰል እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ ይጠቀሳል።

የምርምር ተቋማትም የምርምር ሥራውን በተገቢው መንገድ አከናውነዋል ማለት እንደማያስደፍር የቦርድ ሰብሳቢው ጠቁመዋል:: ዝርያውን ለማሻሻልም የተሄደበት ርቀትም ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለሆነም አሁን ያለውን እና ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የዕጣን ዛፍ ተንከባክቦ መያዝ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል::

ሕገ_ወጥ እንቅስቃሴዎች ዘርፉን በእጅጉ ፈትነውታል። በዚህም የደን ሽፋኑን እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል። አምራቾች የአካባቢ ሚሊሻ ቀጥረው ጥበቃ እስከማድረግ ደርሰዋል። ሕገ_ወጦች ላይ ንብረቱ እንዲወረስ፣ በገንዘብ እንዲቀጡ እና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በእስራት እንዲቀጡም ተደርጓል።

በአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ የደን ምርት ውጤቶች ክትትል እና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ድንቁ ሙሃቤ ከበኵር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት የዕጣን ሀብት በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው። ባለፈው ዓመት በክልሉ 9 ሺህ 750 ኩንታል ዕጣን እና ሙጫ ለማምረት ታቅዶ 9 ሺህ 525 ኩንታል ማምረት ተችሏል።

በተያዘው ዓመት (በ2018 ዓ.ም) ደግሞ 10 ሺህ 477 ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አራት ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ዕጣን እና ሙጫ ተመርቷል። በቀጣይ ሁለት ወራት ምርቱ በስፋት የሚሰበሰብበት ወር እንደሆነም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ገበያ የአንድ ኩንታል ዕጣን ዋጋ የጥራት ደረጃው ቢለያይም ከ70 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል። ከመንግሥት ገቢ አኳያም ከሚሸጠው ምርት ላይ 20 በመቶው ክፍያ ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል ብለዋል።

በኵር ጋዜጣ በሚያዝያ 30/2015 ዕትሟ “የእጣን እና ሙጫ ሀብቱ ተጠቃሚ እያደረጋቸዉ ነው“ በሚል ርእስ በወጣቶች አምድ ባወጣችው ዘገባ አንድ ኩንታል እጣን እስከ 23 ሺህ ብር ለገበያ መቅረቡን   አስነብባለች:: ምርቱ  ለአካባቢው ወጣቶችም ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ዘግባለች። በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችንም ጠቅሳ መፍትሄዎችንም አመላክታ ነበር::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በክልሉ የዕጣን ምርት በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

በሌላ በኩል በምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞኖች ከፍተኛ የዕጣን ሀብት ቢኖርም ሀብቱ በሚገኝባቸው ቆላማ እና በረሃማ አካባቢዎች ያለው የመሰረተ ልማት አለመስፋፋት፣ የፀጥታ ችግር እና የአካባቢው አቀማመጥ አመቺ አለመሆን በዘርፉ በቂ ባለሀብቶች እንዳይሰማሩ እንቅፋት ሆኗል። በዚህም ምክንያት በነዚህ አካባቢዎች ያለው ሀብት በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል።

ተቋሙ የዕጣን ሀብትን በተሻለ መንገድ ለማልማት አዳዲስ አሠራሮችን ለመተግበር በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ነው ያሉት። ለአብነትም ከዚህ ቀደም ለአንድ ዓመት ብቻ ይሰጥ የነበረው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወደ አምስት ዓመት እንዲያድግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።

ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ የዕጣን ዛፎች አያያዝ ነው። የዕጣን ዛፍ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ የተፈጥሮ ሀብት ነው። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ያለው የአመራረት ሂደት እጅግ ኋላቀር እና ዛፉን የሚያጠፋ ነው። ምርቱን ለመሰብሰብ ሲባል የዛፉ ግንድ በተደጋጋሚ (እስከ 12 እና 14 ጊዜ) በስለት ይተለተላል። በተጨማሪም ዛፉ ማረፍ ሲገባው ያለ እረፍት ይመረታል። የዕጣን አመራርቱ እንዴት እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚደማ እና የሚደማበት መጠን እና ጊዜ እንዲሁም እንዴት ተዘጋጅቶ ወደ ገበያ እንደሚገባ፣ ምን ዓይነት ቦታ መቀመጥ እንዳለበት፣ መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ሁሉ የግንዛቤ ፈጠራ እየተሰጠ ቢሆንም ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የደን ባለሙያው እንዳሳሰቡት ዘመናዊ የምርት አሰባሰብ ቴክኖሎጂን (ሳይንሳዊ የክትከት ጥልቀት እና እረፍት) ተግባራዊ ካልተደረገ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የዕጣን ዛፍን በታሪክ ብቻ የምናስታውሰው ይሆናል። በተጨማሪም በየጫካው የሚነሱ ሰደድ እሳቶች፣ የደን ምንጣሮዎች እና የእርሻ መስፋፋት ለሀብቱ መመናመን ሌላኛው ምክንያት ናቸው።

የዕጣን ሀብት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባለፈ ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር መስተካከል ትልቅ ድርሻ አለው። ይህን “የበረሃ ወርቅ” ከጥፋት ታድጎ ለትውልድ ማስተላለፍ እና ተገቢውን የኢኮኖሚ ጥቅም ማግኘት የሚቻለው መንግሥት፣ ባለሀብቶች፣ ተመራማሪዎች፣ አምራች ማህበራት እና የአካባቢው ማህበረሰብ በቅንጅት ሲሠሩ ብቻ መሆኑን ነው ያብራሩት።

መረጃ

የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ አዳዲስ የእርሻ መሬቶችን ለማስፋፋት ሲባል የዕጣን እና ሙጫ ዛፎች እየተጨፈጨፉ ይገኛሉ። እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ዘርፉን ማዳን የሚቻልባቸው ቁልፍ መፍትሔዎችም፦

  • መንግሥት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት የዕጣን እና ሙጫ ደኖችን በልዩ ሁኔታ እንዲጠበቁ ማድረግ።
  • የዛፎቹን ዕድሜ በማያሳጥር እና ጤንነታቸውን በጠበቀ መልኩ ምርቱን እንዴት መሰብሰብ እንደሚቻል በባህላዊ መንገድ ለሚሰበስቡት ሳይንሳዊ ሥልጠና መስጠት ይኖርበታል።
  • ምርቱን እሴት ሳይጨምሩ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ሀገር ውስጥ በማቀነባበር ለዓለም ገበያ ማቅረብ ቢቻል የውጭ ምንዛሬ ገቢውን ማሳደግ ይቻላል።
  • የሕገወጥ (የኮንትሮባንድ) ንግድን ለመግታት ጥብቅ የሆነ የሕግ ቁጥጥር ማድረግ እና አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለገበያ የሚያቀርቡበትን ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here