ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የዳኝነት ሥርዓት

0
55

“የባሕል ፍርድ ቤቶች አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ዛሬ ሳይሆን ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ባልነበረበት ወቅት ማሕበረሰቡ  ተቃርኖ፣ አለመግባባት…ሲገጥመው ለመፍታት ቀደም ባሉት ዓመታት  ነው” በማለት ስለባህል ፍርድ ቤቶች እና ሥርዓት የገለጹት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት  ኃላፊ አቶ ይማም ሰይድ ናቸው::

የባሕል ፍርድ ቤቶች እንደስያሜያቸው ከማሕበረሰቡ ባሕል እና እሴት የሚመነጩ እንዲሁም  ከባሕል የሚቀዱ ሕጎችን መሠረት አድርገው የዳኝነት ሥርዓቱን  የሚሠጡ ተቋማት እንደሆኑ  አቶ ይማም ጠቁመዋል::  የባሕል ፍርድ ቤቶች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜ ያሏቸው የሽምግልና  እና የባሕል ሥርዓት  ተግባራትን ሲከዉኑ የነበሩ ናቸው::

ኢትዮጵያ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓትን ከአውሮፓ ተቀብላ ሥታወጣ ግን በግልፅ ካልተደነገገ /ካልተፈቀደ/ በስተቀር የባሕል ፍርድ ቤቶችን መጠቀም እንደማይቻል በፍትሐብሔር ሕጉ ስለተቀመጠ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሕገ መንግሥቱ እስከ ፀደቀበት ጊዜ ድረስ በሕግ ተከልክለው የቆዩ ጉዳዮች ናቸው::

ሕገ መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም ሲወጣ ግን የግል እና ቤተሰባዊ ጉዳዮችን በሚመለከት በተከራካሪ እና በተሸማጋዮች ፈቃድ የተመሰረተ የባሕል ዳኝነት ሥርዓትን መከተል እንደሚቻል ተደንግጓል ፤ ይሁን እንጂ ዝርዝር አፈፃፀም ሕጉ እና አሠራራቸውን በሚመለከት ሌላ ሕግ እንደሚወጣለት ቢወሰንም ላለፉት 30 ዓመታት እነዚህ ሕጎች ሳይወጡ ቆይተዋል::

የአማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤቱ  ኃላፊ አቶ ይማም እንደሚገልፁት የአማራ ክልል ይህንን የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት የማክበር እንዲሁም የማሕበረሰቡን ባሕል እና እሴት የመጠበቅ ግዴታ እና ኃላፊነት ስላለበት እሱን ለማረጋገጥ  የባሕል ፍርድ ቤቶች ቀለል ያለ ሥርዓትን የሚጠቀሙ፣  እንዲሁም እዛው ማህበረሰቡ ደጅ ድረስ የሚካሄዱ በመሆኑ ጊዜ እና ወጭ ቆጣቢ፣ በእርቅ ቀድሞ የነበረውን ሰላም ወደ ማህበረሰቡ መመለስ የሚያስችሉ ናቸው::  ይህ ደግሞ  ከመደበኛው የፍሕ ሥርዓት ላይ የሌለ (የጎደለ) ስለሆነ ይህንን ዓላማ መሠረት አድርጎ የባሕል ፍርድ ቤቶችን በአዋጅ ቁጥር 298/2017 እውቅና መስጫ አዋጅ እንዲወጣ ተደርጓል::

የባሕል ፍርድ ቤቶች መስጫ አዋጁ እና ከዛ በኋላ የወጣው መመሪያ ቁጥር 23/2018 እንደሚያመለክተው የግለሰብ እና የቤተሰብ ጉዳዮችን  በግለሰቦች ፈቃድ ላይ ተመስርተው እንዲያዩ ነው:: የባሕል ፍርድ ቤቶች በፍትሐብሄር ጉዳዮች ላይ ደግሞ ያልተገደበ ሥልጣን አላቸው፣ ይህም በተከራካሪዎች መልካም ፈቃድ ይሆናል:: የወንጀል ጉዳዮች ደግሞ በግለሰብ አቤቱታ አቅራቢነት የሚቀርቡ፣ ትንንሽ ወንጀሎችን፣ በሌሎች ሕጎች በባሕላዊ ፍርድ ቤት በግልፅ እንዲታዩ የተፈቀዱ ጉዳዮችን፣ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ”እነዚህ ጉዳዮች በባሕል ፍርድ ቤት ቢታዩ ውጤታማ ይሆናሉ፤ /ይበልጥ የማህበረሰቡን ሰላም ያጠናክራሉ/” ብለው በማሰብ ወደ ባሕል ፍርድቤት የሚመሯቸው ጉዳዮች፣ በመንግሥት ክስ የሚያስቀጡ ጉዳዮችን በሚመለከት ደግሞ ጉዳዩን እልባት መስጠት ሳይሆን ለምሳሌ – ግድያ ቢሆን ብይን መስጠት ሳይሆን ቤተሰቦችን በማስማማት እና የካሳ ጉዳዮችን ብቻ ያያሉ::

የጽ/ቤት ኃላፊው እንዳብራሩት በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዋጁ ሳይወጣ እና ከወጣ በኋላ በተደረገ ጥልቅ ጥናት ሽምግልናን ጨምሮ 15  የባሕል የዳኝነት ሥርዓቶች አሉ:: ከነዚህ መካከል  ዘወልድ ፣አበጋር፣ ረከቦት፣ አማሪ ቁና ፣ የሰገድ፣ መዛርጥ ፣ ክፍሎ ፣ አውሳጥ ፣ ዙፋን አውራጅ፣   ስምንቱ ማይ ቤት፣  ሰባቱ ከዘራ… የሚባሉት ተጠቃሽ ናቸው:: እነዚህ የባሕል ፍርድ ቤቶች በተያዘው ዓመት ታህሳስ 21 እና 22/2018 ዓ.ም  በክልል አቀፍ ደረጃ የሕግ እውቅና ተሰጥቷቸዋል::

አሁን ባለው አደረጃጀት አራት ሺህ 176 ቀበሌዎች አሉ፤ በሁሉም ቦታዎች ላይ የባሕል ፍርድ ቤቶች እንደ ሚኖሩ ኃላፊው ጠቁመዋል:: ሽምግልና ደግሞ ድርጊቱ ከተከሰተ በኋላ ስለሚሰበሰብ  እነዛን መምረጥ ይጠይቃል:: በአንድ ሺህ 148 ቀበሌ ላይ የሽማግሌ ምርጫ ተከናውኗል::  ዋናው መርህ ተደራሽነትን ማጠናከር ስለሆነ ማህበረሰቡ ወጭው ሳይበዛ ጊዜውን ቆጥቦ በሚያውቃቸው ሽማሌዎች እና በሚያውቀው ሥርዓት ዳኝነት  ያገኛል:: አዋጁ  ይግባኝ ከሌላቸው የግድ አይጠየቁም ፣ ድሮ ከነበራቸው ሥርዓት የሚጨመር ምንንም አዲስ ነገር አይኖርም::

ለባሕል ፍርድ ቤቶች መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግባቸው ክፍተቶች  መኖራቸውን አቶ ይማም ጠቁመዋል:: የባሕል ፍርድ ቤቶች /ሽምግልና ሥርዓት/ ላይ ያለው  ችግር  የጽሑፍ /የተጻፈ/ መረጃ አለመኖሩ  የሚሰጠውን ውሳኔ ጠንካራ እና ደካማ ጎን በጥልቀት ለማየት አያስችልም:: በተለይም የሰብዓዊ መብቶች ፣የሴቶች  እና ሕፃናት ፣ድጋፍ የሚሹ እና ለአደጋ ተጋላጭ የኅብረተሰቡ ክፍሎችን  እኩል የመሰማት መብት ፣ በአድልኦ ላለመሥራት  በሥልጠና ማገዝ እንዳለበት ጠቁመዋል::

የባህል ፍርድ ቤቶች አሠራር ”ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የዳኝነት ሥርዓት” ስለሚከተል   ሕገ መንግሥቱ ፈቃዳቸውን ያረጋግጣል:: ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ አፈፃጸም ላይ የወሰኑትን ጉዳይ ለማስፈጸም ይታገላሉ፤ ነገር ግን ይህንን የሚፈጽም አካል ባለመኖሩ አፈጻጸሙ ችግር ላይ ነበር:: በቀጣይ የሰጡትን ውሳኔ ወደ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲልኩ እንደ ራሱ ውሳኔ በመውሰድ እንዲያስፈፅም ይደረጋል::

ፍትሕ ፈላጊዎች (ባለጉዳዮቹ) አንድ ጊዜ ፈቃድ ከሰጡ በኋላ በፈለጉ ጊዜ አቋርጠው የሚወጡበት ሂደት ነበር፤ ፈቅዶ ከገተባ በኋላ ግን በተፈለገ ጊዜ ሽምግልና ረግጦ መውጣት እንደማይቻል ጠቁመዋል:: ጸሐፊ እና መረጃ(ዶክመንት) ካለ የግድ ጽ/ቤት ያስፈልጋል:: ለዚህም ቀበሌ ማዕከላትን መገንባት ፣ለጽሑፍ የሚሆኑ ቁሳቁስ የማሟላት ሥራ ይሠራል::

እንደ ኃላፊው ገለጻ ክልሉ በርካታ የተለያዩ የባህል ሥርዓቶች ያሉት በመሆኑ በዓመት አንዴ የሽምግልና እና የባሕል ፍትሕ ሥርዓት (የባሕል ፍርድ ቤት) የሚፈፅሙ አካላት የገጠማቸውን ችግር የሚያወሩበት ጉባኤ ይዘጋጃል::  በጉባኤውም የልምድ ልውውጥ ያካሂዳሉ:: ችግር የፈቱ ሽምግልና /ሥርዓቶች/ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆኑ እና እንዴት ችግር እንደሚፈቱ በጽሑፎች ተሰናድተውም  ለዓለም ይተዋወቃሉ:: የቀበሌ እና ዞን መስተዳደሮች፣ ባህል እና ቱሪዝም፣ ሴቶች ጉዳይ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አስፈላጊውን  ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል:: የባሕል ፍርድ ቤቶች ቀድመውም፤ አሁንም ሥራቸውን እየሠሩ ሥለሆነ አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገ የበለጠ ይጠናከራሉ::

በአማራ ክልል ካለው ማህበረሰብ 80 ከመቶው ከዘመናዊ ፍትሕ ሥርዓት ይልቅ በባሕላዊ የፍትሕ ሂደት የመዳኘት ፍላጎት እንዳለው በሀገር አቀፍ ጥናት መታየቱን ያነሱት አቶ ይማም፤ ይህ የሆነው የባሕል ፍርድ ቤቶች እውነትና ፍትሕን የማረጋገጥ አቅም ስላላቸው ነው:: ይህም ሲባል በመደበኛ ፍርድ ቤት ማስረጃ የሌላቸው በድብቅ የተደረጉ ጉዳዮችን ማገዝ የማይችል ሲሆን በባሕል ግን በቃለ ማሀላ ፣በአባቶች የማጣራት ሂደት እና ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማረጋገጥ እውነት እና ፍትሕ እንዲረጋገጥ ያደረጋል::

የባሕል ፍትሕ ሥርዓት (የባሕል ፍርድ ቤት) ተጎጅና ጎጅ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉትን የማህበረሰብ  ክፍሎች  እናት፣ አባት፣ አክስት ፣አጎት… ቤተሰብ አባል ሁሉ የእርቁ አካል እንዲሆን በማድረግ ያስማማል:: ለዚህም ሥርዓቱ ከቤት መውሰድ ብቻ ሳይሆን ወደ ቤት ይመልሳሉ:: ጉዳዮች ሁሉ  እንዳመጣጣቸው የሚፈታበት የራሱ ሂደት አላቸው:: መደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን የመዝገብ ብዛት በመቀነስ ረገድም የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል:: ይህ እንዲሳካ ደግሞ የትኛውም የማኅብረሰብ ክፍል የመደገፍ ግዴታ እንዳለበት የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ይማም አሳስበዋል::

መረጃ

የባሕል ፍርድ ቤቶች የማይጣሱ መርሆዎች

  1. ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣
  2. ፍትሕን ማረጋገጥ(የፍትሕ በር ለሁሉም ክፍት ናት)፣
  3. ባሕል ላይ ጉዳት ያለማድረስ መርህ፣
  4. የሰብአዊ መብት ማክበር እና ማስከበር መርህ፣
  5. የሴቶች እና የሕፃናት መብትና እኩልነት የማረጋገጥ መርህ፣
  6. የሚወሰኑ ውሳኔዎች ሰብአዊ ጭካኔ ያልተሞላባቸው እና አዋራጅ እንዳይሆኑ የማድረግ መርህ፣
  7. በየተትኛውም ሁኔታ ቢሆን እነዚህን መርሆዎች መከበር እንዳለባቸው ማረጋገጥ፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here