ዓለም አቀፉ አሰላለፍ ወደ የት እያመራ ነው?

0
50

ዓለም ዛሬ በኃያላን መካከል የሚካሄድ የውድድር እና የፉክክር መድረክ ሆኗል። የኃያላኑን ጎራ ለመቀላቀል ጫፍ የደረሱ ሃገራትን ጨምሮ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ ዓለምን የሚዘውሩ ናቸው። ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ እና ወታደራዊ ኃይል ደግሞ ዋነኛ የኃያልነታቸው ማረጋገጫ በማድረግ ነው ላይ እየተወዳደሩ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ደግሞ ለጋራ ጥቅም ይተባበራሉ። ይህ የኃያላን አሰላለፍ ሀገራት እንዴት እንደሚቀራረቡ ወይም የጎሪጥ እንደሚተያዩ አመላካች ነዉ።

ለዚህ ደግሞ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀምሮ ዛሬም ድረስ የሚለዋወጡ አሰላለፎች ማሳያዎች ናቸው። አሰላለፎቹም ታዲያ ‘ቋሚ ወዳጅ ወይም ቋሚ ጠላት የለም’ የሚለውን ሃገርኛ ብሂል የሚያረጋግጡ ናቸው።

የኃይል አሰላለፍ ጅማሮ

የዓለምን ታሪክ ትኩረቱን አድርጎ መረጃዎችን የሚያጋራው ዎርልድ ሂስትሪ (www.worldpoliticsreview.com) ለአንደኛው የዓለም ጦርነት (እ.አ.አ ከ1914 – 1918) መንስኤ በአውሮፓ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ግጭት፣ የኃይል ውድድር እና የሃገራት የኃይል አሰላለፍ ወይም ትብብር (alliances) ነበር። ጦርነቱም ዓለምን በሁለት ጎራ ተከፍሎ ነው የሚሎዮኖችን ነብስ የበላው።

አንደኛው ጎራ ማዕከላዊ ኃይሎች (Central Alliance) ሲሆን በዋናነት ጀርመንን፣ ኦስትሮ – ሃንጋሪን እንዲሁም ኦቶማን እምፓየርን ያካተተ ነበር። ሁለተኛው ጎራ ደግሞ የትብብር ኃይሎች (United Alliance) የሚባለው ነው። ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ ዋና ተዋናይ ናቸው። ግጭቱም ታዲያ አድማሱን አስፍቶ ዓለም አቀፋዊ ገጽታን ይዟል።

በዚህ ወቅት ሁሉም የዓለም ሃገራት ጎራዎቹን አልተቀላቀሉም ነበር። የተወሰኑት የአሰላለፉን የአሸናፊነት ሚዛን በመጠበቅ ዝምታን መርጠው ነበር። አሜሪካ ደግሞ አንደኛዋ ስትሆን የተሻለ የኃይል ሚዛን ወደነበረው የትብብር ኃይሎች ተቀላቅላለች። ጦርነቱም በእነ አሜሪካ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። በአንጻሩ ጀርመን ክፉኛ ነበር የተጎዳችው።

በተመሳሳይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም (እ.አ.አ ከ1939 – 1945) ዓለምን በሁለት አሰላለፎች የከፈለ ነበር። ለጦርነቱ መነሳት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ጀርመን ፖላንድን መውረሯ ነው።

ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን በአንድ ጎራ፣ ብሪታንያ፣ ሶቪየት ኅብረት፣ አሜሪካ እና ፈረንሳይ ደግሞ በሌላኛው ጎራ የተሰለፉበት ነበር። ጦርነቱም በአሰላለፉ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ሀገራት በተመሳሳይ ወቅት ያስኬዱት አልነበረም። የተወሰኑ ሀገራት የኃይል ሚዛኑን መጠበቅ ምርጫቸው እንደነበር ነው የመረጃ ምንጩ ያብራራው። ምክንያቱ ደግሞ ሀገራት ቋሚ ወዳጅም ጠላትም እንደሌላቸው ይልቁንም ብሔራዊ ጥቅማቸውን መሠረት እድርገው አሰላለፋቸውን እንደሚወስኑ ነው የሚያመላክተው።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መዘዙ አሁንም ድረስ የቀጠለውን በጃፓኖቹ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ የዘነበውን የኒውክሌር ቦንብ አስከተለ። የዓለም አሰላለፍም ተቀየረ። በአሜሪካና ሶቪየት ኅብረት የሚመራ የኃያላን አሰላለፍም ፈጠረ። ይህን ተከትሎም ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የተጀመረ ሲሆን መሰል ችግሮች እንዳይደገሙ በሚል የዓለም ድርጅት (United Nations) እንዲቋቋም ምክንያት ስለመሆኑ የመረጃ ምንጩ አስነብቧል።

እንዲህ እያለ የቀጠለው የኃያላኑ አሰላለፍ በአሁኑ ወቅትም ዓለማችንን ሰላም እንዲርቃት ካደረገ ውሎ አድሯል። የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት፣ የታይዋን ጉዳይ፣ አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት፣ ኃያላኑ በአፍሪካ ወደቦች ላይ የበላይነታቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉት ፉክክር እና መሰል ክስተቶች ደግሞ የአሰላለፉ ዋና መገለጫዎች መሆናቸው ቢቢሲ አስነብቧል።

የወቅቱ አሰላለፍ

ምዕራባዊያንን የያዘው በአሜሪካ የበላይነት የሚዘወረው ትብብር በአሁኑ ወቅት የበላይነቱን ሚዛን ይዟል። አሜሪካም የዓለማችን ልዕለ ኃያል ሀገር በመሆን የዓለምን ፖለቲካ ትዘውራለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ሩሲያ እና ቻይና እንዲሁም በዙሪያቸው ያሉ ሀገራት የአሜሪካን ልዕለ ኃያልነት ለመገዳደር አለፍ ሲልም የኃያልነቱን መንበር ለመረከብ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሱ እንደሚገኙ ወርልድ ፖሊቲክስ ሪቪው (www.worldpoliticsreview.com) አስነብቧል። አሁናዊውን የዓለም አሰላለፍም እንደሚከተለው ነው ያስቀመጠው።

በአሜሪካ ዘዋሪነት እስራኤልን፣ እንግሊዝን፣ ጀርመንን፣ ፈረንሳይን፣ ደቡብ ኮሪያን እና ጃፓንን ያካተተው የመጀመሪያው አሰላለፍ ሲሆን ይህም የምዕራባዊያን ጎራ የሚባለው ነው። ጠንካራ የሚባለው እና ትብብር መሠረታዊ መገለጫው የሆነው አሰላለፉ አሁናዊውን የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ይዘውራል።

የአንዱ መጠቃት የሌላው መጠቃት ተደርጎ መታየቱም የአሰላለፉ መገለጫ ነው። ምዕራባዊያን ያቋቋሙት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ደግሞ የዚህ ማሳያ ነው።

ኢራን፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፓኪስታን እና ሰሜን ኮሪያን በዋና አጋርነት ያካተተው ደግሞ ሌላው አሰላለፍ ነው። በዋናነትም የምዕራቡን ዓለም ተፅዕኖ ለመቋቋም ወደ አንድነት የመጡ ሃገራት የተሰባሰቡበት ነው።

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና  ደቡብ አፍሪካ በጋራ ያቋቋሙት  ድርጅት (ብሪክስ) የዓለምን የኃይል ሚዛን በአዲስ ለመቅረጽ በሚል ወደ ትብብር ማዕቀፍ እንደመጡ ዎርልድ ፖሊቲክስ ሪቪው አስነብቧል።

በሌላ በኩል በርካታ ሀገራት ደግሞ ከሁለቱም አሰላለፍ በይፋ ባይቀላቀሉም የሌሎችን የአሰላለፍ ሚዛን ይከታተላሉ። ብዙዎቹ ሀገራት በሁሉም መስክ ራሳቸውን ያልቻሉና የበለጸጉ ሀገራትን እጅ የሚጠበቁ ናቸው።

ሰሞነኛው ክስተት

የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ለዘመናት የቆየውን አሰላለፍ በግልጽ ያሳዬ መሆኑን ትኩረቱን የዓለም ፖለቲካ ላይ ያደረገው ፖሊቲኮ (www.politico.com) የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ያብራራል። ምዕራባዊያን በሩሲያ ላይ በዓለም ታይቶ የማያውቀውን የማዕቀብ መዓት በሩሲያ ላይ እንዲጥሉ ያስገደደ ክስተት ነው። በሌላ በኩል ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና እና መሰል ሃገራት ደግሞ ለሩሲያ አጋርነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞነኛው የመካከለኛው ምሥራቅ ትኩሳት ግን አዳዲስ አሰላለፎችን ይዞ ነው የመጣው። የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ እንዳመላከተው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የጀመሩትን ጦርነት ተከትሎ አራን በባሕረ ሰላጤው (አረብ) ሃገራት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝራለች። ከሃገራቱ ጋርም ይበልጥ ሆድ እና ጀርባ ሆናለች።

የዓለማችንን የነዳጅ አቅርቦት 20 በመቶ ያህሉን ድርሻ ያለው የሆርሙዝ ሰርጥ በኢራን እንዲዘጋ መሆኑን ተከትሎ ተጽዕኖው መላውን ዓለም አዳርሷል። ክስተቱም ወዳጅ ሃገራትን ሳይቀር ፊት አዟዙሯል። በተለይ አሜሪካ ጋር ከምዕራባዊያን (በተለይ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ) የጎሪጥ እንደሚተያይ ባላንጣ ያልተገቡ ቃላትን አወራውሯል። ለአብነትም እንግሊዝ ድጋፍ እንድታደርግ በአሜሪካ በኩል የቀረበላትን ጥሪ “ምን አገባኝ” ማለቷ የሀገራቱን የቆዬ ወዳጅነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል። ይህን ተከትሎ ታዲያ የእንግሊዙ ንጉሥ ንግሥቷን አስከትለው ወደ አሜሪካ አቅንተዋል። ይህም በሀገራቱ መካከል ከሰሞኑ የታየውን ትኩሳት ለማርገብ ያስችላል ነው የተባለው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ60 በላይ የምሥረታ የዕድሜ ዘመን ያለው የነዳጅ አቅራቢ ሃገራት ማሕበር ኦፔክ (OPEC & OPEC+) ፈተና ተጋርጦበታል። ምክንያቱ ደግሞ ሰሞነኛው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው። የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ (UAE) ከድርጅቱ እንደምትወጣ በይፋ አስታውቃለች። አልጀዚራ እንደዘገበው ሃገሪቱ ከማሕበሩ ለመውጣት የወሰነችው ለነዳጅ ግብይቷ የተሻለ ገበያን ለማፈላለግ ነው። ክስተቱም በአረብ ሃገራቱ መካከል አዲስ አሰላለፍን ሊያስከትል እንደሚችል እየተነገረ ነው።

የኢራን እና የሩሲያ ግንኙነት መጠናከር ደግሞ ከሰሞነኛ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው፤ ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የፖለቲካና የወታደራዊ አሰላለፍ ሊቀይር ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢራን ከቻይና ጋር ግንኙነቷን እንደምታጠናክር ይጠበቃል፤ የኢራን ነዳጅ 90 በመቶ መዳረሻ ቻይና መሆኗን ልብ ይሏል።

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የጀመሩትን ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ ከመካከለኛው ምሥራቅ ድንበር አልፎ በመላው ዓለም ላይ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣ የታሪክ ክስተት ይሆናል እየተባለ ነው። ቀጣናውን ብቻ ሳይሆን የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት መሠረት የሚንድ ወይም ዳግም የሚቀርጽ ግዙፍ አንድምታ እንደሚኖረው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ (አፍሌክስ) ፕሬዝደንት ዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል። ከአካዳሚው ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነት ቀጣናውን ወደማይታወቅ አዲስ ምዕራፍ ሊያሸጋግረው ይችላል።

አቶ ዛዲግ እንዳብራሩት የኢራን ወታደራዊ አቅም ከተዳከመ ለዘመናት የዘለቀው የሺዓ እና የሱኒ የኃይል ፉክክር አዲስ መልክ ሊይዝ ይችላል፤ ይህም ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቀጣናው ላይ ያላቸውን የበላይነት እንዲያጠናክሩ ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢራን የሚደገፉት እንደ ሂዝቦላህ፣ ሃማስ እና ሁቲዎች ያሉ አባላት የገንዘብና የወታደራዊ ድጋፍ ምንጫቸውን ሊያጡ ስለሚችሉ፣ በሊባኖስ፣ በየመን እና በሶሪያ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር መንገድ ይከፍታል። እስራኤልም ትልቁን ስትራቴጂያዊ ጠላቷን በማዳከም በቀጣናው ያላትን ወታደራዊ የበላይነት ታረጋግጣለች፤ ይህም ከአረብ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ሊያፋጥነው ይችላል።

በሌላ በኩል ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኃያላን ሀገራት መካከል ያለውን ፉክክር (Great Power Rivalry) ይበልጥ ሊያሻክረው ይችላል። ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ወቅት ከኢራን ያገኘችውን ድጋፍ ለማካካስና አሜሪካን ለመገዳደር ለቴህራን የላቁ የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን ልትሰጥ ትችላለች፤ ይህም የሞስኮን እና የዋሺንግተን ግንኙነት ወደ ቀዝቃዛ ጦርነት ደረጃ ያሸጋግረዋል። ቻይና ደግሞ የነዳጅ ፍላጎቷንና የኢንቨስትመንት ጥቅሟን ለመጠበቅ ስትል ጦርነቱን በማውገዝ የሰላም አደራዳሪ ሆና ለመቅረብ ትሞክራለች። አውሮፓውያን ደግሞ በስደት ማዕበል እና በነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት ስጋት ውስጥ ስለሚገቡ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው የፖሊሲ አንድነት ሊላላ ይችላል።

አቶ ዛዲግ አክለውም ጦርነቱ ወደፊት ሊተነበዩ የማይችሉ መዘዞችን (Future Consequences) ይዞ ሊመጣ እንደሚችልም ነው የገለጹት። የኒውክሌር መስፋፋት ስጋት አንዱ ሲሆን “ኒውክሌር የሌለው ይጠቃል” የሚል ትምህርት የወሰዱ ሌሎች ሃገራት የራሳቸውን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲያበለጽጉ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።

የሃገራት የአሰላለፍ ለውጥ ገፊ ምክንያቶች ከላይ እንደተብራራው ዘርፈ ብዙ ናቸው። ጠቅለል ብሎ ሲገለጽ ደግሞ ብሔራዊ ጥቅማቸው ነው። ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ የሚያደርጉት ወቀወቱን የዋጀ አሰላለፍ ደግሞ ቋሚ ወዳጅም ጠላትም እንደሌለ ያመላክታል።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here