አፈርን በወቅቱ በማከም ምርታማነትን  እናሳድግ!

0
6

የአፈር አሲዳማነት በሀገራችን በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ የሚገኝ የአፈር ለምነት ችግር ሲሆን ለችግሩ በመንስኤነት ከሚጠቀሱት መካከል በዋናነት   የዝናብ መብዛት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የሰብል ተረፈ-ምርትን ሙሉ በሙሉ ከማሳ ማንሳት፣  ፍግ /የተፈጥሮ ማዳበሪያ/ አለመጠቀም ተጠቃሾች ናቸው።

ከነዚህ በተጨማሪም  ለረዥም ዓመታት መሬቱ ካለማፈራረቅ መታረሱ፣ በተደጋጋሚ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያን ከመጠን በላይ መጠቀም፣ የአፈር እና የውኃ ጥበቃ ሥራ በተገቢው መንገድ  አለመሠራቱ፣ መሬትን በአግባቡ አለመጠበቅ፣ የተፈጥሮ  ማዳበሪያን በትኩረት አለመጠቀም፣  የመሬት ጥበቃ ሥራ አለመሠራት አፈር በአሲድ እንዲጠቃ ዋነኛ  ምክንያቶች  ናቸው።

የአፈር አሲዳማነት በረዥም ጊዜ የተፈጥሮ መዛባት ሂደት ውስጥ የሚከሰት ሲሆን  አንዴ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ መፍትሔ በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ወጪ እና ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነውና ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢ  ነው፡፡

የአፈር  አሲዳማነት በአንድ ጊዜ በተወሰነ መጠን ተከስቶ የሚቆይ ሳይሆን በሂደት እየጨመረ እና እየተስፋፋ የሚሄድ በመሆኑ ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙና በምርታማነታቸው ሳይቀር የተሻሉ  የሀገሪቱን አካባቢዎችን ሳይቀር  ጭምር እየጎዳ መሬቱንም ከምርት ውጪ እያደረገው በመሆኑ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል።

ለግብርና ሥራ ትልቅ ግብዓት በሆነው አፈር ላይ የሚያጋጥመው አሲዳማነት በምርታማነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ፣ የአሲዳማነት ሽፋኑንም  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ  በመምጣቱ አፋጣኝ መፍትሄ እና ትኩረት መስጠትን ግድ ይላል።

የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከልም   የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም፣ በኖራ ማከም፣ የአፈር አሲዳማነትን ሊቋቋሙ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን እንደ አኩሪ አተር፣ ካሳቫ፣ አናናስ፣ ዳጉሳ፣ ቡና፣ ሻይ ቅጠል እንዲሁም የስንዴ ዝርያዎችን በማሳ ላይ በማፈራረቅ መዝራት አዋጭ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያወች ጠቁመዋል። የአፈር አሲዳማነት ጉዳይ መፍትሔ ካልተሰጠው ምርታማነትን ከ50 በመቶ እስከ 100 በመቶ ሊያሳጣ እንደሚችል ነገር ግን አርሶ አደሩ አንድ ጊዜ መሬቱን በኖራ ማከም ከቻለ እስከ አምስት ዓመት ሊያገለግለው እንደሚችል ባለሙያዎች ጠቁመዋል። በመሆኑም ከጅምሩ አፈሩ ከመጎዳቱ በፊት ጥንቃቄ እና እንክብካቤ ማድረግ፣ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ አሲዳማ አፈሩን በማከም ጥሩ ምርት ማግኘት ስለሚቻል  የአሲዳማ አፈርን ማከም ተግባር ላይ ከባለሙያዎች በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ አካላት  ትብብር ሊያደርጉ ይገባል- ውጤቱ ለሁሉም ነውና።

በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ዳይሬክተር እና  የአፈር ለምነት ተመራማሪ ተስፋዬ ፈይሳ (ዶ.ር) እንደጠቆሙት የአፈር አሲዳማነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዜጎችን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ የጣለ፣ በዓለም ኢኮኖሚ ላይም እስከ 40 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ እያስከተለ የሚገኝ ዝምተኛ ጠላት ነውና  የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል።

የአፈር አሲዳማነት  በአሁኑ ወቅት ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ አርሶ አደሮች ከአምራችነታቸዉ እያራቁ በመሆኑ ለመፍትሄዉ ሁላችንም እንበርታ።

በኲር የሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here