‘‘ፈጠራን ማክበር ሀገርን ማክበር ነው’’

0
170

በሀገራችን የፈጠራ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና የፈጣሪዎች መብት እንዲከበር የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በሀገራችን የፈጠራ ሥራዎች፣ የንግድ ምልክቶች እና የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ምን እንደሚመስል እና የመብት ጥሰት ሲደረግ የሚ ወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ  ኃላፊ ከሆኑት አቶ ስሜነህ አንተነህ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!!!

 

በመጀመሪያ ለዚህ ቃለ-መጠይቅ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!  ራስዎን በማስተዋወቅና ወደዚህ የሙያ ዘርፍ እንዴት እንደገቡ በመግለጽ ውይይታችንን እንጀምር?

ስለዚህ ጉዳይ ግንዛቤ ለመፍጠር ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ እኔም አመሰግናለሁ። ስሜነህ አንተነህ እባላለሁ፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ኃላፊ ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ። በዚህ ተቋም ውስጥ ለበርካታ ዓመታት አገልግያለሁ፤ ጉዞዬን በቅጅ መብት ባለሙያነት ጀምሬ አሁን በኃላፊነት ደረጃ ላይ እገኛለሁ። ወደዚህ ዘርፍ ከመምጣቴ በፊት በባህልና ቱሪዝም ቢሮ በሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያነት እንዲሁም በቋንቋ መምህርነት ሠርቻለሁ። የትምህርት ዝግጅቴን በተመለከተ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ያገኘሁ ሲሆን አሁን በምመራው ዘርፍ ደግሞ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ሕግ የማስተርስ ዲግሪዬን ከቻይና ሻንሃይ ቶንግጂ ዩኒቨርሲቲ አግኝቻለሁ።  የዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀንን ጨምሮ የዓለማቀፍ የመፃሕፍት ቀን እና የኮፒ ራይት ቀን በሚከበርበት ሚያዝያ ወር ውስጥ ይህን ቃለ ምልልስ ማድረጋችን ወቅታዊና አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።

 

የዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀንን (World IP Day) በተመለከተ አጠር ያለ ሐሳብ ቢሰጡን?

የዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀን በየዓመቱ ሚያዝያ 18 (April 26) በመላው ዓለም ይከበራል። የዘንድሮው የዓለም አእምሯዊ ንብረት ቀን “አእምሯዊ ንብረትና ስፖርት፣ መዘጋጀት፣ መጀመር፣ መፍጠር” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን የመጀመሪያ በሆነውና በቅርቡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተመረቀው አዲስ ስፖርት ፓርክ በስፖርታዊ ውድድሮች እና በፓናል ውይይት ተከብሯል።

 

“አእምሯዊ ንብረት” የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ለብዙዎች አዲስ ሊሆን ይችላል፤ ለመሆኑ አእምሯዊ ንብረት ምንድነው? ከሌሎች የንብረት ዓይነቶችስ በምን ይለያል?

መሠረታዊ ጥያቄ ነው። አእምሯዊ ንብረት (Intellectual Property) የምንለው የሰው ልጅ አእምሮውን ተጠቅሞ ያመነጫቸው የፈጠራ ውጤቶች ማለት ነው።

አእምሯዊ ንብረት መብት (IP Right) ደግሞ እነዚህ አእምሯዊ ውጤቶች ለተወሰነ ጊዜ የሕግ ጥበቃ እንዲያገኙ የሚሰጥ ልዩ መብት ነው። ይህ መብት ለፈጣሪው ወይም ለባለቤቱ “የብቸኝነት መብት” (Exclusive Right) ይሰጠዋል። ይህም ማለት ፈጣሪው ሥራውን ሌሎች እንዲጠቀሙበት የመፍቀድ ወይም የመከልከል ሙሉ የሕግ ሥልጣን ይኖረዋል ማለት ነው። ከሚዳሰሱ ንብረቶች (እንደ ቤት ወይም መኪና) የሚለየው የማይዳሰስ (Intangible) መሆኑና ጥበቃውም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መቆየቱ ነው።

 

የአእምሯዊ ንብረት ዘርፎች ወይም ዓይነቶች ስንት ናቸው? በሀገራችን በብዛት የሚታወቁትስ የትኞቹ ናቸው?

አእምሯዊ ንብረት በዋናነት በሦስት ትላልቅ ዘርፎች ይከፈላል። አንደኛው የቅጅ መብትና ተዛማጅ መብቶች (Copyright and Related Rights)የሚባለው ነው። ይህ ዘርፍ በዋናነት የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን የሚመለከት ነው። እንደ ሥነ-ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ሥዕል፣ ፊልም፣ ትያትር እና የኮምፒውተር ሶፍትዌሮች በዚህ ስር ይመደባሉ። እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ የቅጅ መብት የሚጠብቀው “ሐሳብን” ሳይሆን “ሐሳቡ የተገለጸበትን መንገድ” (Expression of idea) ነው። ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ንብረት (Industrial Property) ይባላል። ይህ ደግሞ ከቴክኖሎጂና ከንግድ ጋር የተያያዙ ፈጠራዎችን ይይዛል። በውስጡም ፓተንት (Patents) ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ የንግድ ምልክት (Trade Mark) ደግሞ የአንድን ድርጅት ምርትና አገልግሎት ከሌላው ለመለየት የምንጠቀምበት ምልክት ነው። በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ዲዛይን እና መልክዓ-ምድራዊ አመላካቾች (Geographical Indication) በዚህ ስር ይካተታሉ። የጋራ መብቶች (Communal Rights) ሦሥተኛው ነው። እንደ ጄኔቲክ ሀብቶች (Genetic Resources)፣ ባሕላዊ ዕውቀት (Traditional Knowledge) እና ባሕላዊ መግለጫዎች (Cultural Expressions) ያካትታል። እነዚህ የግለሰብ ሳይሆኑ የአንድ ማኅበረሰብ የጋራ ሀብቶች በመሆናቸው ለየት ያለ የሕግ ጥበቃ ይሻሉ።

 

አንድ የፈጠራ ሥራ ባለቤት ሥራውን ለማስመዝገብ ምን ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል?

እዚህ ጋር ትልቅ ልዩነት አለ። በቅጅ መብት (Copyright) ዘርፍ፣ ምዝገባ ግዴታ አይደለም። “መፍጠር ከጥበቃ ጋር እኩል ነው” የሚል መርህ አለን። አንድ ሥራ ተፈጥሮ ሊታይ፣ ሊሰማ ወይም ሊዳሰስ በሚችል መልኩ ከተዘጋጀ ባለቤቱ በሕግ ጥበቃ ያገኛል። ነገር ግን ለተሻለ ማስረጃነትና ለንግድ ውሎች እንዲያመች ማስመዝገቡ እጅግ ይመከራል።

በኢንዱስትሪ ንብረት (ፓተንትና የንግድ ምልክት) ዘርፍ ግን ማስመዝገብ ግዴታ ነው። ካላስመዘገብክ መብቱ የለህም። አሁን ላይ ሂደቱን ለማቃለል የኦንላይን (E-service) ምዝገባ ጀምረናል፤ ባለሙያዎች በ eipa.gov.et ድኅረ ገጽ ገብተው ካሉበት ሆነው በቀላሉ ማመልከት ይችላሉ።

 

ማስመዝገብ ለፈጣሪው የሚያስገኘው ትክክለኛ ጥቅም ምንድነው?

ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው። አንደኛው የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት ሲሆን፣ ይህ ሰርተፊኬት በሕግ ፊት እንደ ጠንካራ ማስረጃ ያገለግላል። ሁለተኛው፣ ሥራህን ለሌላ አካል ለመሸጥ ወይም በውል ለመስጠት (Licensing) ያስችልሃል። ሦስተኛው፣ የፈጠራ ሥራህን እንደ መያዣ (Collateral) በመጠቀም ከባንክ ብድር ለማግኘት ይረዳል። አሁን ላይ ይህንን አሠራር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ለማገናኘት በቅርበት እየሠራን ነው። አራተኛውና ዋነኛው ግን ሌሎች ያንተን ሥራ ያለ ፈቃድ እንዳይጠቀሙበት የመከልከልና ከተጠቀሙም ካሳ የመጠየቅ መብት ይሰጥሃል።

 

ስለ መብት ጥሰት ካነሱ አይቀር፣ የመብት ጥሰት የሚባለው ምንድነው?

የመብት ጥሰት ማለት አንድን ጥበቃ የሚደረግለትን የአእምሯዊ ንብረት ሥራ ያለ ባለቤቱ ፈቃድ ለንግድ ዓላማ መጠቀም ነው። ይህ ጥሰት በቀጥታ ሥራውን በመገልበጥ ጥሰቱ እየተፈጸመ መሆኑን እያወቁ ዝም በማለት ወይም ለጥሰቱ የሚሆኑ መሣሪያዎችን በማቅረብ ሊፈጸም ይችላል።

በጥናት እንደተረጋገጠው በሀገራችን በተለይም በሙዚቃና በፊልም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ይታያል።

እዚህ ጋር አንድ አነጋጋሪ ነጥብ ላንሳ፤ “ሀገርን እስከጠቀመ ድረስ ቴክኖሎጂን መቅዳት ችግር የለውም” የሚል አስተሳሰብና “አእምሯዊ ንብረት መጠበቅ አለበት” የሚሉ ሐሳቦችን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

ይህ በጣም አስፈላጊና ወቅታዊ ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ሕግ የሚመራበት ዋናው መርህ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማሳደግ ሲሆን ይህም የሚከናወነው በፈጣሪዎች መብትና በሕዝብ ጥቅም መካከል ተገቢውን ሚዛን በመጠበቅ ነው። ሕጉ አንድ ፈጣሪ ላፈሰሰው ጊዜና ገንዘብ ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ኢንቨስትመንቱን እንዲያስመልስ የሚያበረታታ ቢሆንም ይህ የባለቤትነት መብት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንዲገደብ በማድረግ (ለምሳሌ ለፓተንት 20 ዓመት) ግኝቱ ውሎ አድሮ የሕዝብ ሀብት እንዲሆንና ማኅበረሰቡ በቀላሉ እንዲጠቀምበት ያደርጋል።

በተጨማሪም ሕጉ እውቀት ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበትን ሥርዓት የሚዘረጋ ሲሆን ፈጣሪዎች የጥበቃ መብት ለማግኘት የግኝታቸውን ዝርዝር መረጃ ለባለሥልጣኑ የመግለጽ ግዴታ አለባቸው። ከዚህም ባለፈ እንደ ትምህርት፣ ምርምርና ዜና ዘገባ ላሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ‘ፍትሐዊ አጠቃቀም’ በሚል መመሪያ የፈጣሪውን ፈቃድ ሳይጠይቁ በከፊል መጠቀምን ይፈቅዳል። እንደ ወረርሽኝ ያሉ የሕዝብ ጤና አደጋዎች ሲያጋጥሙ ደግሞ መንግሥት ያለባለቤቱ ፈቃድ ሌላ አካል እንዲያመርት የሚፈቅድበት ‘አስገዳጅ ፈቃድ’ የተሰኘ አሠራር መኖሩ፣ ሕጉ ለሕዝብ ሕይወትና ደኅንነት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያረጋግጣል።

 

የአእምሯዊ ንብረት መብት መከበር ለውጭ ኢንቨስትመንትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ያለው ፋይዳ ምንድነው?

ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው። ማንኛውም ባለሀብት ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጣ መጀመሪያ የሚጠይቀው “የእኔ የፈጠራ ሥራ ወይም የንግድ ምልክት በሕግ ጥበቃ ይደረግለታል ወይ?” የሚለውን ነው። ስለዚህ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓታችንን ማጠናከር የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ የኢኮኖሚ ዋስትናችን ነው። ይህ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው። በተለይ ደግሞ እንደ እኛ ዓይነት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታትና የባለሙያዎችን መብት በማስከበር የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ይችላሉ።

 

በመጨረሻም ለፈጣሪዎች፣ ለንግዱ ማኅበረሰብና ለሕዝቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

መልዕክቴ “መብትህን ቀድመህ አስከብር” የሚል ነው። ብዙ ሰዎች ሥራቸው ገበያ ላይ ወጥቶ ጥሰት ሲያጋጥማቸው ነው ወደ እኛ የሚመጡት። ያን ጊዜ ጉዳቱ ሰፊ ስለሚሆን ለመመለስ ይከብዳል። ስለዚህ ማንኛውም ፈጣሪ ሥራውን ለሕዝብ ከመልቀቁ በፊት ቢሯችን መጥቶ ማማከርና ማስመዝገብ አለበት። ሕዝቡም የሌሎችን ልፋትና የፈጠራ ውጤት ያለ ፈቃድ ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርበታል። አእምሯዊ ንብረት የሀገር ሀብት ነውና ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል።

ስለነበረን ሰፊና ዝርዝር ማብራሪያ እጅግ እናመሰግናለን።

እኔም አመሰግናለሁ።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here