አንዳንዱ ሰው ለተለየ ዓላማ ይጠራል:: ብዙኀኑ ግን ተመሳስለው ያልፋሉ:: ጥቂቶች ብቻ በልዩነት የግል አሻራቸውን አሳርፈው ይሄዳሉ:: ኢትዮጵያ ብዙ ሰዎችን ወልዳ ሸኝታለች:: ግን ማን ይታወሳል? ማን ይሄን ሠራ ይባላል? ማን ለሰው ልጆች ባስቀመጠው ዘመን አይሽሬ ሥራ ይወሳል? ከጥቂቶች በቀር!
ብዙዎች መንጋውን ሲከተሉ፣ በመኖር ስንክሳር ሲተበተቡ፣ መስሎ መኖርን እንደ ጥበብ ሲቆጥሩ ጥቂቶች እውነቱን ተናግረው ቅርብ አድረዋል:: እውነቱን ተናግረው ዛሬ ላይ ስማቸውን እንድናስታውሰው አድርገውናል::
ከተወለደ 93 ዓመቱ ነው:: ከሞተ ደግሞ 46 ዓመታት አልፈዋል:: በሁለት መንግሥታት ብርቱ የነጻነት ተጋድሎ አድርጓል:: ጀግኖች ሁልጊዜም በሚከተላቸው ትውልድ አንደበት ውስጥ ይታሰባሉና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ዐባይ የቋንቋዎች እና ባህል ጥናት ተቋም “ዐባይ ዝክረ ታላላቅ” በሚል አቤ ጉበኛን ዘክሮታል::
የደራሲ፣ ትውኔት ጽሐፊ፣ ጋዜጠኛ፣ገጣሚ እና ታጋይ አቤ ጉበኛን የሕይወት ታሪክ ያቀረቡት በዩንቨርሲቲው አስተማሪ የሆኑት ሞገስ ሚካኤል (ዶክተር) “አቤ አብዮትን የሚጠላ፣ ሰላማዊ ትግልን የሚወድ የነጻነት ታጋይ ነበር” ብለዋል::
አቤ በንጉሡ እና ደርግ ዘመናት ብርቱ የብዕር ተጋድሎ አድርጎ በመጨረሻም ለነጻነት የተሳደደ፣ የተገረፈ፣ የተጋዘ እና የሞተ ሰው ነው::
ብዕር ከጠመንጃ ይልቅ ገዳይ ነው፤ ጠመንጃ ሰውነትን ብቻ ሲጎዳ ብዕር ግን የጨቋኞችን የጥፋት ሥርዓት ከሥር መሠረቱ ይነቅላል::
የአቤ ጉበኛ የሕይወቱ መርህ ስነ ጽሑፍን ለነፃነት አዋጅነት መጠቀም ነበር:: በቃላት ሰይፍ የሥርዓትን አረመኔነት የገጠመው፣ በምርኮና በስቃይ ያልተበገረው የኢትዮጵያዊ የሕሊና ነፃነት ትንቢታዊ ድምፅ አቤ ጉበኛ ሰኔ 25 ቀን 1925 ዓ.ም በአቸፈር ወረዳ ተወለደ::
የአብነት ትምህርቱን በይስማላ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከታትሏል:: የቅኔና የዜማ ሊቅ የነበረው አቤ መምህራኑ “እሱ አቤ ጉበኛ ሳይሆን አቤ ጉደኛ ነው” በማለት የውስጡን ኃያል ብቃት ቀደም ብለው ተንብየውለታል በማለት የደራሲውን የሕይወት ታሪክ መዝገብ በመጥቀስ ሞገስ ሚካኤል ገልጸዋል::
የሕይወት ክብደቱ የጀመረው ገና በሦስት ዓመቱ እናቱን በሞት ሲያጣ ነበር:: ይህም በዓለማችን ላይ ላለው የሰው ልጅ ስቃይ አቤ ጥልቅ ስሜት እንዲኖረው አድርጎት ሊሆን ይችላል::
በዳንግላ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ተምሯል:: አቤ በ1946 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ባዕታ ቤተ ክርስቲያን ተጠግቶ እንደ ቆሎ ተማሪ ሆኖ እውቀቱን አዳብሯል:: መርጌታም ሆኖ አገልግሏል::
በ1949 ዓ.ም የታተመው “ከመቅሰፍት ሰራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት” የተሰኘው የግጥም መድበሉ የአቤ የብዕር ትግል መጀመሩን ያበሰረ የመጀመሪያ ሥራው ሆኖ ይጠቀሳል:: ይህንን ክህሎቱን በማየትም በ1951 ዓ.ም በ26 ዓመቱ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ተቀጥሮ ሠርቷል፡፡
በ1953 ዓ.ም ያሳተመው የሮም አወዳደቅ የተሰኘው ተውኔት በወቅቱ የነበረው ገበሬ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ያለውን ብሶት ቁልጭ አድርጎ በማሳየቱ የሥልጣን ባለቤቶችን ያስደነገጠ ነበር::
በመቀጠል በ1955 ዓ.ም ባወጣው የአመፅ ኑዛዜ በተሰኘው ልብወለድ ተምረውና ሰርተው ሀብት ያገኙ ሰዎች ደሃ ወገኖቻቸውን እንዲረዱ ማሳሰቢያ የሰጠበት ነበር::
በ1956 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ሰይፈ ነበልባል ደግሞ የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍ ታሪክን የቀየረ ድርሰት ነበር:: መጽሐፉ እንደ “አልወለድም” ይታገዳል በሚል ስጋት ህዝቡ ለመግዛት የነበረው ርብርብ ከፍተኛ ነበር፤ በሁለት ወር ውስጥ ብቻ አራት ጊዜ ታትሞ 25 ሺህ ኮፒ መሰራጨቱ መጽሐፉ በሕዝብ ዘንድ ምን ያህል እንደተወደደ ያሳያል ብለዋል መምህር ሞገስ::
ይህ መጽሐፍ በደርግ ዘመን መንግሥት ሳይቀር እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ መሰራጨቱ አቤ ወደፊት የሚመጣውን ሥርዓት ቀድሞ የመተንበይ ችሎታ እንደነበረው ማስረጃ ሆኖ ይቀርባል::
በ1957 ዓ.ም በሰኔ ወር ለሕዝብ እንደራሴነት ለመወዳደር መነሳቱና የ50 ሰዎች የድጋፍ ፊርማ ማግኘቱ የብዕር ትግሉን ወደ ተግባራዊ የፖለቲካ ትግል መለወጡን የሚያሳይ ነው:: ነገር ግን የነፃነት ታጋዩ አቤ ሰኔ 21 ቀን 1957 ዓ.ም በፀጥታ ኃይሎች በድንገት ተይዞ ታሰረ::
በእስር ላይ በነበረበት ወቅት በቀን ሦስት ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ መፈረም፣ ከተወሰኑ ስፍራዎች ውጭ እንዳይዘዋወር መገደብ፣ ከማንኛውም ሰው ጋር እንዳይገናኝ መከልከልና በወር ከ50 ብር በላይ እንዳይይዝ መገደብ በሚሉ አስከፊ ሕጎች መታቀቡ የሥርዓቱን ፍርሐት ያሳየ ነበር::
ከአራት ወር ተኩል በኋላ በወቅቱ ኢሉባቦር “ሞቻ የሰው ልጅ መሞቻ” ወደ ተባለው አስከፊ ቦታ ተወርውሮ እስከ 1961 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ዓመታት በስቃይ ቆይቷል::
በ1969 ዓ.ም በጻፈው ጽሑፍም ይህንን የግፍ ዘመን አስታውሶ “እኔ የማንም መጫወቻ ሆኛለሁ፣ በኢትዮጵያዊነቴ ባላፍር ምናለበት?” በማለት የደረሰበትን በደል በምሬት ገልጾታል::
በ1961 ዓ.ም ከእስር እንደወጣ በሁለት ቀን ልዩነት የሀሜት ሱሰኞች የሚለውን መጽሐፉን አሳትሟል:: በመቀጠልም 602 ገጽ ባለው አንድ ለእናቱ መጽሐፉ አፄ ቴዎድሮስን የአንድነት ተምሳሌት አድርጎ በመሳል የወቅቱን አመራር ክፉኛ ነቅፏል::
አቤ በህይወት ዘመኑ ከ23 በላይ መጻሕፍት ማበርከቱን ታሪክ ይመሰክራል::
አቤ ጉበኛን ለመዘከር በተሰናዳው መድረክ ላይ በአልወለድም መጽሐፍ ስልት እና ይዘት ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አንተነህ አወቀ (ዶክተር) “አቤ በዚህ መጽሐፍ በገጸ ባህሪ እና በተግባር የክርስቶስን ሚና ወስዷል” ብለዋል::
ስለ ነጻነት መሳደድ፣ መታሰር፣ ማስተማር፣ መገረፍ፣ በግዞት መያዝ እና ሞትን መቀበልን የመሳሰሉ መከራዎችን ለነጻነት ሲል ተቀብሏል ብለዋል::
በዚህ መጽሐፉ በ1955 ላይ ሆኖ የሚመጣውን የ1966 ዓ.ም የደርግ አብዮት መተንበይ የቻለ ታጋይ ብዕረኛም ነበር ብለዋል::
አቤ የመጀመሪያው ልጁን ሚካኤል አቤን የወለደው በኢሉባቦር አውራጃ በተጋዘበት ወቅት ነበር፡፡ በኋላም ሁለት ሴት ልጆችን ወልዷል:: በነበረበት ጊዜም ለወገኖቹ በጻፈው ደብዳቤ ይህችን ግጥም ማስፈሩ በታሪክ ይወሳለታል::
መቱንም አላየሁ ጎሬንም አላየሁ
እናንተ ዘመዶቼ አልሞትኩም ሞቻለሁ፡፡
እንዳይንቀሳቀስ መከልከሉን፣ በቅርብ የነበሩትን ጎሬ እና መቱ ከተማን ማየት አለመቻሉን ነገር ግን ሞቻ የሚባል ቦታ ላይ በግዞት በሕይወት መኖሩን የተናገረበት ቅኔ ነበር:: በሕይወት አለሁ:: ሞቻ የሚባል ቦታ ማለቱ ነበር::
እንዲህ ዓይነት ታጋዮች እንደ ንጋት ኮከብ አልፎ አልፎ የሚገኙ ናቸው:: ሁልጊዜ አምባገነን አገዛዝን የሚታገሉ፤ ሕዝብን ወደ ነጻነት መንገድ የሚመሩ፤ ሀገርን ከራሳቸው ያስቀደሙ ታጋዮች ብርቅ ናቸው::
ሕዝብን የሚበድልን አገዛዝ ፊት ለፊት በመጋፈጥ የኖረው አቤ ከሥራው ተባሮ በሙሉ ጊዜ ጸሐፊነት ብቻ ይኖር ነበር:: የካቲት 1 ቀን 1972 ዓ.ም አዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ አካባቢ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድቦ ተገኘ::
የብዕር ታጋዩ አቤ ሆስፒታል እንደገባ ሕይወቱ አለፈ:: የካቲት 4 ቀን 1972 ዓ.ም በአሁኑ ሰሜን ጎጃም ዞን በይስማላ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስርአተ ቀብሩ ተፈጸመ::
ዛሬም ድረስ አቤ ጉበኛ ለሀገሩና ለወገኑ የነበረው ጽኑ ፍቅርና ለፍትህ የከፈለው መስዋዕትነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በወርቃማ ቀለም ተጽፎ ይኖራል:: የአቤ ምንፈስ አፍሪካዊ አትንኩኝ ባይነትን ያሳደገ የአያቶቻችን ጀግንነት ነበር::
ማረፊያ
እግዜር ባያድለኝ እናትን እንድጠቅም
ወዴት ብዮ ልርዳት እናቴን አላውቅም
እናቴ በድንገት ተነሥተሽ ባይሽ
ማሚቴ ልልሽ ነው እማማ ልልሽ
ከሠላሳ ስርቅ እኔ እንኳን ልጅሽ
አንቺ አሥራ ሰባትን ሳትደርሽ ቀረሽ፡፡
አቤ ጉበኛ እናቱን በ3 ዓመቱ ሲያጣ እሳቸው 17 ዓመት ሊሞላቸው ጫፍ ደርሰው ነበር፡፡ ይህ ግጥም ያን የገለጸበት ነበር፡፡
(አቢብ በዓለሜ)
በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


