ተመራማሪዎች በእንክብል መልክ የተዘጋጀ የቫይታሚን “ዲን” ተጨማሪ ምግብ የጡት ካንሰር ህሙማን በየእለቱ እንዲወስዱ ማስቻል ከ “ኬሞቴራፒ” ህክምና በኋላ የመዳን ምጣኔያቸውን ካልወሰዱቱ በእጥፍ እንደሚያሳድገው ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑኑ አስነብቧል::
በብራዚል የሳኦፖሎ ተመራማሪዎች እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆናቸው 80 ተመላላሽ የጡት ካንሰር ታማሚዎች በሁለት ቡድን ተከፍለው 40ዎቹ የተመጠነ የቫይታሚን “ዲ” ተጨማሪ እንክብል ቀሪዎቹ የ “ኘሌስቦ ታብሌት” ወስደው “የኬሞቴራፒ” ህክምና ተሰጥቷቸዋል::
የ “ኬሞቴሯፒ” ህክምና 40 በመቶ የካንሰር እጢዎችን ለመቀነስ እና ለማስወገድ ከቀዶ ጥገና በፊት የሚሰጥ ህክምና መሆኑም ተገልፆል:: ከስድስት ወራት ክትትል በኋላ በቡድኖቹ መካከል ጉልህ ልዩነት መገኘቱን ነው የደረሱበት – ተመራማሪዎቹ:: በውጤቱም ቫይታሚን “ዲ” የወሰዱት ከ “ኬሞቴራፒ” በኋላ የካንሰር ህመማቸው ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን አረጋግጠዋል:: “ኘሌስቦ” የወሰዱት የቡድን አባላት ደግሞ 24 በመቶ የሚሆኑት ከካንሰር ህመማቸው ተፈውሰዋል::
ቫይታሚን “ዲ” አካል “ካልሼየም” አና “ፎስፈረስን” እንዲሻ ይረዳል፤ በዚህም የአጥንት ጥንካሬን ይጠብቃል:: ከዚህ በበለጠም ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን የመከላከል ዓቅምን ያሳድጋል:: ቫይታሚን “ዲ” በዋናነት ከፀሀይ ብርሃን የሚገኝ ቢሆንም ከተወሰኑ የመግብ ዓይነቶችም ሊገኝ እንደሚችል ነው የተጠቆመው::
በመጨረሻም ቫይታሚ “ዲ” የጡት ካንሰር የ “ኬሞቴራፒ” ህክምናን ውጤታማነት ለማሻሻል ከሚጠቅሙ ሌሎች መድሃኒቶች ጋር ሲነፃፀር ተደራሽ እና በቀላሉ በአነስተኛ ወጪ የሚገኝ አማራጭ መሆኑ ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


