ሃብት፣ ሥልጣን፣ ዝና ወይም ኃይል ከሰው ህይወት ጋር ሊያያዙ ቢችሉም፤ የሰውን እውነተኛ ክብር የሚያሳየው ግን ጥበብ ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ “ጥበበኛ ሰው” ተብሎ የሚጠራው ብዙ መፃህፍት ያነበበ ወይም ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያለው ብቻ አይደለም። ጥበበኛ ሰው ህይወትን በሚዛናዊ አስተሳሰብ የሚመለከት፣ ሰዎችን በክብር የሚያይ፣ በችግር ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔ የሚሰጥ እና ለሌሎች ጥቅም የሚኖር ነው።
በአግባቡ መረዳት እንዲያስችለን ጥበብ ምንድን ነው? ለሚለው ቀዳሚ ምላሽ ማግኘት ተገቢ ነው። ጥበብ ማለት እውቀትን ከልምድ፣ ከሥነ-ምግባር እና ከትክክለኛ ፍርድ ጋር በማጣመር ትክክለኛ ውሳኔ የመስጠት ችሎታ ነው። አንድ ሰው ብዙ እውቀት ሊኖረው ይችላል፤ ጥበብ ግን ያ እውቀት ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲውል የሚያደርግ ኃይል ነው። በሌላ አነጋገር እውቀት “ምን?” ብሎ ሲጠይቅ፣ ጥበብ ግን “እንዴት?” እና “ለምን?” ብሎ ውሳኔ ላይ ይደርሳል።
ለምሳሌ አንድ ሰው ብዙ ሃብት ማግኘት የሚችል ቢሆንም ያንን ሃብት ለራሱ እና ለሌሎች ጥቅም ላይ ካላዋለ ጥበበኛ ሊባል አይችልም። በተመሳሳይ በትምህርት ከፍ ያለ ደረጃ የደረሰ ሰው ሰዎችን በንቀት የሚመለከት ከሆነ ጥበበኛ አይደለም፡፡
ጥበብ ብዙ ጊዜ ከትዕግስት፣ ከማስተዋል፣ ከርህራሄ እና ራስን ከመቆጣጠር ጋር ይያያዛል። ጥበበኛ ሰው ከመናገሩ በፊት ያስባል፤ ከመፍረዱ በፊት ያዳምጣል፤ ከመቆጣቱ በፊት ሁኔታውን ይመረምራል።
የጥበበኛ ሰው ዓበይት መለያ ባህሪያት
የ“ጥበብ ሰው” መለያ ባህሪያትን በተመለከተ ብዙ ፈላስፎች፣ የሥነ-ምግባር ባለሙያዎች፣ የሥነ-ልቦና ተመራማሪዎች እና መንፈሳዊ መምህራን ፅፈዋል።
ጥበበኛ ራሱን ያውቃል፦ ጥበበኛ መጀመሪያ ራሱን ያውቃል። ድክመቱን እና ጥንካሬውን ይገነዘባል። ሁሉን አውቃለሁ ብሎ አይመካም፤ ከሌሎች ለመማር አያፍርም። “እውነተኛ ጥበብ ራስን በማወቅ ይጀምራል” በማለት ደግሞ ሶቅራጥስ ጥበበኛ ሰው ራሱን የሚመረምር፣ የራሱን ድክመት የሚያውቅ እና “ሁሉን አውቃለሁ” ብሎ የማይመካ ነው ማለቱ በጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ ፕሌቶ “Apology” መፅሐፍ ላይ ተገልጿል።
ጥበበኛ ትዕግስተኛ ነው፦ ዘመናችን ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ ቢሆንም፣ ጥበበኛ ሰው ግን ትዕግስትን ያስቀድማል። በችግር ጊዜ አይደነግጥም፤ በቁጣም ፈጣን ውሳኔ ላይ አይደርስም። ሁኔታዎችን በጥልቀት በማየት መፍትሄ ይፈልጋል። የሰው ልጅ መልካም ህይወት፣ ሥነ-ምግባር፣ ደስታ እና በጎ ባህሪ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በአርስቶትል የተፃፈው “Nicomachean Ethics” መፅሐፍ ጥበበኛ ሰው ሚዛናዊ፣ ትዕግስተኛ፣ ፍትሃዊ እና በምክንያት የሚመራ ነው። ከመጠን የወጣ ባህሪን ይቃወማል፤ “መካከለኛ መንገድ” ይከተላል ይላል።
ጥበበኛ ሰዎችን ያከብራል፡- ጥበብ ከሰብዓዊነት ውጭ አይኖርም። ጥበበኛ ሰው የሌሎችን ሃሳብ ያዳምጣል፣ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ይፈልጋል። በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ ወይም በሃብት ልዩነት ሰዎችን አይከፋፍልም። “A calendar of Wisdom” በተሰኘው መፅሐፍ ደግሞ ሊዮ ቶልስቶይ ጥበበኛ ሰው ለሌሎች የሚራራ፣ በፍቅር የሚኖር እና ህሊናውን የሚያዳምጥ ሰው መሆኑን ፅፏል።
ጥበበኛ ከስህተቱ ይማራል፡- ሰው ሁሉ ስህተት ይሰራል። ጥበበኛ ሰው ግን ስህተቱን በመቀበል ከሱ ይማራል። ሌሎችን ከመውቀስ ይልቅ ራሱን ይመረምራል። ስህተትን እንደ ትምህርት ያያል። ይህን የጥበበኛ ሰው መለያ ባህሪ ፓውሎ ኮኤሎ “The Alchemist” በተሰኘው መፅሐፍ “ጥበበኛ ሰው ከህይወት ተሞክሮው ይማራል፤ ስህተቱን አይደግምም” ይላል።
ጥበበኛ ለሌሎች ይኖራል፦ እውነተኛ ጥበብ ራስን ብቻ አያገለግልም። ጥበበኛ ሰው ለቤተሰቡ፣ ለማህበረሰቡ እና ለሃገሩ ጥቅም ያስባል። እርዳታ ማድረግ፣ ምክር መስጠት፣ ሰላም ማስፈን እና ችግር መፍታት መገለጫዎቹ ናቸው። “ጥበብ ከርኅራኄ ጋር ሲቀላቀል ነው እውነተኛ የሚሆነው” በሚል ደግሞ “The Art of Happiness” መፅሐፍ ላይ ዳላይ ላማ ርህራሄ የጥበበኛ ሰው ቁልፍ መገለጫ ባህሪ መሆኑን አስገንዝቧል።
በአሁኑ የዲጂታል ዘመን፣ መረጃ (Information) በየሴኮንዱ እንደ ናዳ በሚወርድበት ወቅት፣ በመረጃ መበልጸግን እና ጥበበኛ መሆንን የማምታታት አዝማሚያ ይታያል። ሆኖም ግን “ሁሉን አዋቂነት” እና “ጥበበኝነት” ሰማይና ምድር ናቸው። እውቀት መረጃዎችን የማከማቸት ችሎታ ሲሆን፣ ጥበብ ግን እነዚያን መረጃዎች መቼ፣ እንዴት እና ለምን መጠቀም እንዳለብን የመለየት ጥልቅ ጥበብ ነው።
የጥበብ ሰው፣ ጥያቄ የማይጠፋበት ሳይሆን ለጥያቄዎቹ ትክክለኛውን ጥልቀት የሚሰጥ ነው። ጥበበኛ ሰው ማለት ዓለምን እንደ ሁኔታው የሚረዳ፣ ከራሱ ስሜት ይልቅ ለዕውነት ቅድሚያ የሚሰጥ እና በእውቀት ከመታበይ ይልቅ ባለማወቁ ውስጥ ለመማር ዝግጁ የሆነ ሰው ነው። ጥበብ የሚጀምረው “ሁሉንም አውቃለሁ” ከሚል ትዕቢት ሳይሆን፣ “ከማውቀው ይልቅ የማላውቀው ይበልጣል” ከሚል ትህትና ነው።
አንድን ሰው እውነተኛ ጥበበኛ የሚያደርገው የዕውቀቱ ብዛት ሳይሆን፣ ለዕውቀት ያለው አመለካከት ነው። ይህም “የአዕምሮ ትሕትና” (Intellectual Humility) ተብሎ ይጠራል። ብዙዎች ጥበብን ሁሉንም መልሶች እንደመያዝ ይቆጥሩታል፤ እውነታው ግን ጥበብ የሚጀምረው መልስ በማጣት ሳይሆን፣ “አላውቅም” ብሎ ለመቀበል ባለመፍራት ነው።
ታዋቂው ፈላስፋ ሶቅራጥስ “እኔ ከሌሎች የምበልጠው አንድ ነገር ብቻ ስለማውቅ ነው፤ እርሱም ምንም አለማወቄን ማወቄ ነው” በማለት የተናገረው ዝነኛ ንግግር የጥበብን ማዕዘን ያሳየናል። ጥበበኛ ሰው የራሱ እውቀት ውሱን መሆኑን ይረዳል፤ በዚህም ምክንያት አዳዲስ ሀሳቦችን ለመቀበልና ስህተቱን ለማረም ሁልጊዜ ዝግጁ ነው።
በሚጮህና ሁሉም ሰው ለመሰማት በሚሽቀዳደምበት ዓለም ውስጥ፣ የጥበበኛ ሰው ትልቁ መለያው የዝምታው ጥልቀት ነው። ብዙዎች ዝምታን እንደ ድክመት ወይም እንደ አለማወቅ ቢቆጥሩትም፣ ለጥበበኛ ሰው ግን ዝምታ መረጃን የመሰብሰቢያ እና የማሰላሰያ ላቦራቶሪው ነው።
ጥበበኛ ሰው ከመናገሩ በፊት ያዳምጣል፤ ሲናገርም ቃላቱን ይመዝናል። “ሞኝ ሰው መናገር ስላለበት ይናገራል፤ ጥበበኛ ሰው ግን የሚናገረው የሚባል ነገር ሲኖረው ብቻ ነው” የሚለው አባባል ይህንን እውነት ያረጋግጣል። ማዳመጥ ለጥበበኛ ሰው ሌላው ሰው የሚናገረውን ድምፅ መስማት ብቻ አይደለም፤ ከንግግሩ በስተጀርባ ያለውን ስሜት፣ ፍላጎት እና ያልተነገሩ እውነቶችን የመረዳት ጥበብ ነው።
ጥበብ የሚገኘው በንግግር ብዛት ሳይሆን በጥልቀት በማዳመጥ ነው። ጥበበኛ ሰው ምላስ የልብ ተርጓሚ መሆኗን ስለሚያውቅ፣ ልቡ ሳይመዝነው ምላሱ አይቀድመውም። ዝምታው ደግሞ ባዶነት ሳይሆን፣ በትዕግስት እና በማስተዋል የተሞላ ዝግጅት ነው።
ጥበበኛ ሰው ነገሮችን የሚመለከተው አሁን ካለበት ቅጽበት አልፎ ነው። ብዙ ሰው በዕለት ተዕለት ችግሮችና ስሜቶች ተመርቶ ውሳኔ ሲያሳልፍ፣ ጥበበኛ ሰው ግን ከፍ ብሎ ሁኔታውን ከሩቅ ይቃኛል። ይህም በአጭር ጊዜ ጥቅምና በረጅም ጊዜ ውጤት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲረዳ ያደርገዋል። ጥበብ ማለት የአንድ ነገር ፈጣን ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት የሚመጣውን ሰንሰለታማ ተጽዕኖ ቀድሞ ማስተዋል ነው። ጥበበኛ ሰው በደመ ነፍስ የሚመራ ሳይሆን፣ በዓላማና በራዕይ የሚኖር ነው።
ጥበበኛ ሰው “ሁለቱም እውነት ሊሆኑ ይችላሉ” ብሎ ማሰብ የሚችል ነው። ነገሮችን በአንድ ወገን ብቻ ረግጦ ከመቆም ይልቅ፣ በተቃራኒዎች መካከል ያለውን ውበትና ሚዛን መፈለግ የጥበብ ከፍተኛው ደረጃ ነው። ይህ ችሎታው በግጭት ወቅት ሰላምን እንዲያወርድ፣ በውሳኔ ወቅትም ፍጹም ሚዛናዊ እንዲሆን ይረዳዋል።
ጥበበኛ ሰው መሆን በአንድ ጀምበር የሚደረስበት ግብ ወይም የሚጨበጥ የክብር ማዕረግ አይደለም። ይልቁንም በየቀኑ የሚታደስ፣ በየሰዓቱ የሚለማመዱት የሕይወት መንገድ ነው። ጥበብ በትምህርት ቤት የሚሰጥ የምስክር ወረቀት ሳይሆን።
በዝምታው፣ በትዕቢቱ ሳይሆን በትሕትናው የሚታወቅ ነው።
ጥበብ ለጥቂት የተመረጡ ሰዎች ብቻ የተሰጠች ስጦታ አይደለችም፤ ይልቁንም ቆም ብሎ ለማስተዋል፣ በትሕትና ለመኖርና እውነትን በቅንነት ለመፈለግ ለሚመርጥ ለማንኛውም ሰው ክፍት የሆነች መንገድ ናት። ስለዚህ፣ ጥበበኛ ለመሆን መነሳት ያለብን ከውጭ ሳይሆን ከውስጣችን ነው። ዓለምን ለመለወጥ ከመሞከር በፊት ራስን መረዳት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ነው።
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


