ከቅኝ ግዛት ወደ አጋርነት

0
94

የዓለማችንን ጉዞ ከሚወስኑ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ መልክዓምድራዊ አቀማመጦች አንዱ ነው – የአፍሪካ ቀንድ። ይህ በመሆኑም  ኀያላኑ ለአፍታም ቢሆን ዐይናቸውን አንስተውበት አያውቁም። በቀንዱ አካባቢ በሚገኙ ሃገራት የቀይ ባሕር ዳርቻዎች የጦር ሰፈር መመሥረታቸው እና ለመመሥረት የሚያሳዩት እሽቅድምድም የዚህ ማሳያ መሆኑን አፍሪካ ኒውስ አስነብቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አካባቢው በጸጥታ ስጋት ከሚታመሱት መካከልም አንዱ ነው። ይህን ችግር በመፍታት በዕድገት ጎዳና የምትራመድ አህጉር ለማድረግ ታዲያ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

አፍሪካ ከውጭ ርዳታ ተቀባይነት ወደ እኩል አጋርነት ለመሸጋገር የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ እየሠራችም ነው። ለስኬቱ  አንደኛው ስልት ደግሞ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፍ ትብብር መሆኑን ከአፍሪካ ኒውስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ፈረንሳይ አንዷ አጋር ስትሆን በአህጉሪቱ ያላትን ተፅዕኖ በአዲስ መልኩ ለማስቀጠል እየሞከረች ትገኛለች። ከሰሞኑ በኬኒያ መዲና ናይሮቢ ከተማ የተካሄደው ጉባዔ ደግሞ ብዙ ክስተቶች የተስተናገዱበት ነው።

አፍሪካ ኒውስ እንዳመላከተው የአፍሪካ እና አውሮፓ ሃገራት ግንኙነት አብዛኛው የቅኝ ግዛት ታሪክ ነው። ከሰሞኑ በተካሄደው ጉባዔም ይህ ሐሳብ ከፍ ብሎ ነበር የተስተጋባው። ይህን የተዛባ ግንኙነት በማረም ለአዲስ እና ፍትሐዊ ግንኙነት በር የከፈተ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።

የፈረንሳዩ ዜና ማሰራጫ ፍራንስ 24 እንደዘገበው በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ – ፈረንሳይ ጉባዔ በአፍሪካ እና በፈረንሳይ መካከል ስላለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነትና የልማት ግንኙነት ውይይት ተደርጓል። በተለይ በአፍሪካ ስላለው የኀይል ሚዛን፣ የወጣቶች ጥያቄ፣ የውጭ ተፅዕኖ እና የኢኮኖሚ ትብብር ላይ ትኩረት የተደረገበት ነበር።

በጉባኤው የሃገራት መሪዎችን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት (AU)፣ የአውሮፓ ሕብረት (EU)፣ የልማት ባንኮች፣ የቢዝነስ ተቋማት እና የወጣቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል። “በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት” የሚለው ሐሳብ ደግሞ ተደጋግሞ ስለመነሳቱ የመገናኛ አውታሮች ዘግበዋል።

በጉባዔው ምን ተባለ?

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከቀድሞው የቅኝ ግዛት ታሪክ የተለዬ አዲስ የአጋርነት ግንኙነት ለመገንባት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል። ሃገራቸው በተለይ በደህንነት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንትና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ከአፍሪካ ጋር ትብብሯን ለማጠናከር እንደምትሠራ ነው የተናገሩት።

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በንግግራቸው “የወደፊቱ ግንኙነት በመተባበር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” ብለዋል።

ማክሮን እንዳሉት ሃገራቸው ከአፍሪካ ጋር አዲስ እና እኩልነት ያለው ሽርክና መፍጠር ትፈልጋለች። ግንኙነቱም በቅኝ ግዛት ታሪክ ሳይሆን በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል።

በአፍሪካ የወጣቶች ኀይል ለዓለም ኢኮኖሚ ትልቅ ዕድል መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ማክሮን፣ በቴክኖሎጂ፣ በታዳሽ (ንፁህ) ኃይል፣ በትምህርትና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ትብብሮች እንዲጠናከሩ ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን በጣም እየጎዳ መሆኑን በመግለጽ ለአረንጓዴ ልማት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል። በደህንነት እና በፀረ – ሽብር ዘርፍ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር በቅርበት መሥራት ወሳኝ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።

“ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መውጣት፣ አፍሪካ እንደ ተቀባይ ሳይሆን እንደ እኩል አጋር መታየት አለባት” የሚለው ሐሳብ ደግሞ ከአፍሪካ ሃገራት መሪዎች በኩል ተደጋግሞ ተነስቷል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አፍሪካ የውጭ እርዳታን ብቻ የምትጠብቅ አህጉር መሆን እንደሌለባት ገልጸዋል። “አፍሪካ ሀብት አላት፣ ወጣት ኃይል አላት፣ የሚያስፈልጋት ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት ነው” ብለዋል።

አፍሪካ ከውጭ አጋሮች ጋር ያላት ግንኙነት በእኩልነትና በመከባበር ላይ መመሥረት እንዳለበት አሳስበዋል። በአፍሪካ ወጣት አምራች ኃይል በብዛት መኖሩ ለዓለም ኢኮኖሚ በጣም ጠቃሚ  እንደሚሆንም ተናግረዋል።

በታዳሽ (ንፁህ) ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚና በአረንጓዴ ልማት ላይ ትብብሩ እንዲጠናከር ጠይቀዋል። የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ላይ የሚያሳድረውን ጉዳት በመግለጽ ለአፍሪካ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲጨምርም ጠይቀዋል።

አፍሪካ በዓለም ውሳኔ ሰጪ ተቋማት ውስጥ በቂ ውክልና ሊኖራት እንደሚገባም አስታውቀዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ቦታ (ውክልና) እንደሌላት ልብ ይሏል።

ፈረንሳይ ደግሞ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው አምስት ሃገራት መካከል አንዷ ናት። ይህ መሆኑ ደግሞ የአፍሪካ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተሳታፊ ነበሩ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና ሊኖራት እንደሚገባ ተናግረዋል። በኬንያ የተካሄደው ጉባዔም ለአፍሪካ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ነው የተጠቆመው።

 

የጉባዔው ዋና ነጥቦች

የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር

የጉባዔው ትልቁ ዓላማ እንደነበር አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አመላክቷል፤ በአፍሪካና በፈረንሳይ መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደተደረገ ያነሳው ዘገባው አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት፣ በወጣት የሰው ኀይልና በሰፊ ገበያ ዕድሎች የተሞላች አህጉር ስለመሆኗ ጠቁሟል፤ ፈረንሳይ ደግሞ በመሠረተ ልማት፣ በኀይል፣ በግብርናና በቴክኖሎጂ ዘርፎች በስፋት ለመሰማራት ፍላጎቷን ገልጻለች።

ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአውሮፓ ኩባንያዎች ዘንድ አዲስ የንግድ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቅሷል።

የደህንነትና የፀረ – ሽብር ትብብር

በአፍሪካ በተለይ ምሥራቁ የአህጉሪቱ ክፍል የጸጥታ እና የሽብርተኝነት ስጋት የሚስተዋልበት ነው፤ የፖለቲካ አለመረጋጋትም የአህጉሪቱ ፈታኝ ችግር ሆኗል፡፡ በዚህ ጉባዔ ታዲያ እነዚህን ችግሮች ለመዋጋት በሚያስችሉ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደነበር ተጠቁሟል። የአፍሪካ ሀገራት ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም ለመፍታት የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ጠይቀዋል። ፈረንሳይም የደህንነት ትብብሯን ለማጠናከር ፍላጎት አሳይታለች ነው የተባለው።

የአየር ንብረት ለውጥና ዘላቂ ልማት

የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ በጉባዔው በስፋት ተነስቷል። ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋና የምግብ እጥረት በብዙ የአፍሪካ ሀገራት እየተባባሱ እንደሚገኙ ተገልጿል። በመሆኑም ፈረንሳይ በንፁህ ኀይል፣ በአረንጓዴ ቴክኖሎጂና በአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክቶች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች።

ከላይ በተነሱት ነጥቦች ዙሪያ ስምምነቶች ተደርገው ነው ጉባዔው የተጠናቀቀው፤ ለስምምነቶቹ ተግባራዊነትም ፈረንሳይ በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብታለች፡፡

መደምደሚያ

በአጠቃላይ የአፍሪካ – ፈረንሳይ ጉባኤ የቀድሞ ግንኙነቶችን እንደገና ለመገምገም ወሳኝ ዕድልን ፈጥሯል። የተነሱት ሐሳቦች በተለይ እኩልነት፣ ፍትሃዊ ንግድ፣ የወጣቶች ኃይልና የራስን አቅም መጠናከር ላይ ትኩረት ያደረጉ ነበሩ። የፈረንሳይ አዲስ አቀራረብ በተግባር ከታዬ እና የአፍሪካ ሀገራትም የራሳቸውን አቅም ካጠናከሩ፣ ወደፊት የተሻለ እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደሚገነባ ዕምነት ተጥሎበታል።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የግንባት 10  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here