ፓርቲዎች ስለገጠር ልማት ምን አሉ?

0
95

ኢትዮጵያ ለ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ እየተዘጋጀች ነው፤ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው የመጨረሻው ምዕራፍ ላይም ትገኛለች፡፡ በዚህ ዕትም አዴኃን፣ ኢዜማ እና ብልጽግና ፓርቲዎች በግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲዎች ላይ ያቀረቡትን የፖሊሲ አማራጭ በእጣቸው መሠረት አዘጋጅተነዋል፡፡

በቅድሚያ የኢትዮጵያ  ዴሞክራሲያዊ ሕዝብ ንቅናቄ (ኢዴኃን) ተወካይ  አቶ አዲሱ ጉልላት የግብርና እና ገጠር ልማት  ፖሊሲን በተመለከተ የፓርቲውን የፖሊሲ አማራጭ አቅርበዋል፡፡  አቶ አዱሱ “ግብርና የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው” ብላዋል፤ በኢትዮጵያ 80 በመቶው ሕዝብ በግብርና ቢተዳደርም ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ከማደግ ይልቅ ውድቀት እንደገጠመው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የግበርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲው ውድቀት ማሳያ መሆኑን  ፓርቲያቸው  መገምገሙን ጠቁመዋል፡፡

ለውድቀቱ ምክንያት ያሏቸውም የመሬት ባለቤትነት  ጥያቄ እና ዋስትና ማጣት፣ የእርሻ መሬት አነስተኛ መሆን እና የግብርና ግብዓት ሥርጭት ችግር፣ የገበያ ትሥሥር አለመፈጠር እንዲሁም  የመሠረተ ልማት እጥረት ናቸው፡፡

መሬት የመንግሥት እና የሕዝብ በመሆኑ አርሶ አደሩ ሙሉ ዕምነት እንዳይኖረው መደረጉንም አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በመሬቱ ብድር ማግኘት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ይህን ተከትሎም አርሶ አደሩ ቋሚ ተክሎችን ማልማት እና የመሬቱን ለምነት ለመጠበቅ መቸገሩን አንስተዋል፡፡ በዚህም አርሶ አደሩ ግብርናውን ማዘመን አልቻለም፡፡

እንደ ፖርቲው ዕምነት ተደጋጋሚ የሕግ ለውጥ መደረጉ ያልተፈለገ ውጤት ያመጣል፡፡

ለምሳሌ በግለሰቦች እና በባለሀብቶች ላይ አለመረጋጋትን እና ግራ መጋባትን ይፈጠራል፡፡

በተደጋጋሚ የሚቀያየሩ ሕጐች እርስ በርስ እንዲቃረኑም ያደርጋል፡፡ ምርታማነትንም ማሳደግ አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ የውኃ ሀብት ቢኖራትም ግብርናው አሁንም ድረስ በዝናብ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑንም የፓርቲው ተወካይ አንስተዋል፡፡ በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ በሚኖር ጊዜ ግብርናው ክፉኛ ይጐዳል፡፡ አሁን ያለው የመስኖ ልማትም በፖሊሲ ደረጃ እንጅ በተግባር ዝቅተኛ በመሆኑ  የአርሶ አደሩ ሕይወትም አለመቀየሩን አንስተዋል፡፡

ተወካዩ እንዳሉት በሀገሪቱ የሕዝብ ብዛት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱም የአርሶ አደሩ ማሳ የተበጣጠሰ በመሆኑ በትራክተር ለማረስና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም አያስችልም፡፡

ችግሩን በአማራ ክልል ለመፍታትም መንግሥት ምንም ሲሠራ አለመታየቱን አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦትም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በመሆኑ ውድድር እንዳይፈጠር አድርጓለ፡፡

በዚህም ጥራቱን የጠበቀ ግብአት በወቅቱ እንዳይቀርብ ዋጋውም ከአቅም በላይ ማደጉን አንስተዋል፡፡ ፓርቲያቸው በምርጫው ቢያሸንፍ የተጠቀሱትን ችግሮች እንደሚፈታ ጠቁመዋል፡፡

የኢዜማ ተወካይ አቶ ይበልጣል አድማሴ በበኩላቸው የገብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲን በተመለከተ አማራጭ ፓሊሲያቸውን አቅርበዋል፡፡ ፓርቲው ግብርና እና ገጠር ልማት የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት ብቻ ሳይሆን የዜጎች የሉዓላዊነት እና የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ፓርው እንደሚያም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ተወካዩ ማብራሪያ ግብርና እና ገጠር ልማት ማለት በሁሉም የግብርና ዘርፎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ በተበጣጠሰ ማሳ አምርቶ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደማይቻልም ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

የምግብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠውም የዜጐች ኑሮ በተግባር ሲለወጥ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢዜማ ግብርና እና ገጠር ልማትን ከውድቀት ለመታደግ የፖሊሲ ርምጃዎችን ይወስዳል ብለዋል፡፡  እንደ እርሳቸው ገለጻ አርሶ አደሩ በከተማ ለመኖር ቢፈልግም መሬቱን እነጠቃለሁ በሚል ስጋት በቁራሽ መሬት ታግቶ ተይዟል፡፡

ችግሩን ለመፍታ እና ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፤ እንደ ተወካዩ ማብራሪያ ያለመሬት ባለቤትነት የምግብ ዋስትና ሊታሰብ አይችልም፤ ይህን ለመፍታት ፓርቲው ገበሬው መሬቱን ሸጦ ወደ ከተማ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ ሰፋፊ እርሻ ለማልማት አቅመ ያላቸውን በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ያደርጋል፡፡ ገበሬውም በአቅራቢያ ባሉ ከተሞች የመኖሪያ ቦታ እንዲያገኝ እና የሥራ እድል እንዲፈጠርለት ምቹ ሁኔታን ይፈጠራል፡፡

ኢዜማ በአግሮ ኘሮስሲንግ፣ በከብት እርባታ፣ በኢንዱስትሪዎች እንዲሰማሩ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የብልጽግናና ፓርቲ ተወካይ አቶ ደረጄ ማንደፍሮበበኩላቸው ቀደም ባሉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ከሞፈርና ቀንበር እርሻ፣ ከዝናብ ያልተላቀቀ ነበር፡፡

ለእንስሳት ዘርፍ ትኩረት ያልሰጠ፣ የምርት ዕድገት የማይታይበት፣ የተፈጥሮ ሀብቱ የተራቆተና የተጎሳቆለ እንደ ነበር አውስተዋል፡፡ በዚህም ዜጐች ከድህነት ሳይላቀቁ ቆይተዋል፡፡

ሆኖም ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ሰባት ዓመታት ቃል ኪዳኑን በተግባር በመለወጥ ውጤት አሳይቷል ብለዋል፡፡

ተወካዩ እንዳሉት ከተረጅነት ወደ ሉዓላዊነት አድጓል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ዋናው የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ እሳቤ በዋናነት በምግብ ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለስንዴ ግዥ ታወጣው የነበረውን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ማስቀረት ሳይሆን ወደ ውጭ መላክ  ችላለች፡፡

እንደ አቶ ደረጄ ማብራሪያ ግብርናውን ከሞፈርና ቀንበር እንዲሁም ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በመስኖ ልማት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል፡፡ አንድም መሬት ጦም እንዳያድር በተያዛው አቋምም በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት ተችሏል፡፡ ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት አነስተኛ   ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በከልሉ ኩታ ገጠም እርሻን 52 በመቶ ማድረስም ተችሏል፡፡

ሜከናይዜሽንና የግብርና ግብዓት አቅርቦትን በተመለከተም ብልጽግና ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ግብርናው የሰውን ጉልበት፣  ጊዜ ከሚያባክነው ኋላቀር አሰራር  ተላቆ  በኮምባይነር፣ ትራክተር እና ሌሎች ዘመናዊ አራሮችን  እንዲከተል ተደርጓል፡፡

ለምርትና ምርታማነት ዕድገትም ለማዳበሪያ ግዥ ድጐማ በማድረግ አለኝታነቱን  ማረጋገጡን የፓርቲው ተወካይ ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የማዳበረያ ማምረቻ ለመገንባት የገባውን ቃል በተግባር አስመስክሯል፡፡

በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍም በመስኖ፣ በእንስሳት ጤና መሻሻል  ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡  አደረጃጀቱንም በማሻሻል አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በሌማት ትሩፋትም በወተት፣ በእንቁላል ምርት በዓሳ እና በማር ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

የኢንዱስትሪ ትስስር እና የገበያ ምርት ውጤቶች ግብርናው ከቤት ፍጆታ አልፎ የውጭ ምንዛሬ ወደ ማስገኘት  ተሸጋግሯል፡፡

አርሶ አደሩን ከባለ ሀብቱ ጋር በውል እርሻ በማስተሳሰር ግብዓት በመጨመር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማምረት አርሶ አደሩ የገቢ አቅሙ ማደግ ችሏል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም ከባለፉት ሰባት ዓመታት ለዓለም ተምሳሌት የሚሆን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በአማራ ክልል የደን ልማት ከነበረበት 14 ነጥብ ስድስት በመቶ ወደ 19 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ አድጓል፡፡

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የግንቦት 17   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here