ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፎ

0
309

የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ይበልጥ ማሳደግና በየዘርፉ ያላቸውንም ተጠቃሚነት በሚገባ ማረጋገጥ እንዲቻል በተለይ ሴቶች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት እና ለዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት በሆነው የምርጫ ሂደት ውስጥ በተሟላ መንገድ በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል። በምርጫ ተሳታፊ በመሆናቸውም ሴቶች የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውንና የማህበረሰባቸውን ሕይወት በተጨባጭ ይለውጣሉ፤ ሀገርንም ወደ ፊት ያራምዳሉ፡፡ በአጠቃላይም ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አሻራ ማኖር እና የዜግነት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡

 

ይሁንና በሴቶች አመራርነት ላይ የተዛቡ አመለካከቶች መኖር፣ በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል፣ ከትምህርት ዝግጅት እና ከመረጃ አንጻር የሚታዩ ክፍተቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ በበይነ መረብ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሴቶች በሕዝብ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በቂ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ተግዳሮት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ  በመሆን ይነሳሉ፡፡

ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ያህሉን የሚሸፍኑት  ሴቶች በፖለቲካ ሂደት ውስጥ ሲሳተፉ የሚያገኙት ጥቅም ግላዊ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰባዊ ነው። ስለኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው፣ ስለነፃነት፣ እኩልነትና የሚደርሱባቸውን ጥቃቶች ስለመከላከል የሚወጡ ሕጎችና ፖሊሲዎች በትክክል የሚተገበሩት የሴቶች ድምፅ ሲኖር ነው።

 

ሴቶች በሀገራዊ ምርጫ አሸንፈው  በምክር ቤቶች ውስጥ በመሳተፍ በሀገሪቱ በጀትና ዕቅድ ላይ የራሳቸውን አሻራ ያሳርፋሉ። የተሳትፏቸው ማደግ ወጣት ሴቶች በራሳቸው እንዲተማመኑና ለሀገር ግንባታ እንዲነሳሱ ያደርጋል።

በዓለም-አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሴቶች በምርጫ መሳተፍ ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው። በፖለቲካ ውስጥ በንቃት የሚሳተፉባቸው ሀገራት ለግጭት የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣቸው የጥናት ውጤቶች ያሳያሉ።

ድርጅቱ “Women’s Full and Effective Participation and Decision-making in Public Life” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ ጥናት አስጠንቷል።ይህ ጥናት ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ሲገኙ ስላላቸው በጎ ሚና እና ስለሚያመጡት ማህበረሰባዊ ለውጥ በዝርዝር ያትታል። የሴት መራጮች ቁጥር መጨመርና በአንድ የምርጫ ዘመን በንቃት መሳተፋቸው ለቀጣዩ ትውልድ ሴቶች በፖለቲካው ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎትን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።

በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ ሲሳተፉ ደግሞ ለትምህርትና ለጤና የሚመደበው በጀት እንዲጨምር ምክንያታዊ ሀሳቦችን በማቅረብ በፖሊሲ አወጣጥ ላይ አበርክቶ ይኖራቸዋል። ይህም የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገትን ያመጣል። በሌላ በኩል በንፅፅር በሴቶች የሚመሩ ተቋማት ከሙስና የጸዱ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው።

ዩኤን ኦርግ ድረ ገፅ ያደረገው ጥናት  እንደ ሚያመላክተው ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሴቶች ከወንዶች እኩል የመምረጥ እና የመመረጥ መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ጭምር ቢያስቀምጡም በሁለቱም በኩል ያለው ተሳትፎ በቂ አለመሆኑን ነው  ያመላከተው፡፡

ድርጅቱ ሴቶቹ መብት እንዳላቸው ቢቀመጥም የሚገጥሟቸው መሰናክሎች  ምን ሊሆኑ ይቸላሉ? ብሎ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት   በማህበረሰቡ ያለው የሥርዓተ-ፆታ አመለካከት ችግር፣ በሴቶቹ በኩል ያለው  የሥነ-ልቦና እና ባህላዊ መሰናክሎች፣ ትምህርት (ዕውቀት አለመኖር)፣ ድህነት (የኢኮኖሚ ጥገኝነት)፣  የፖለቲካ ፓርቲዎች አሳታፊነት ችግር፣ ብሔረሰቦች ወይም ጎሳዎች  የመሪነት ቦታን  አብዛኛውን ጊዜ ለወንድ መሥጠት   የሚሉ ምላሾች መገኘታቸውን ጠቁሟል፡፡

በሀገራችን በ1987  በተደረገው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ 536 ወንዶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን የሴቶች ቁጥር ደግሞ 10 እንደነበር ጥናቱ አስፍሯል። በዚሁ ወቅት  ለክልል ምክር ቤቶች ደግሞ አንድ  ሺህ 355 ወንዶች በዘጠኙ ክልል ባሉ የክልል ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ማግኘት መቻላቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። በዚያው ዓመት በዘጠኙ ክልሎች መቀመጫ ያገኙ የሴቶች ቁጥር ደግሞ 77 ነበር።

ጥናቱ አስርት ዓመታትን ወደ ኋላ ሄዶ በንጉሡ አገዛዝ ዘመን ከነበረው ቁጥር ጋር ሲያነጻጸር ከ240 የፓርላማ አባላት መካከል ሁለቱ ሴቶች ነበሩ፡፡ በደርግ ጊዜ ደግሞ ከ835 የሸንጎ አባላት መካከል 14ቱ ሴቶች ነበሩ። ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ( ከአስር አመታት በኋላ) ባደረገችው ምርጫ የምክር ቤቱን መቀመጫ ማሸነፍ የቻሉት ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሻሻልን አሳይቷል። በ2007 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ሴቶች የነበራቸው ቁጥር 212 ወይም 38 ነጥብ 8 በመቶ ነበር። በክልል ምክር ቤቶች ደግሞ ሴቶች  800 ወይም  40 ነጥብ 3 በመቶ መቀመጫ አግኝተዋል፡፡

በወቅቱ በምክር ቤቶች ያለው የሴቶች ውክልና ቁጥር መሻሻል ቢያሳይም በወሳኝ ቦታዎች አለመቀመጥ እና በርካቶቹ የፓርቲዎቻቸውን ፕሮግራም ከማስፈፀም በዘለለ አጀንዳዎችን በመቅረፅም ሆነ ፖሊሲዎችን በማርቀቅ ደረጃ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ  እንደ ነበር  የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል።

በተለይም የሥርዓተ ፆታ የኀይል ሚዛን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት መዋቅራዊ የሆኑ የፖሊሲ ለውጦች ያስፈልጋሉ በሚባልበት ወቅት ሴቶች የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው መወሰን ያልቻሉበት ወቅት እንዳልነበር መረጃው አመላክቷል፡፡

ዩኤን ዲፒ ባደረገው ሌላ ጥናት ደግሞ በምርጫ ሂደቶች ውስጥ መሳተፍ ድምጽን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ተሳትፎን በተመለከተ  የመናገር፣ የመሰብሰብ እና የመሰብሰብ ነፃነትን ያስገኛል።

ከቅርብ  ዓመታት ጀምሮም  ሴቶችን የማካተት እና የማብቃት ፍላጎቶች በሁሉም መንግሥታት  እያደጉ መምጣታቸውን መረጃው አመላክቷል፡፡ ይሁንና የዴሞክራሲያዊ ፖሊሲዎች ቁልፍ እሴቶች ውስጥ የሴቶች ማህበራዊ ክፍተቶች በመሙላት ድምጽ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ በፖሊሲ አወጣጥ ሂደት ላይ እንዲሁም በማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወይም ከትምህርት ጋር ያለውን ችግር በደንብ በመረዳት  ማስገንዘብ ይጠይቃል።

የሴቶች የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቤተሰብ ውስጥ ያለው ተጽእኖ ሊካድ አይችልም.፤አንዲት ሴት ከቤተሰብ ውጪ ለራሷ ቦታ እና ድምፅ መደራደር እንድትችል ማሳየት በሰፊው ሊሠራበት የሚችል ጉዳይ እንደሆነ ያነሳው (women votres servey) ጥናት ነው፡፡  ይህ ከተደረገ በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን እና ይህ ለኔ ይገባኛል ፣ይሆነኛል የሚል ፍላጎት እና ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ መቻል፣ ሕዝባዊ ተግባር መሆኑን እና ሴቶች እኩል መሆናቸውን አጉልቶ ሊያሳያቸው ይችላል፡፡

የቢቢሲ ዘገባ ደግሞ ኢትዮጵያ በነበሯት ሕጎችም ሆነ ባህላዊ መዋቅሮች ሴቶችን በልዩነትና በበታችነት ለዘመናት ስታይ መቆየቷን አንስቷል። ለዓመታትም የነበረው ሁኔታ ሲታይ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ በመንግሥት ደረጃ የፖለቲካውን ስፍራ የተቆጣጠሩት ወንዶች እንደሆኑ ጠቁሟል።

በሀገሪቱ ማህበረሰቡን ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ሴቶችን የሚመለከቱ ሕጎችን የሚያረቁትም ሆነ የሚያስፈፅሙት ወንዶች መሆናቸውም የሕግ አውጭ ምክር ቤቱ በወንዶች ለመያዙ አስረጅ እንደሆነ ዘገባው አመላክቷል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ለምን አስፈለገ? ለሚለው የፍትሕ ጥያቄ  ግማሹን የህብረተሰብ ክፍል እንደ መያዛቸው  በውክልና ዲሞክራሲ ሴቶች በራሳቸው መወከላቸው ተገቢ መሆኑን ነው መረጃው የጠቆመው፡፡

ሌላኛው ደግሞ የሴቶችና የወንዶች የሕይወት ልምድ በተለይም ከታሪካዊ ፆታዊ ኢ-ፍትሐዊነት ጋር ተያይዞ መስተካከል ያለባቸው ሕግጋትንና አፈፃፀማቸውን ከሴቶች በላይ የሚያውቅ ስለሌለ እንደሆነም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሴቶችን በፖለቲካውም ሆነ በምርጫ እንዲሳተፉ ምርጫ ለማድረግ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦችን ማምጣት እንደሚያስፈልግ በርካቶች ይናገራሉ። የሴቶችን ድርብርብ የሥራ ጫና ከመቀነስ ጀምሮ በማህበረሰቡ ላይ ግንዛቤን መፍጠር እንዲሁም ፓርቲዎች አቃፊ እንዲሆኑ ማስቻል ከሴት ፖለቲከኞች የሚነሱ ሃሳቦች ናቸው።

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here