አግድም የተገነባው ሰማይ ጠቀስ ህንፃ

0
22

በቻይና ቾንግኪንግ ከተማ 250 ሜትር ቁመት ባላቸው አራት ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች አናት አግድም 300 ሜትር ርዝመት ያለው ሰማይጠቀስ ህንፃ መገንባቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ  ባለፈው  ሳምንት  ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በቾንግኪንግ ከተማ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ካላቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የያንግዚ እና የጂያሊንግ ወንዞች መገናኛ ላይ የሚገኘው “ክሪስታል” የተሰኘው አግዳሚ ህንፃ በሀገሪቱ ከተገነቡት ትልልቅ የኪነ ህንፃ ኘሮጀክቶች አንዱ እና ተጠቃሽ ነው፡፡

በቻይና እንዲሁም በሌሎች ሀገራት በየራሳቸው ለተገነቡበት ሀገር መለያ ሆነው ያገለግላሉ፤ “ክሪስታል” የተሰኘው አግድም የተሰራው ሰማይጠቀስ ህንፃ ግን አራት ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎችን የሚያገናኝ አግድም በመስታዉት መሰል ድንጋይ የተሰራ መሆኑ ከሌሎቹ የተለየ እንደሚያደርገው ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡

በእስያ ካሉ ትልልቅ በሪልስቴት ከተሰማሩ ኩባንያዎች አንዱ በሆነው “ካፒታላንድ” የተገነባ ሲሆን የወጣበት ወጪም አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ በግንባታው ሂደትም በጥሬ እቃ  ግብአትነት ሦስት ሺህ የመስታዉት  ክፍልፋዮች እንዲሁም አምስት ሺህ የአሉሙኒዬም ቁርጥራጮች አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡

አግዳሚው ህንፃ ሰባት ረዣዠም የብረት አቃፊ ክፍሎችም አሉት፡፡ አብዛኛዎቹም መሬት ወለል ላይ ተሰርተው በጠንቃቄ ወጥተው አናት ላይ መገጣጠማቸውን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡ የብረታብረቶቹ ክብደትም 12 ሺህ ቶን ወይም 12 ሚሊዬን ኪሎግራም መመዘኑ ነው የተረጋገጠው፡፡

አግድም የተገነባው ሰማይ ጠቀስ ህንፃ አራቱን የተሸከሙትን ህንፃዎች ከማገናኘቱ ባሻገር ቡና ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ የአትክልት ስፍራ፣ የሁነት ማቅረቢያ ቦታዎች የግል ክለቦችን እና መዋኛ ገንዳዎችንም አካቶ መያዙ በማደማደሚያነት ለንባብ በቅቷል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here