የምርጫ ታሪካችን

0
242

በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ዘመናዊ ምርጫ የተጀመረው በጥንታዊቷ ግሪክ አቴንስ ከተማ ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን (በ508 ዓ.ዓ አካባቢ) ነው። በአቴንስ ይሠራበት የነበረው ሥርዓት “ቀጥተኛ ዴሞክራሲ” ይባል ነበር። በወቅቱ ዜጎች ተወካይ ከመምረጥ ይልቅ በከተማዋ ስብሰባ ላይ በአካል በመገኘት በሕጎች እና በፖሊሲዎች ላይ በቀጥታ ድምፅ ይሰጡ ነበር። ይሁንና የመምረጥ መብት የነበራቸው ነፃ የሆኑ ወንዶች ብቻ ሲሆኑ፣ ሴቶች፣ ባሪያዎች እና የውጭ ሀገር ዜጎች የመምረጥ መብት አልነበራቸውም።

የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ከዘውድ ሥርዓት እስከ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም እና እስከ ቅርብ ጊዜው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድረስ በረጅም እና ውስብስብ ሂደቶች ውስጥ ያለፈ ነው።

ከዐፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሕዝብ ቀጥተኛ ድምፅ የሚከናወን ዘመናዊ የምርጫ ሥርዓት ጨርሶ አልነበረም ሲሉ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል። በወቅቱ የነበረው የሥልጣን ሽግግር እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ሙሉ በሙሉ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ዘውዳዊ ሥርዓቶችን ብቻ የተከተለ ነበር።

የባህላዊ ሥልጣን አመራረጥ ሥርዓት

በዚህ ዘመን ሥልጣን የሚገኘው በዘር ሐረግ ወይም በጦር ሜዳ ጀግንነት እንጂ በሕዝብ ድምፅ አልነበረም። ንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣንን ከእግዚአብሔር ያገኘ መለኮታዊ መሪ ተደርጎ ይታመን ነበር። አዲስ ንጉሥ ወደ ሥልጣን በሚመጣበት ጊዜ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ እና የሃይማኖት መሪዎች ተሰብስበው ዕጩውን የመቀበል ወይም የመቃወም ሥልጣን ነበራቸው። ይህ ሂደት ውስን የሊቃውንት መረጣ እንጂ የሕዝብ ተሳትፎ ያለበት እውነተኛ ምርጫ አልነበረም።

የአማካሪ ምክር ቤቶች አጀማመር

በዐፄ ኃይለስላሴ (በወቅቱ ራስ ተፈሪ መኮንን) አልጋ ጠባቂነት ዘመን በ1911 ዓ.ም አካባቢ የምርጫ መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ የአማካሪ ምክር ቤቶች መቋቋም ጀመሩ። ይሁንና ይህንን ምርጫ ያከናወነው ሕዝቡ ሳይሆን ንጉሡ ራሳቸው ነበሩ። ከደጃዝማቾች፣ ከመኳንንቱ እና ከባላባቶች መካከል የፈለጓቸውን ግለሰቦች በአማካሪነት መርጠው የዘውድ ምክር ቤት አቋቋሙ።

ባህላዊ የዴሞክራሲ ሥርዓቶች

በሀገሪቱ ማዕከላዊ የዘውድ ሥርዓት ውስጥ ዘመናዊ ምርጫ ባይኖርም፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የራሱ የሆነ የገዳ ሥርዓት ይሠራበት ነበር። በዚህ ሥርዓት መሪዎች ወይም አባ ገዳዎች በየስምንት ዓመቱ በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ እና በምርጫ ሥርዓት ይለወጡ ነበር። ይሁንና ይህ ሥርዓት በወቅቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን መያዣ መንገድ ሆኖ አያገለግልም ነበር።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ-መንግሥት ወጥቶ፤ የመጀመሪያው የፓርላማ ተወካዮች ስብስብ የተመሠረተው በ1924 ዓ.ም በዐፄ ኃይለስላሴ ዘመን ነው። ከዚህ ዓመት በፊት የነበረው የታሪክ ክፍል ሙሉ በሙሉ በባህላዊ የሹመት ሥርዓት ላይ ብቻ የተመሰረተ ነበር።

የዘውድ ሥርዓት እና የመጀመሪያው ምርጫ (ከ1924 – 1966)

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በ1924 ዓ.ም በታሪክ ተዋወቀ። ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት በንጉሡ እና በባላባቶች እንጂ በሕዝብ ቀጥተኛ ድምፅ አልነበረም።

የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት በ1948 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን የመጀመሪያውን ቀጥተኛ የፓርላማ ምርጫ መብት ፈቀደ።

በ1949 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ሕዝባዊ ምርጫ ተካሄደ። ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች በሙሉ የመምረጥ መብት አገኙ። በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልነበሩም። ዕጩዎች በግል ይወዳደሩ ነበር። መመዘኛው የንብረት ባለቤትነት እና የትምህርት ደረጃ ላይ ያተኩር ነበር። በዚሁ ሥርዓት እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ አምስት አጠቃላይ ምርጫዎች ተካሂደዋል።

የደርግ ሥርዓት እና የአንድ ፓርቲ ምርጫ (ከ1967 – 1983)

የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ የነበረውን ፓርላማ አፈረሰ። የኢሕዲሪ ሕገ-መንግሥት በ1979 ዓ.ም ሀገሪቱን የሶሻሊስት ሪፐብሊክ አደረጋት። በዚሁ ዓመት በ1979 ዓ.ም የብሔራዊ ሸንጎ ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ምርጫ ተካሄደ። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ብቸኛው ሕጋዊ ፓርቲ ነበር። ውድድሩ በፓርቲው አባላት ወይም በፓርቲው በተደገፉ የግል ዕጩዎች መካከል ብቻ የተገደበ በመሆኑ እውነተኛ የፖለቲካ አማራጭ አልነበረውም።

የኢሕአዴግ ዘመን ምርጫዎች (ከ1983 – 2010)

የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት በ1987 ዓ.ም ከፀደቀ በኋላ በየአምስት ዓመቱ መደበኛ አጠቃላይ ምርጫዎች መካሄድ ጀመሩ። በ1987 ዓ.ም የተካሄደውን የመጀመሪያውን አጠቃላይ ምርጫ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አልተቀበሉትም። ኢሕአዴግ እና አጋሮቹ አብዛኛውን የፓርላማ ወንበር በቀላሉ አሸነፉ።

በ1992 ዓ.ም በሁለተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጥቂት ተቃዋሚዎች ቢሳተፉም ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ አብዛኛውን ወንበር በበላይነት ወሰደ።

የ1997 ዓ.ም ሦስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ እና የፖለቲካ መነቃቃት የታየበት እንደነበር “የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ፣ ፈተናዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች” ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በጻፉት መጽሐፍ ጠቅሰዋል። እንደ ቅንጅት እና ኅብረት ያሉ ጠንካራ ተቃዋሚዎች ተሳትፈው ነበር። ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ መቶ በመቶ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ወንበር አሸነፉ። ከምርጫው ማግስት የውጤት ማጭበርበር ክሶች ተነስተው በተከሰተ ግጭት የብዙ ዜጎች ሕይወት አለፈ፤ የፖለቲካ መሪዎችም ታሰሩ።

የ2002 እና የ2007 ዓ.ም ምርጫዎች ላይ ከ1997 ቀውስ በኋላ የነፃነት ምኅዳሩ ጠበበ። በአራተኛው ምርጫ ተቃዋሚዎች አንድ ወንበር ብቻ ሲያገኙ በአምስተኛው ምርጫ ኢሕአዴግ እና አጋሮቹ 100 በመቶ ሁሉንም የፓርላማ ወንበሮች ማሸነፋቸውን አወጁ። ይህ ውጤት በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሮ ለ2010 ዓ.ም የሥርዓት ለውጥ መንስኤ ሆነ።

የሪፎርም ምዕራፍ እና ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ (2013)

በ2010 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ የምርጫ ሥርዓቱን ለማሻሻል በርካታ እርምጃዎች ተወሰዱ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ተቋም ሆኖ እንደገና ተደራጀ። የቀድሞ የፖለቲካ እስረኛ እና ተቃዋሚ መሪ የነበሩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ቦርዱን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ ተሾሙ።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ዘግይቶ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ተካሄደ።

ገዥው የብልጽግና ፓርቲ፣ የዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና ሌሎች በርካታ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። የብልጽግና ፓርቲ አብዛኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር በማሸነፍ አዲስ መንግሥት መሰረተ። ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ የቴክኒክ ዝግጅት የነበረው ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ፍጹም እንዳልነበር ገልጸዋል።::

ሳምንቱ በታሪክ

ማጀቴ እና ካራቆሬን ያፈራረሰው አደጋ

የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ግንቦት 24 ቀን 19 53 ዓም ተከሰተ፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት የጂኦሎጂካል ክስተቶች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ታሪካዊ ክስተት ነው።  በሬክተር ሚዛን ከ6 ነጥብ 5 እስከ 6 ነጥብ 6 የሚደርስ ከፍተኛ ኃይል ነበረው። አደጋው ማዕከል ያደረገው በሰሜን ሸዋ በኤፌሶን ወረዳ ስር በሚገኙት የማጀቴ እና የካራቆሬ አካባቢዎች ላይ ነበር። ዋናው የመሬት መንቀጥቀጥ ከመከሰቱ በፊት ከግንቦት 11 ቀን 1953 ዓ.ም ጀምሮ ትናንሽ ንዝረቶች ይሰሙ ነበር።  ዋናው አደጋ ካለፈ በኋላም እስከ ጳጉሜ 1953 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥሉ በርካታ የድኅረ-ንዝረቶች ተመዝግበዋል። በአደጋው ምክንያት የማጀቴ ከተማ ሙሉ በሙሉ ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረች ሲሆን በካራቆሬ ከተማ ደግሞ አብዛኞቹ በድንጋይ እና በኮንክሪት የተገነቡ ዘመናዊ ሕንፃዎች እና መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል። የሚገርመው የታሪክ እውነታ ግን በጭቃ እና በባሕር ዛፍ ማገር የተሠሩት ባህላዊ የኢትዮጵያ ጎጆዎች ንዝረቱን የመለጠጥና የመቋቋም አቅም ስለነበራቸው ሳይፈርሱ መቆየታቸው በወቅቱ የነበሩ የጂኦፊዚክስ ተመራማሪዎችን አስገርሟል። በዚህ ድንገተኛ አደጋ ሳቢያ ከበርካታ መቶዎች በላይ ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የብዙ ዜጎች ሕይወትም አልፏል።

አደጋው ያስከተለው የመሬት መሰነጣጠቅ እና የድንጋይ ናዳ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሰሜን የሚወስደውን ዋና  መኪና መንገድ እና በርካታ ድልድዮችን ለአንድ ሳምንት ያህል ሙሉ በሙሉ ዘግቶት ቆይቷል። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከሉ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ 200 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ቢሆንም ንዝረቱ ግን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በኃይል ተሰምቶ ነበር።

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን 1953 እትም

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here