ምርጫ ለተረጋጋ  ሕዝብና ሀገር፤ እንዲሁም ለፀና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ነው

0
185

ዴሞክራሲን በተግባር የገለጡ ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን “የምርጫ ወረቀት ከጥይት ይበልጣል፤ ምርጫ ደግሞ የሕዝብ ነው” ብለው ነበር የምርጫን ሚና የገለጹት።

ምርጫ የዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን በማንሳትም ዴሞክራሲ የሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ የሆነ መንግሥት መገለጫ ስለመሆኑ ነው በወቅቱ ያስተጋቡት።

ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ እንደተቀመጠው በሃገራችን ሃገራዊ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይካሄዳል። በዚህ መሠረትም ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጩ ለሚፈልገው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ድምጹን በመስጠት ፍጻሜውን አግኝቷል። በቀጣይ ቀናት ደግሞ የመጨረሻው ውጤት ይፋ የሚደረግ ይሆናል።

ጠቅላላ ምርጫውን በተመለከተም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መራጮች ሐሳባቸውን አጋርተውናል። በኩር በባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ ጣቢያዎች ተንቀሳቅሳ የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ቃኝታለች።

ሐሳባቸውን ያካፈሉን የከተማዋ ነዋሪ መራጮች እንደተናገሩት ከምርጫው በፊት በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች የተደረጉ የምርጫ ክርክሮችን ተከታትለዋል። ይህም በመረጃ ላይ ተመሥርተው የሚበጃቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ አስችሏቸዋል።

መራጮቹ እንዳሉት በምርጫ ካርዳቸው ድምጽ የሰጡት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ሊያሸንፍም፣ ሊሸነፍም ይችላል። ይህ ደግሞ የምርጫ ባሕሪ ነው። በመሆኑም የሕዝብን ድምጽ መሠረት በማድረግ ይፋ የሚሆነውን አሸናፊ በመቀበል በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።

በተለይ የኑሮ ውድነቱ ነዋሪውን እየፈተነ መሆኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ አሸናፊው ፓርቲ ትኩረት ሊያደርግበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከምርጫ መልስ ሐሳቧን ያካፈለችን የባሕር ዳር ከተማ ወጣት “የመረጥኩት ፓርቲ ቢያሸንፍ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እና የትምህርት ጥራት ላይ እንዲሠራ እፈልለሁ” ስትል ተናግራለች። ሌላኛዋ ሐሳባቸውን ያካፈሉን መምህርትም “አሸናፊው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በተለይ በትምህርት ዘርፍ ላይ ውጤታማ ለውጥ እንዲያመጣ እጠብቃለሁ” ብለዋል።

ከአረጋውያን ሐሳባቸውን ያካፈሉን የ72 ዓመቷ ዓመት የእድሜ ባለፀጋ እማሆይ ስንታየሁ አያሌው ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች እንደተሳተፉና “ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላሟ እንዲበዛ፣ ዜጎቿም በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ እመኛለሁ። ጸሎትም አደርጋለሁ” ብለዋል።

ሌሎችም አስተያየታቸውን በስልክ ያጋሩን የቻግኒ፣ ደብረ ታቦር፣ ፍኖተ ሰላም፣ ወልዲያ፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ከተማ መራጮችም ተመሳሳይ ሐሳብ ነው ያነሱት።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ስለፖለቲካ ፖርቲዎች ፖሊሲ ግንዛቤ እንዳገኙ የተናገሩት መራጮች ይህም በመረጃ ላይ ተመሥርተው የሚበጃቸውን ለመምረጥ እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።

መራጮቹ እንዳሉት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ ነገሮችን ለማከናወን ለሕዝቡ ቃል ይገባሉ። ይህንን ቃላቸውን ከምርጫ ማግስት ለቃላቸው ታማኝ በመሆን መፈጸም ይገባቸዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድርና እና በባሕር ዳር ከተማ  የክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ አረጋ ከበደ  የጸና መንግሥት ለመመሥረት ምርጫ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።

በርካታ መራጭ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሲጓዝ መመልከታቸውን ያነሱት አቶ አረጋ ይህም ሕዝቡ ለምርጫው ከፍተኛ ትኩረት ስለመስጠቱ እንደማሳያ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ “በሀገራችን እንዲህ አይነት የምርጫ ሂደትን መመልከት የዲሞክራሲ መገለጫ ነው፤ ይህም ዴሞክራሲን ይበልጥ እንዲዳብር ያደርጋል” ነው ያሉት፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳብራሩት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ ያለበትም በሕዝብ ድምፅ ነው።

በባሕር ዳር ከተማ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የሆኑትምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው “ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ሲመርጥ በማየቴ ደስ ብሎኛል። ውጤቱ ምንም ይሁን የአሸናፊውን ድምጽ እናከብራለን፤ ዋና ትኩረታችን ሃገር ግንባታ ላይ ነው” ብለዋል።

የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚጠነክረው በዜጎች ንቁ ተሳትፎ  መሆኑን በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አበራ ታደሰ ይናገራሉ። መምህሩ እንዳብራሩት፣ ምርጫ ዜጎች በነጻነት ድምጻቸውን የሚሰጡበት ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው። ሰላማዊ ምርጫ ደግሞ ለሀገር መረጋጋት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሕጋዊ የሥልጣን ሽግግር መሠረታዊ ነገር ነው።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ መራጩ በንቃት መሳተፉ ታዲያ “የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድን ያሳድጋል” ነው ያሉት።

በተለይም እንደ አማራ ክልል በጸጥታ ችግር ውስጥ ለቆዬ ምርጫ ገጽታን ለመቀየር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ያነሱት መምህሩ ይህም ሕዝቡ በሕግ እና በሥርዓት የሚያምን መሆኑን የሚያረጋግጥ አመላካች እንደሆነ ነው የገለጹት።

እንደ አቶ አበራ ማብራሪያ ምርጫ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት መድረክ ነው። ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ደግሞ ዜጎች በመተማመን ላይ የተመሠረተ መንግሥት እንዲመሠርቱ ያስችላቸዋል።

ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ የአፍሪካ ሕብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ተወካዮቻቸውን በመላክ ታዝበዋል፤ 59 አባላት ያሉት የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ የተመራ ነው።

በሀገር ውስጥ የተደራጁ 55 ሲቪክ ማኅበራት ደግሞ ከምርጫ ቦርዱ ፈቃድ አግኝተው ምርጫውን ታዝበዋል፤ እነዚህ የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች አንድ ሺህ 562 የምርጫ ታዛቢዎችን አሰማርተዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 871  መራጮች ተመዝግበዋል። ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ደግሞ 42 ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በዚህ ሂደትም 10 ሺህ 438  የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች  80  የግል ዕጩዎች ተወዳድረዋል። መራጩ ህዝብም  ይበጀኛል የሚለውን ወጥቶ መርጧል፡፡

 

(ጌትሽ ኃይሌ እና መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here