ታላቁ የእግር ኳስ ድግስ

0
242

እ.አ.አ በ1930 በፈረንሳዊው ጁልስ ሪሜት አነሳሽነት በ13 ሀገራት በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ኡራጓይ የተጀመረው የዓለም ዋንጫ ዛሬ ዘጠኝ ዐስርት ዓመታትን ተሻግሮ የዓለም ትልቁ የሰው ልጆች መሰባሰቢያ መድረክ ሆኗል፡፡ በወቅቱ ኡራጓይ አርጀንቲናን አሸንፋ የመጀመሪያውን ዋንጫ ስታነሳ ውድድሩ በዚህ ልክ ያድጋል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዓለም ዋንጫ በየአራት ዓመቱ የሚከናወን፣ የሀገራት ክብር እና ማንነት የሚገለጽበት ትልቅ መድረክ መሆኑን የፊፋ ዶት ኮም መረጃ አስነብቧል፡፡

ዓለም እስካሁን ካየቻቸው የዓለም ዋንጫዎች ሁሉ የዘንድሮው የተለየ እንደሚሆን መረጃው ያስነብባል፡፡ ለረጅም ዓመታት በ32 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ብቻ ሲደረግ የቆየው ይህ ግዙፍ የእግር ኳስ መድረክ በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ወደ 48 ከፍ ብሏል፡፡ የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በሦስት ሀገራት ጥምረት የሚዘጋጀው፡፡ ውድድሩ ለ39 ተከታታይ ቀናት ሲከናወን ውድድሩ በ16 ከተሞች 104 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡

ሜክሲኮ ይህንን ውድድር ለሦስተኛ ጊዜ በማስተናገድ የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን በካናዳ ምድር ሲደረግ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሆን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያስነብባል፡፡ ከቀደሙት ሁሉ ይደምቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የመክፈቻ ስነ ስርዓት የፔሌ እና የማራዶና ታሪክ በተጻፈበት የሜክሲኮው አዝቴካ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡ የፍጻሜው ጨዋታ በኒውጀርሲ ሜትላይፍ ስታዲየም እንደሚካሄድ አወዳዳሪው አካል አሳውቋል፡፡

አሜሪካ ከአጠቃላዩ 104 ጨዋታዎች ውስጥ 80 ያህሉን ታስተናግዳለች፡፡ በውድድሩ 48 ሀገራት መሳተፋቸው የውድድሩን ቅርጽ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል፡፡ ቡድኖቹ በ12 ምድቦች ተከፍለው በእያንዳንዱ ምድብ አራት ቡድኖች የሚፎካከሩ  ይሆናል፡፡ ከየምድቡ አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ምርጥ  ሦስተኛ ደረጃን የሚይዙ ስምንት ብሄራዊ ቡድኖች የጥሎ ማለፉን ዙር ይቀላቀላሉ፡፡

ብራዚል እስካሁን አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ሀገር ናት፡፡ ጀርመን እና ጣልያን እኩል አራት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ታሪክ የተጋሩ ሀገራት ናቸው፡፡ በዚህ የዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት ቁጥርም ጨምሯል፤ ቁጥሩ ከአምስት ወደ ዐስር ከፍ ብሏል፡፡  ለዓመታት የቆየውን የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ የበላይነት በመስበር አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ሰፊ በር ከፍቷል፡፡ የቡድኖች ቁጥር መጨመር ለአፍሪካ እና ለእስያ ሀገራት ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል፡፡

ፊፋ ከዚህ ውድድር 11 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደጋፊዎች በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታዎችን እንደሚታደሙ ይገመታል፡፡

በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ሀገራት ይሳተፋሉ፤ ኬፕ ቨርዴ ፣ ኩራሳኦ፣ ጆርዳን እና ኡዝቤኪስታን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የመሳተፍ ህልማቸውን ያሳኩ ሀገራት ናቸው፡፡

የ2026ቱን ዋንጫ ያነሳሉ ተብለው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል ስፔን ቀዳሚዋ ናት፡፡ በላሚን ያማል እና በኒኮ ዊሊያምስ የሚመራው የወጣት ተጫዋቾች ስብስብ  የዩሮ 2024 ሻምፒዮና መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ኪሊያን ምባፔን የያዘው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫዎች ፍጻሜ መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ልምዱን  በመጠቀም ዋንጫውን  ለማንሳት ትልቅ ግምት የተሰጠው ሌላኛው ብሄራዊ ቡድን ነው፡፡ በአሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል የሚመራው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንም ለ60 ዓመታት የራቀውን ዋንጫ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ከስፔን እና ፈረንሳይ ቀጥሎ ግምት አግኝቷል፡፡

የደቡብ አሜሪካ ኃያላን የእግር ኳስ ሀገራት ብራዚል እና አርጀንቲናም የዋንጫ  ግምት የተሰጣቸው ሌሎች ሀገራት ናቸው፡፡ ብራዚል በቪኒሲየስ ጁኒየር መሪነት ስድስተኛውን ዋንጫዋን ለማግኘት ያላት ጉጉት እና  የተጫዋቾች ጥራት ግምት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ የወቅቱ የዓለም እና የኮፓ አሜሪካ ሻምፒዮኗ አርጀንቲና ክብሯን ለማስጠበቅ በቀላሉ እጅ እንደማትሰጥ ይገመታል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ  ምናልባትም የመጨረሻው የዓለም ዋንጫው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ምርጥ ስብስበ ያላት ፖርቹጋልም ዋንጫውን ያነሳሉ ተብለው ከፍተኛ  ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት ውስጥ ትገኝበታለች፡፡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶም የመጨረሻው ተሳትፎው እንደሚሆን የፊፋ ዶት ኮም መረጃ አመልክቷል፡፡

የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር መጨመር ፊፋ እና አስተናጋጅ ከተሞች ከቲኬት ሽያጭ፣ ከቱሪዝም እና ከስፖንሰርሺፕ ከፍተኛ ገቢ ያገኛሉ ተብሏል፡፡ በ16ቱም ከተሞች ዘመናዊ የአየር አውሮፕላን ማረፊያ እና የመጓጓዣ መሰረተ ልማት መገንባት ደጋፊዎች በሦስቱም ሀገራት  በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ያስችላቸዋል፡፡

ስታዲየሞቹም በአብዛኛው የአሜሪካ እግር ኳስ (NFL) የሚከናወንባቸው ግዙፍ እና ምቹ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ ይህ ሁሉ ዝግጅት የዓለም ዋንጫን ከጨዋታነት ባለፈ ወደ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የቲያትር መድረክ ይቀይረዋል ይላል የፊፋ ዶት ኮም መረጃ፡፡

ብራዚል ሁሉንም የዓለም ዋንጫዎች የተሳተፈች ብቸኛ ሀገር በመሆን ቀዳሚ ሀገር ናት፡፡ ጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎዝ በ16 ግቦች የዓለም ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ  ሆኖ  በታሪክ  መዝገብ  ላይ   ሰፍሯል፡፡

ፈረንሳዊው ጀስት ፎንቴን እ.አ.አ በ1958ቱ የውድድር ዘመን ብቻ 13 ግቦችን በማስቆጠር በአንድ ውድድር ብዙ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች በመሆን ክብረ ወሰኑን ይዟል፡፡ ኤል ሳልቫዶር በሀንጋሪ ዐስር ለአንድ የተሸነፈችበት ታሪክ በታሪካቸው ከፍተኛ ሽንፈት ካስመዘገቡ ጥቂት ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች፡፡  እስካሁን በተከታታይ የዓለም ዋንጫን በማንሳት ጣሊያን እና ብራዚል  በታሪክ መፃህፍት ተመዝግበዋል፤ ይህንን ታሪክ ለመድገም አርጀንቲና በ2026 ከፍተኛ ትግል ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።

ብራዚል ከ1930 እ.አ.አ ጀምሮ እስካሁን የተደረጉትን ሁሉንም የዓለም ዋንጫዎች (22 ጊዜ) በመሳተፍ ብቸኛዋ ሀገር ናት፡፡ አንቶኒዮ ካርባሃል፣ ሉተር ማቲያስ፣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ በአምስት የተለያየ የዓለም ዋንጫዎች በመሳተፍ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ ጀርመናዊ አጥቂ ሚሮስላቭ ክሎዝ በዓለም ዋንጫ ታሪክ 16 ግቦችን በማስቆጠር ባለክብረወሰን ነው፡፡ ፈረንሳያዊው ጀስት ፎንቴን ደግሞ በአንድ የዓለም ዋንጫ (እ.አ.አ በ1958) ብቻ 13 ግቦችን በማስቆጠር ባለክብረወሰን ነው፡፡

ካናዳ፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ቶጎ በዓለም ዋንጫ ታሪክ አንድም ጨዋታ ያላሸነፉ ሀገራት ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ታሪክ አንድም ግብ ያላስቆጠሩ ሀገራት ጭምር ናቸው፡፡ በተለይ ሆንዱራስ በዘጠኝ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፋ አንድም ጨዋታ ያላሸነፈች ብቸኛዋ ሀገር ስትሆን ሦስት ግቦችን ማስቆጠሯን ግን የፊፋ ዶት ኮም መረጃ አመልክቷል፡፡

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር የተሻለ መድረክ  እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡  ከፊል አውቶማቲክ የኦፍሳይድ ቴክኖሎጂ እና የተሻሻሉ የቪዲዮ ረዳት ዳኞች (VAR) ስህተቶችን ለመቀነስ በሥራ ላይ ይውላሉ ተብሏል፡፡ እያንዳንዱ ቡድን 26 ተጫዋቾችን ይዞ ወደ ሜዳ እንዲገባ የሚፈቀድ ሲሆን ይህም ለአሰልጣኞች ሰፊ የቅያሪ አማራጭ እድል ይሰጣል፡፡ በሰሜን አሜሪካ ሰማይ ስር የሚካሄደው ይህ ታላቅ የእግር ኳስ ድግስ ከመዝናኛነት ባለፈ የሰው ልጅን አንድነት፣ የባህል ልውውጥን እና የስፖርታዊ ጨዋነት መንፈስ ለዓለም የሚታይበት ትልቅ መድረክ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 1   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here