የጦርነት ዳፋ

0
264

በጦርነት አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ የለም፤ የመጨረሻ ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ ያደጉትንም ይሁን ተዳጊ ሀገራትን ያሽመደምዳል፡፡

ዓለም ዐቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር እንደገለጸው በግጭት እና በጦርነት ውስጥ ያለፉ ሀገሮች ብዙ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገሩ በርካታ ጠባሳዎች ይኖሯቸዋል፡፡ ጦርነቱ ቢቆም እንኳ ሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት፣ የትውልድ ክፍተት፣ መርዛማ አካባቢ መፈጠር እና የመሬት መራቆት እንዲሁም የሕብረተሰብ መዋቅሮች መሰባበር ያጋጥማቸዋል፡፡ የመሠረተ ልማት እና ኢኮኖሚ ላይ የደረሰ ኪሳራን ለመመለስ በርካታ  ዐሥርት ዓመታት ሊያስፈልጋቸውም  ይችላል፡፡

ለአብነትም በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ ግጭቶች  ምክንያት በክልላዊ የኃይል አውታሮች፣ በነዳጅ መሠረተ ልማቶች እና ወደቦች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ወሳኝ የሀገር ውስጥ ምርትን ሽባ በማድረግ ዋና የገቢ ምንጮችን አቋርጧል፡፡ ለአብነትም  20 በመቶ ያህሉ የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ የባሕር ዳርቻ መዘጋት ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓትን አስተጓጉሏል፡፡ ዓለም አቀፋዊ የጭነት እና የኢንሹራንስ ወጪዎችን ከፍ አድርጓል፣ የረጅም ጊዜ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት ምክንያትም ሆኗል፡፡ በየሀገራቱ ውስጥ ንግዶች እንደልብ እንዳይሳለጡም አድርጓል፡፡

ተቋማዊ ውድቀት የደረሰባቸው እንደ ሱዳን፣ ሶሪያ እና አፍጋኒስታን የመሳሰሉ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሀገራትም ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ምርት መቀነስ እና በከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዲሰቃዩ ምክንያት ሆኗል፡፡

ጦርነት የወጣቶችን መሠረታዊ ዕድሎችን በመግፈፍ የሀገርን የወደፊት የሰው ኃይል ውጤታማነት ያደናቅፋል፡፡ በተጨማሪም ጦርነቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በማፈናቀል በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን አውድመዋል፡፡ ለአብነትም  ሴቭ ዘ ችልድረን መጋቢት ላይ (2026) ባወጣው መረጃ በመካከለኛው ምሥራቅ  ክልል ውስጥ ያለው ግጭት ቢያንስ 52 ሚሊዮን ለትምህርት የደረሱ ሕፃናትን ከትምህርት ገበታቸው ለይቷቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው እስራኤል በጋዛ ላይ በፈጸመቻቸው ወታደራዊ ዘመቻዎች በግዛቱ የነበሩ 78በመቶ የሚጠጉ ሕንፃዎች ወድመዋል፤ ወደ 92በመቶ የሚጠጉ የመኖሪያ ሕንፃዎችም  ተጎድተዋል፡፡ ግዛቱ በ53 ሚሊዮን ቶን በሚገመት ፍርስራሽም ተሸፍኗል፡፡

 

በጦርነቶች ሆን ተብሎ ወይም በስህተት የሚደርሰው የጤና ተቋማት  ውድመት ሀገራትን  ሥር ለሰደዱ  በሽታዎች፣ ለጨቅላ ሕፃናት ሞት መጨመር እና መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ፈጣን ስርጭት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡

በአፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያ ላይ የተካሄደው የምዕራባዊያን የጦር ዘመቻ የጦርነት አስከፊ ጠባሳን ከሚያሳዩ ጦርነቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2011 በአሜሪካ የበላይነት እንደሚዘወር የሚነገርለት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጣልቃ ገብነት ምክንያት ሀገሪቱን ለ42 ዓመታት የገዟት ፕሬዝዳንት ሙአመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ከባድ የሥርዓት ውድመት ገጥሟታል፡፡

በደረሰባት የጦር መሳሪያ ድብደባም ሀገሪቱ የተከፋፈለች እና ተቋማቷ የማስፈጸም አቅማቸው ደካማ ሆነዋል፡፡ በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገችው ሀገር ከደረሰባት ፍጹም ጭካኔ የተመላው የቦንብ ድብደባ በኋላ ብሄራዊ አንድነቷ ፈራርሷል፡፡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድመት ድርሶባታል፤ በየጊዜው የሰዎች ሞት የሚከሰትባት እና አስከፊ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀውስ ውስጥ እንድትገኝ ሆናለች ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ሌላዋ ከጦርነት በኋላ ከባድ ጠባሳ የደረሳባት ሀገር ቬትናም ናት፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው አሜሪካ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በደቡብ ምሥራቅ እስያ የኮሚኒዝም መስፋፋትን ለማስቆም ጣልቃ ገብታለች፡፡ በዚህም ከቬትናም ጋር ጦርነት ገጥማለች፡፡ በቬትናም እና በአሜሪካ የተደረገው  ጦርነት  ካበቃ ከ50 ዓመታት በላይ ቢሆንም  ቬትናም ሊቀለበስ የማይችል የአካባቢ ውድመት አጋጥሟታል፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር በ1962 እና 1971 መካከል የአሜሪካ ጦር  በቬትናም ወደ 19 ሚሊዮን ጋሎን የሚጠጋ ዲዮክሲን የሚባል መርዛማ ፀረ አረም ኬሚካል በመርጨቱ  መርዛማው ብክለት በቋሚነት የስነ-ምህዳር ለውጥ አስከትሏል፡፡ አሜሪካ ይህንን መርዛማ ኬሚካል የተጠቀመችው ለቬትናም ወታደሮች ሽፋን የሚሰጡ ጥቅጥቅ ያሉ የጫካ ቅጠሎችን ለማርገፍ እና  የምግብ ሰብሎችን ለማጥፋት ነበር፡፡ በዚህም ከሦስት ሚሊዮን በላይ ቬትናማዊያን ከባድ የጤና እክል አጋጥሟቸዋል፡፡  ዘገባው እንዳመላከተው ከፍተኛ የካንሰር እና የመንቀሳቀስ እክሎች እና የወሊድ ጉድለቶችን ወደ ሦስተኛው እና አራተኛው ትውልድ አምጥቶባቸዋል፡፡

በቬትናም ገጠራማ ሰፋፊ አካባቢዎች በተቀበሩ ፈንጂዎች እና ባልፈነዱ ቦምቦች ተሞልተዋል፡፡ ይህም  ለም መሬቶችን ሙሉ በሙሉ ለእርሻ እንዳይውሉ አድርጎቸዋል፡፡ የተቀበረው ፈንጂም ከዓመታት በኋላ የሞት እና የአካል ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል፡፡

የቢቢሲ ዘገባ እንዳመላከተው እ.አ.አ በ1945 በጃፓን ላይ የተጣሉት ሁለቱ የኒውክሌር ቦምቦችም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለው የአካል ጉዳት ያደረሱ ሲሆን ጉዳታቸው ዛሬም ድረስ ይታያል፡፡ እ.አ.አ በ1945 መጨረሻ ላይ የቦምብ ጥቃቱ በሂሮሺማ 140 ሺህ እና በናጋሳኪ 74 ሺህ ሰዎችን ገድሏል፡፡ ከተገደሉት መካከል 38 ሺህ ያህሉ ሕጻናት እንደሆኑ ይገመታል፡፡

በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ ብዙዎቹ ከጦርነቱ የተረፉ ሰዎች በተለያዩ ካንሰሮች ወይም ሌሎች ከጨረር የሚመጡ አስከፊ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳጋጠማቸው ከዓለም አቀፉ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን የማስወገድ ዘመቻ ተቋም ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስገነዝባል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ኔቸር ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው እ.አ.አ. መጋቢት 7/ 2026 የአሜሪካ እና የእስራኤል የአየር ጥቃቶች በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ዙሪያ ያሉ በርካታ የነዳጅ ዴፖዎችን እና ማጣሪያዎችን ኢላማ አድርገዋል፡፡ ውጤቱም ለቀናት ሰማይን የሸፈነ ጥቁር ጭስ እና በዘይት የተመላ የአሲድ ዝናብ ከ10 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሉባት ከተማ ላይ እንዲዘንብ አድርጓል፡፡

ከተማዋ በሰልፈር ኦክሳይድ፣ ናይትሮጅን ኦክሳይድ፣ ፖሊሳይክሊክ አሮማቲክ ሃይድሮካርቦኖች እና ቤንዚን ጨምሮ በመርዛማ  ጭስ ተሸፍና  ነበር፡፡ መርዛማ ጭሱ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎችን ሊያስከትል፣ የእውቀት (ኮግኒቲቭ) ተግባርን ሊጎዳ እና አልፎ ተርፎም ስትሮክን ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡  የዘነበው ጥቁር ዝናብ ሰፊ የግብርና አፈርን፣ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ውኃ አቅርቦቶችን እንዲሁም በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ የስነ-ምህዳሮችን ብክለት ሊያስከትል ይችላል፡፡

በዓለማችን ከኃያላኑ ጎራ የመትመደበው ሩሲያም ከዩክሬን ጋር የምታደርገው ጦርነት አራት ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ ታዲያ በዚህ ጦርነት የዩክሬንን 20 በመቶ ግዛት ብትቆጣጠርም ይሕንን ግዛት ለመቆጣጠር ከፍተኛ መስዋዕት እየከፈለች ትገኛለች፡፡ ትክክለኛ የተጎጂዎች አሃዝ በሩሲያ መንግሥት በጥብቅ የተያዙ ምስጢሮች በመሆናቸው ባይታወቁም የምዕራቡ ዓለም የስለላ ኤጀንሲዎች እንደገለጹት ግን አጠቃላይ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸውን ይገምታሉ፡፡

የእንግሊዝ የስለላ ድርጅት 500 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች መሞታቸውን ሲጠቁም ቢቢሲ እና እንደ ሚዲያዞና ያሉ የመረጃ ምንጮች በበኩላቸው  ከ221ሺህ በላይ ሩሲያዊያን መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡  የዩክሬን መንግሥት እንዳስታወቀው ደግሞ እ.አ.አ ከየካቲት  2022 ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አጠቃላይ የተገደሉ እና የቆሰሉ ሩሲያዊያን መኖራቸውን ዘግቧል፡፡

የስትራቴጂክ እና የዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል (CSIS) ባወጣው መረጃ ሩሲያ  ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ የሞት ፣የመቁሰል እና የመጥፋት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ አሃዝ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ የጉዳት መጠን አንዱ እንደሆነ ነው የተገኘው መረጃ የሚያትተው፡፡

መረጃው ከሁለት ሺህ 700 በላይ ታንኮችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስነብቧል፡፡ ይህም የሩስያ ጦር ሰራዊትን ወደ ሁለት አስርት ዓመታት ወደ ኋላ  እንዲመለስ አድርጓል፡፡

ጆርናል ኦፍ ዴሞክራሲ በሠራው የምጣኔ ሀብት ትንተና ጦርነቱ በወታደራዊ ቅጥር ምክንያት ከፍተኛ የሰው ኃይል ጉልበት እጥረት፣ ከሀገር የሚሰደዱ ሩሲያዊያን መበራከትን፣ የነዳጅ ማመንጫ  እና የማጣራት ማዕከላት በተደጋጋሚ ጉዳት ስለደረሰባቸው የሀገሪቱን በጀት እንዲዋዥቅ እና ገቢዋ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ከ1ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም ከሀገሪቱ መልቀቃቸውን አሳውቋል፡፡ ይህም ሀገሪቱ የምታገኘው ገቢ ከመቀነሱ ባሻገር በኩባንያዎች ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ዜጎቿ ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡

በተጨማሪም መረጃው እንደሚያትተው ጦርነቱ  ሩሲያን የቻይና የኢኮኖሚ እስረኛ አደርጓታል፡፡ በተያያዘም  በዩክሬን ላይ   በመሠረተ ልማት እና በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ የካቲት (2026) ላይ የዓለም ባንክ እንዳወጣው መረጃ የመልሶ ግንባታው ወጪ 588 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል፡፡

ሩሲያ ማተርስ እንደዘገበው ደግሞ አራት ዓመታትን በተሻገረው ጦርነት ከ250 ሺህ እስከ 300 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል፡፡ የስትራቴጂክ እና ዓለምአቀፍ ጥናት ማዕከል በበኩሉ እንዳስታወቀው 140ሺህ የሚደርሱ የዩክሬን ወታደሮች እንደተገደሉ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ አጠቃላይ ወታደራዊ ጉዳት የደረሰባቸው ቁስለኛ እና የጠፉትን ጨምሮ ወደ 600ሺህ አካባቢ ደርሷል፡፡

ታዲያ ጦርነት ከሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ፣ አካላዊ እና ማሕበራዊ ጎዳቶች ባለፈ ጥሎት የሚያልፈው የሥነ ልቦና ጠባሳ ከፍተኛ ነው፡፡ ለአብነትም በዩክሬን 40 በመቶ በላይ የሚሆኑ ንፁሃን የሚሳኤሎችን እና የቦምቦችን ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መስማት፣ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ማየት እና የተጎዱ ሰዎችን መመልከት አሰቃቂ ጭንቀት አድርሶባቸዋል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here