የ26 ዓመቱ ቪዬትናማዊ ወጣት ቀደም ብሎ የነበረውን ከመጠን ያለፈ ውፍረት በወራት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ 38 ኪሎ ግራም ከመቀነሱ ባሻገር ̋ዊሚንግ” በተሰኘ የፊት ጡንቻ ልምምድ በፊት ቅርጹ ላይ ለውጥ በማምጣቱ ማንነቱን እስከ አለመለየት መድረሱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
ንጉዬን ቪዬት አንህ የተሰኘው በቪዬትናም የሀኖይ ከተማ ኗሪ ከዓመታት በፊት ከመጠን ባለፈ ውፍረቱ ጓደኞቹ ይዘበቱበት እንደነበረ ነው የተናገረው፡፡ ወጣቱም ይህን መሰረት አድርጐ የአካል ብቃት በመስራት ለማስተካከል ይወሰናል፡፡
በ2021 የኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በቤት ውስጥ የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ከሚያስተላልፉ ማህበራዊ ድረ ገፆች በመከታተል ልምምዱን ይያያዘዋል፡፡ በዚህም ምርጥ የተሰኘውን ለውጥ ማሳየት ቻለ – 38 ኪሎ ግራም በመቀነሱ፡፡
ያልተፈለገ ክብደት ወይም ከመጠን ያለፈ ውፍረትን በቤቱ በቤተሰቦቹ እገዛ ጭምር መቀነሱ የወጣቱን ግብ በከፊል ብቻ ነበር ያሳካለት፤ እናም አራት ማእዘን የተዘጋ የፊት ቅርጹን ማስተካከል እንዳለበት አምኖ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
የፊት ቅርጹን ለማስተካከል “ሚዊንግ” የተሰኘ እንቅስቃሴን በድረገፆች ሲተላለፍ ተከታትሎ ለ ስድስት ወራት ይከወናል፡፡ “ሚዊንግ” ምላስን ከላይኛው ትናጋ ጋር ለጥፎ መለማመድ መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡
በዚህ መልኩ በተከታታይ በራሱ ተነሳሽነት በቤቱ ባደረገው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያልተፈለገ ውፍረቱን አራግፎ ሸንቀጥቀጥ ብሎ በአንድ ነጥብ 82 ሜትር ቁመቱ በሞዴሊንግ ሞያ ለመሰማራት መቻሉን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
አሁን ላይ በባዩሚዲካል ኢንጂነሪንግ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከመከታተል ባሻገር በሀገሩ የ2026 “ሚስተር ቱሪዝም” ውድድር 25ቱ ውስጥ ለመግባት እየተጋ መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


