በኢትዮጵያ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ይህን ተከትሎም ጊዚያዊ ውጤቶች በየምርጫ ጣቢያዎች ይፋ ተደርገዋል፡፡ ለመሆኑ ከምርጫ በኋላ የሚከናወኑ ትግባራት ምን ምን ናቸው? በማንስ ይከናወናሉ?
የምርጫ ጣቢያዎች ኃላፊነትና እና ተግባር
ከድምፅ አሰጣጥ መጠናቀቅ በኋላ የድምፅ ቆጠራን በታዛቢዎች ፊት ማካሄድ፣ ውጤቱን ይፋ ማድረግ እንዲሁም የምርጫ ቁሶችን ለከፍተኛው የምርጫ አካል ማስረከብ ላይ ያተኩራሉ።
ከምርጫ በኋላ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትም የድምፅ ቆጠራ ማካሄድ፣ ድምፅ መስጠት እንደተጠናቀቀ የጣቢያው ኃላፊዎች ከታዛቢዎች እና ከተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በመሆን ሳጥኖችን በመክፈት የተሰጡ ድምፆችን በግልፅ ይቆጥራሉ።
ምርጫ ጣቢያዎች ውጤትን መመዝገብ እና ማሳወቅ ተጨማሪ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የእያንዳንዱን ዕጩ/ፓርቲ ውጤትም በትክክል በሕጋዊ ቅፅ (ፎርም) ላይ መመዝገብ፣ የውጤት መግለጫ መለጠፍ እንዲሁም የተቆጠረውን ውጤት በምርጫ ጣቢያው መውጫ ላይ ለሕዝብና ታዛቢዎች በሚታይ መልኩ መለጠፍ ነው።
ቁሶችን ማሸግ እና መላክ፣ ጥቅም ላይ የዋሉ እና ያልዋሉ የምርጫ ወረቀቶች እንዲሁም የተጠናቀቁ ፎርሞችን በታሸገ ሁኔታ ለሚመለከተው የምርጫ ክልል ማስተላለፍም የምርጫ ጣቢያዎች ተግባርና ኃላፊነት ነው።
የምርጫ ቦርድ ተግባር እና ኃላፊነት
ቦርዱ በሕገ መንግሥቱ እና በምርጫ ሕግ መሠረት የሚካሄድ ማንኛውም ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት ማስፈፀም፤ የመራጮችን ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት፤ መከታተልና መቆጣጠር፤ የፖለቲካ ድርጅቶችን መመዝገብ፣ በሕጉ መሠረት መከታተልና መቆጣጠር፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበትን መስፈርት ማውጣትና በመስፈርቱ መሠረት ድጎማውን ማከፋፈል፤ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም የመወሰን ሥልጣንና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያዎችን በመላው ሀገሪቱ ማደራጀት፣ ገለልተኛ፣ ብቃትና የሕዝብ ታአማኒነት ያላቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች መመልመልና ማሠልጠን፣ ከምርጫና ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማጠናከር፣ የምርጫ ሕጎችንና አፈጻጸምን በመገምገም ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ለይቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክን ማስተባበር፣ የምርጫው ውጤቶችን ማረጋገጥና ይፋ ማድረግ አለበት፡፡
በምርጫ ሂደት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ መፍትሔ መስጠት፤ በምርጫ ሂደት የምርጫ ውጤትን የሚያዛንፍ የሕግ ጥሰት ተከስቷል ብሎ ሲያምን ውጤቱን መሰረዝና ድጋሚ ምርጫ ማካሄድ እንዲሁም በምርጫ ሂደት የተፈጸመ የሕግ መጣስ፣ ማጭበርበር ወይም የሰላምና ፀጥታ ማደፍረስ ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦችን በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ፣ በጀት አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ፣ ማጽደቅና በሥራ ላይ ማዋል፣ በየደረጃው የሚካሄዱ ምርጫዎችን መርሀ ግብር (የጊዜ ሰሌዳ) ማዘጋጀት፣ ማጽደቅ፣ እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻልና አፈጻጸሙን መከታተል፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ማቅረብ፤ በዚህ ሕግና በሌሎች ሕጎች የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ ማንኛውንም ተግባራትን ማከናወን ነው፡፡በምርጫ ወቅት የቅሬታ አቀራረብ ሂደት
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ ምርጫ ውድድር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በውድድሩ ቅሬታ ካለም የሚፈታበት ሥርዓት (ሂደት) አለው፡፡
የምርጫ ወቅት ቅሬታዎች ሲኖሩ በየደረጃው በሚቋቋሙ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት በቦታው በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች እና ክልሎች ይታያሉ፡፡ ሰፊ እና አቤቱታ የሚጠይቁ ጉዳዮች ደግሞ በቀጥታ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም ለፍርድ ቤቶች እና ሰበር ሰሚ ችሎት ይቀርባሉ፡፡
አንድ የተመዘገበ/ች መራጭ ድምፅ ከመስጠት ሲከለከል/ስትከለከል ግለሰቡ አቤቱታውን በቅድሚያ ለምርጫ ጣቢያው ኃላፊ፣ የምርጫ ጣቢያ ኃላፊውም ጉዳዩን በማጣራት አቤቱታ አቅራቢው ድምፅ እንዲሰጥ ወይም ጊዜያዊ ድምፅ እንዲሰጥ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ጊዚያዊ ድምፅ እንዲሰጥ የተወሰነበት መራጭ ቅሬታውን ለምርጫ ክልል ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ጊዚያዊ ድምፁን ውድቅ ካደረገው እና በዚህ ውሳኔ ቅር ከተሰኙ ወዲያውኑ ቅሬታውን ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ጊዜያዊ ድምፅ የሰጠ መራጭ ከምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ወይም ሥልጣን ካለው ፍርድ ቤት የመምረጥ መብት እንዳለው የሚገልፅ ውሳኔ የድምፅ መደመሩ ከመጠናቀቁ በፊት ለምርጫ ክልል ማቅረብ አለበት፡፡የአንድን መራጭ ድምፅ መስጠት የሚቃወም ማንኛውም ሰው ቅሬታ ሲኖረው በመጀመሪያ ለምርጫ ጣቢያው ኃላፊ፣ በምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ/ኘች ደግሞ ለምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ፤ በምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ/ኘች ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት በማቅረብ ማስወሰን ይችላል/ትችላለች፡፡በድምጽ ቆጠራና ውጤት ላይ ቅሬታ ሲኖር ደግሞ ቅሬታ ያለው ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወኪል ወይም የግል እጩ ወኪል ቅሬታውን በቅድሚያ ለምርጫ ጣቢያው ኃላፊ፣ በምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ በሁለት ቀናት ውስጥ ለምርጫ ክልል ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ፣ በምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ ቅር ከተሰኙ ውሳኔው በተሰጠበት በአምስት ቀናት ውስጥ አቤቱታዎን ለቦርዱ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በቦርዱ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ውሳኔ ከተሰጠ በ10 ቀናት ውስጥ አቤቱታን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይቻላል።
የቅሬታ አቀራረብ እና አፈታት ሂደት
የምርጫ ጣቢያ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በምርጫ ጣቢያዎች በሚከናወኑ የመራጮች ምዝገባ ወይም የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ላይ ቅሬታ ካለው መጀመሪያ የሚታየው እዚያው ባለው የተውጣጣ ገለልተኛ ኮሚቴ እንደሆነ ነው አቶ አሻግሬ የሚገልፁት፡፡ የምርጫ ክልል ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በምርጫ ጣቢያው በተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካለ ደግሞ ለምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ይላል፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በክልል ደረጃ ከተሰጡ ውሳኔዎች ጋር አሁንም ቅሬታ ካለ ጉዳዩ በቀጥታ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚቀርብ ሲሆን ቦርዱ መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ በአንድ ወር ውስጥ ይሰጣል፡፡ የፍርድ ቤት ሥርዓት በምርጫ ሕጉ መሰረት የአስተዳደር ውሳኔዎች ሆነው በቦርዱ ውሳኔዎች ላይ ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች ካሉ ጉዳዩ በሕግ አግባብ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ይታያል፡፡ በምርጫ ሂደት በየደረጃው ስለሚኖር ቅሬታ አቀራረብ፣ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አደረጃጀት እና አሠራር መመሪያ ቁጥር 10/2013 በዝርዝር ተቀምጧል፡፡የኢትዮጵያ ምርጫ አዋጅ እና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች ማቋቋሚያ እና አሠራር መመሪያ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በምርጫ ጣቢያ፣ በምርጫ ክልል እና በክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ደረጃ ባሉ የምርጫ አፈጻጸም መዋቅሮች ላይ ሦስት ሦስት አባላት ያሏቸው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችን ያቋቁማሉ፡፡የምርጫው ሂደት ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ ሳይጓተት እንዲጠናቀቅ ለማስቻል በምርጫው ሂደት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በሕግ አግባብና ግልጽ በሆነ ሥርዓት ማስተናገድ እንደሚቻል ያነሱት አቶ አሻግሬ፤ ከአንዱ ቦታ የተወሰነው ውሳኔ በአግባቡ በመያዝ ወደ ቀጣዩ የውሳኔ ሂደት መሄድ እንደሚገባ ነው፡፡
የምርጫ ውጤቶች እንዴት እና በማን ይገለፃሉ?
በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ እንዲሁም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያ መሠረት በምርጫ ጣቢያ የተደረገ የቆጠራ ውጤት ቆጠራው በተጠናቀቀ በአንድ ሰዓት ውስጥ በምርጫ ጣቢያው ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ወጥቶ ለሕዝብ በይፋ ይገለጻል፡፡
የምርጫ ክልል የምርጫ ጽሕፈት ቤቶች የምርጫ ውጤት ከየምርጫ ጣቢያው እንደደረሳቸው ወይም የተረጋገጠ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር በምርጫ ክልሉ የድምጽ መስጫ ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪዎች ወይም ወኪሎቻቸው በተገኙበት ደምረው የተገኘውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋሉ፡፡የምርጫ ቦርድ በአጠቃላይ የምርጫ ውጤት ከየምርጫ ክልሉ ተጠናቆ እስኪደርሰው ድረስ ከየምርጫ ክልሉ የመጣለትን የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት የምርጫ ውጤት በጊዜያዊነት በቦርዱ ጽሕፈት ቤት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሆኖም የምርጫው ይፋዊ ውጤት በ10 ቀናት ውስጥ ካልተገለጸ ቦርዱ ጊዜያዊ ውጤቱን ይፋ ማድረግ ይኖርበታል፡፡የምርጫው ሂደት ከተጠናቀቀና አስፈላጊ መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላ የተረጋገጠ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር ከምርጫው ቀን ቀጥሎ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር፣ ድምፅ የሰጡ መራጮች ቁጥር፣ ድምፅ የሰጡና ያልሰጡ፣ የተመዘገቡ መራጮች መጠን በመቶኛ፣ የተመረጡ እጩዎች ስም ዝርዝርና የተመረጡበት የምርጫ ክልል፣ የአሸናፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች ስምና ለየምክር ቤቱ ያሸነፉትን መቀመጫ ብዛት፤ ጥቅም ላይ የዋለ፣ ያልዋለ፣ ከጥቅም ውጭ የሆነ የድምፅ መስጫ ወረቀት፣ እያንዳንዱ እጩ በየምርጫ ጣቢያው ያገኘው የድምፅ ውጤት እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው መረጃዎችን የያዘ ይፋዊ መግለጫ ያወጣል፡፡
ሆኖም በምርጫ ክልል ደረጃ በተገለጹ ውጤቶች ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች ውጤት መገለጹን እንዲዘገይ የሚያደርግ ከሆነ ይፋዊ ውጤት የሚገለጽበት ጊዜ እስከ 20 ቀን ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


