ብዙዎቻችን እኩለ ሌሊት ላይ አነቃቂ ቪዲዮዎችን አይተን፣ አዳዲስ መጽሐፍትን አንብበን ወይም የዓለምን ስኬታማ ሰዎች ታሪክ ሰምተን “ነገ ጠዋት ዓለምን እለውጣለሁ!” ብለን እንነሳለን።
ነገር ግን ጠዋት ስንነሳ ያ ትልቅ መነቃቃት (Motivation) ወዴት እንደጠፋ አናውቀውም። ለምን? ምክንያቱም ሞቲቬሽን በባህሪው “አታላይ” እና “ጊዜያዊ” ስለሆነ ነው።
በዚህ ጽሁፍ ሞቲቬሽን ለምን እንደማይሰራ እና በምትኩ ምን እንደሚያስፈልገን ከተለያዩ ታዋቂ ሰዎች፣ መጽሐፍት እና ሳይንሳዊ ጥናቶች በመነሳት እንመለከታለን።
አእምሯችን አነቃቂ ንግግሮችን ሲሰማ “ዶፓሚን” የተባለውን የደስታ ኬሚካል ያመነጫል። ዶክተር አና ሌምብኬ “Dopamine Nation” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደሚገልጹት ዘመናዊው ዓለም አእምሯችንን በዝቅተኛ ጥረት በሚገኝ ደስታ እንዲጠመድ አድርጎታል።
አነቃቂ ቪዲዮዎችን ማየት አእምሯችን “ስራውን የሰራን ያህል” እርካታ እንዲሰማው ያደርገዋል። ይህ የውሸት መነቃቃት ይባላል። በቪዲዮው ስንደሰት አእምሯችን ውጤቱን ያገኘው ስለሚመስለው በተግባር ስራውን ለመስራት የሚያስፈልገውን እውነተኛ ጉልበት ይነፍገናል። ሞቲቬሽን ስሜት እንጂ ድርጊት አይደለም።
ታዋቂዋ ደራሲ ሜል ሮቢንስ ሞቲቬሽን የለም የሚል ጠንካራ አቋም አላት። እሷ እንደምትለው የሰው ልጅ አእምሮ የተፈጠረው እኛን “ከአደጋ ለመጠበቅ” ነው።
አዳዲስ ስራዎችን መስራት፣ ጠዋት በጊዜ መነሳት ወይም ከባድ ስራዎችን መጀመር ለአእምሯችን “አደጋ” ናቸው። ስለዚህ አእምሯችን እነዚያን ስራዎች እንዳንሰራ በተለያዩ ሰበቦች ያግደናል።
ሜል ሮቢንስ እንዲህ ትላለች “ስራውን ለመስራት ‘ስሜቱ’ እስኪመጣልህ የምትጠብቅ ከሆነ እድሜ ልክህን ልትጠብቅ ትችላለህ። አእምሯችን ከባድ ስራዎችን ለመስራት በጭራሽ ፍላጎት አይኖረውም። ስለዚህ ስሜትን ጠብቆ ለውጥ ማምጣት የማይቻል የሞኝ ህልም ነው” ትላለች።
የቀድሞው የአሜሪካ የባህር ኃይል አባል እና “Can’t Hurt Me” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ዴቪድ ጎጊንስ ሞቲቬሽን ለደካሞች እንደሆነ ይናገራል። ጎጊንስ እንደሚለው ሞቲቬሽን እንደ አየር ሁኔታ የሚመጣና የሚሄድ ስሜት ነው።
ጎጊንስ የሚመክረው ማድረግን እና “ዲሲፕሊንን” ነው። “ባይመችህም፣ ዝናብ ቢዘንብም፣ ቢደብርህም እና ቢጨልምብህም መደረግ ያለበትን ነገር ማድረግ ስትችል ብቻ ነው ስኬታማ የምትሆነው” ይላል። የእሱ ህይወት እንደሚያሳየው ስኬት የሚመጣው ስሜትን በመገደብ እንጂ ስሜትን በማዳመጥ አይደለም።
አቶሚክ ሀቢትስ በሚለው ዝነኛ መጽሐፉ ጄምስ ክሊር አንድ ትልቅ እውነታን ያስቀምጣል”እኛ ወደ ግቦቻችን አንወጣም፤ ይልቁንም ወደ ስርዓቶቻችን እንወርዳለን።”
ሞቲቬሽን በግቦች ላይ ያተኩራል (ለምሳሌ፦ 10 ኪሎ መቀነስ)። ዲሲፕሊን ግን በስርዓት ላይ ያተኩራል (ለምሳሌ፦ በየቀኑ ለ20 ደቂቃ በእግር መጓዝ)።
ግቦች ሞቲቬሽን ይፈልጋሉ፤ ስርዓቶች ግን ልማድ ይፈልጋሉ። ልማድ ደግሞ አንዴ ከተገነባ በኋላ መነቃቃትን አይፈልግም። ልክ እንደ ጥርስ መቦረሽ፣ ሳያስቡት የሚደረግ ተግባር ይሆናል። ክሊር እንደሚለው ትልልቅ ለውጦች የሚመጡት በአንድ ቀን ትልቅ መነቃቃት ሳይሆን በየቀኑ በሚደረጉ ትናንሽ እና ተከታታይ ስራዎች ነው።
ጄፍ ሃደን “ዘ ሞቲቬሽን ሚት” በተሰኘው መጽሐፉ ስለ ሞቲቬሽን ያለንን ግንዛቤ ይገለብጠዋል። ብዙዎቻችን እንዲህ ብለን እናስባለን፦
መነቃቃት -> ድርጊት -> ውጤት
ነገር ግን እውነተኛው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው ይላል ሃደን፦
ድርጊት -> ውጤት -> መነቃቃት
ማለትም መነቃቃት የሚመጣው ስራውን ከጀመርን በኋላ ነው። ትንሽ ስራ ሰርተን ውጤት ስናይ ያ ውጤት በራሱ የበለጠ እንድንሰራ ያነቃቃናል። ስለዚህ “ሞቲቬሽን” ስራን ለመጀመር የሚሰራ ቀዳሚ ግብዓት ሳይሆን ስራን በመስራት ሂደት ውስጥ የሚገኝ “ተረፈ ምርት” ነው።
ማነቃቂያ ጊዜያዊ ስሜት እንደሆነ እና በጄምስ ክሊር፣ ሜል ሮቢንስ እና ዴቪድ ጎጊንስ እይታ ለምን ለዘላቂ ስኬት እንደማያበቃ ተመልክተናል። አሁን ደግሞ ይበልጥ ወደ አእምሯችን ባዮሎጂያዊ አወቃቀር፣ ወደ ጥንታዊያን ፈላስፋዎች ጥበብ እና ወደ ስነ-ልቦናዊ ምርምሮች ዘልቀን እንገባለን።
ደራሲ ስቲቨን ፕሬስፊልድ “The War of Art” በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ ስራን ለማከናወን የምናደርገውን ትግል ተቃውሞ ይለዋል። ተቃውሞ ማለት ማንኛውንም ጠቃሚ ስራ (መጽሐፍ መጻፍ፣ ስፖርት መስራት፣ ንግድ መጀመር) እንዳንሰራ የሚገፋፋን ውስጣዊ ኃይል ነው።
ፕሬስፊልድ እንደሚለው ሞቲቬሽን ለዚህ ኃይል ፍጹም አቅም የለውም። ሞቲቬሽን “አማተር” (ተራ) ስሜት ነው። አማተር ስራውን የሚሰራው ስሜቱ ሲመጣለት ብቻ ነው። “ባለሙያ” ግን ስሜቱን ሳይጠብቅ በየቀኑ በሰዓቱ ተገኝቶ ስራውን ይጀምራል። “ባለሙያው ድል የሚመጣው ስራውን ከጀመረ በኋላ እንደሆነ ያውቃል፤ አማተሩ ግን ስራውን ለመጀመር መነቃቃትን ይጠብቃል” ይላል። ስለዚህ ተቃውሞን ለማሸነፍ “ፕሮፌሽናል” መሆን እንጂ “የተነቃቁ” መሆን አይረዳም።
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የነበረው የሮማው ንጉሠ ነገሥት ማርከስ ኦሬሊየስ ሜዲቴሽንስ በተሰኘው የግል ማስታወሻው ላይ ስለ ጠዋት መነሳት እንዲህ ሲል ጽፏል “ጠዋት ከአልጋህ ለመነሳት በሚከብድህ ጊዜ እንዲህ በል፦ ‘ስራዬን ለመስራት እየተነሳሁ ነው። የተፈጠርኩበትን አላማ ለማከናወን ስሄድ ለምን አጉረመርማለሁ?’”
ስቶይኮች (የጥንት ሮማዊያን) በስሜት ላይ ሳይሆን በግዴታ ላይ ያምናሉ። ለእነሱ አንድን ስራ መስራት መነቃቃትን የሚጠይቅ ጉዳይ ሳይሆን የሰው ልጅ የመሆን ግዴታ ነው። ስሜትህ “ደብሮኛል” ቢልህም አእምሮህ ግን “ይህ መደረግ ያለበት ስራ ነው” ይላል። ስኬት የሚመጣው ስሜትን አሸንፎ በምክንያት መመራት ሲቻል ነው።
በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ቢ.ጄ ፎግ “ቲኒ ሀቢትስ” በተሰኘው መጽሐፋቸው የመነቃቃት ማዕበል የሚል ጽንሰ-ሐሳብ ያቀርባሉ። ሞቲቬሽን እንደ ባህር ማዕበል ነው፤ በድንገት ይነሳል፣ በድንገት ይሞታል ይሉታል።
ፎግ እንደሚሉት አንድ ስራ በጣም ከባድ ከሆነ ከፍተኛ መነቃቃት ያስፈልገዋል። ነገር ግን መነቃቃቱ ሲወርድ ስራውን እናቆመዋለን። ስለዚህ መፍትሄው ስራውን እጅግ በጣም ቀላል ማድረግ ነው። ለምሳሌ “በቀን አንድ ሰዓት ስፖርት እሰራለሁ” ከማለት (ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈልግ) “በቀን ሁለት ጊዜ ፑሽ አፕ እሰራለሁ” (ዜሮ ሞቲቬሽን የሚፈልግ) ወደሚል መቀየር። ስራው ቀላል ሲሆን መነቃቃትን አይፈልግም፤ በዲሲፕሊን ብቻ ይከናወናል።
ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአእምሯችን ውስጥ የማያቋርጥ ጦርነት አለ። “ሊምቢክ ሲስተም” የተባለው ጥንታዊው የአእምሮ ክፍላችን የቅርብ ደስታን፣ ምቾትን እና እረፍትን ይፈልጋል። “ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስ” የተባለው የፊት ክፍላችን ደግሞ አመክንዮአዊ፣ የወደፊት እቅድ አውጪ እና ዲሲፕሊን ያለው ክፍል ነው።
መነቃቃት አብዛኛውን ጊዜ ከሊምቢክ ሲስተም ጋር የተያያዘ “ስሜት” ነው። ነገር ግን ስራን በተከታታይ ለመስራት ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስን ማሰልጠን ያስፈልጋል። ይህ ክፍል ደግሞ የሚሰለጥነው በልምምድ እና በግዴታ እንጂ በደስታ ስሜት አይደለም። ስራውን ባይመቸንም በግዴታ ስንሰራው አእምሯችን ለረጅም ጊዜ ጥቅሞች ቅድሚያ መስጠትን ይማራል።
መነቃቃት ስሜት ነው፤ ስኬት ግን ድርጊት ነው። መነቃቃት ለውጥን ለመጀመር እንደ “ክብሪት” ሊያገለግል ይችላል። ክብሪት እሳቱን ይለኩሰዋል፤ ነገር ግን ቤቱን የሚያሞቀውና ምግቡን የሚያበስለው የሚነደው “እንጨት” (ዲሲፕሊን) ነው።
ስኬታማ ለመሆን ከፈለጉ እነዚህን ሦስት ነገሮች ተግባራዊ ያድርጉ፦
አንደኛ ዲሲፕሊን ይኑርዎት፦ ስሜትዎ ምንም ይሁን ምን ስራውን ይስሩ።
ሁለተኛ ስርዓት ይገንቡ፦ በትልልቅ ግቦች ከመጨነቅ ይልቅ በየቀኑ የሚሰሩ ትናንሽ ልማዶችን ይቅረጹ።
ሦስተኛ ድርጊትን ያስቀድሙ፦ ስሜቱ እስኪመጣ አይጠብቁ። ስራውን ይጀምሩ፤ ስሜቱ በራሱ ይከተልዎታል።
የሰብዕና ግንባታ አስተማሪው ጂም ሮን እንዳለው “ዲሲፕሊን በምኞት እና በስኬት መካከል ያለው ድልድይ ነው” ድልድዩን ሳይገነቡ ማዶ ለመሻገር አይሞክሩ። ሞቲቬሽን ያታለልዎታል፤ ዲሲፕሊን ግን ዳር ያደርስዎታል።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


