በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀልብ የሳበው እና በዓለማችን ግዙፉ የስፖርት መድረክ የሆነው የዓለም ዋንጫ በቀላሉ አልተፈጠረም፡፡ ይልቁንስ የጥቂት ግለሰቦች ጽኑ እምነት፣ ታሪካዊ ውሳኔዎች እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንጂ፡፡ የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት በምድራችን ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር የሚካሄደው በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ነበር፡፡
እ.አ.አ በ1924 እና 1928 የተደረጉት የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ ብዙ ተመልካችን አግኝተው እንደነበር የፊፋ ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የኦሎምፒክ ሕግ ጀማሪ ስፖርተኞች ብቻ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ በመሆኑ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) አዲስ እና ግዙፍ የእግር ኳስ መድረክ እንዲወልድ ምክንያት ሆኖታል፡፡
የዚህ ድንቅ ሀሳብ መሀንዲሶች ደግሞ ፈረንሳዊው የፊፋ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ሪሜት እና የወቅቱ የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የነበሩት ዋና ጸሐፊ ሄንሪ ዴላውናይ ናቸው፡፡እ.አ.አ. ግንቦት 28 ቀን 1928 በኔዘርላንድስ አምስተርዳም ከተማ በተካሄደው የፊፋ ኮንግረስ አባል ሀገራቱ በሙሉ ድምፅ አዲስ የዓለም እግር ኳስ ሻምፒዮና በየአራት ዓመቱ ለማካሄድ ወሰኑ። ኡራጋይንም የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ አድርገው መረጡ፡፡ ኡራጓይ የተመረጠችበት ዋነኛው ምክንያት የ1924 እና 1928 እ.አ.አ የኦሎምፒክ እግር ኳስ ሻምፒዮን በመሆኗ ነው፡፡ በተጨማሪም እ.አ.አ በ1930 የአገሪቱ 100ኛ የነፃነት በዓል የሚከበርበት ወቅት በመሆኑ ነበር፡፡
በወቅቱ ምንም ዓይነት የማጣሪያ ጨዋታ ሳይደረግ 13ቱም ተሳታፊ ሀገራት በፊፋ ግብዣ ነበር ወደ ኡራጓይ ያቀኑት። በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ግን በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ሰለነበሩ በአዲሱ የእግር ኳስ መድረክ ለመሳተፍ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ግብፅ በውድድሩ ላይ እንድትሳተፍ የተጋበዘች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር ነበረች። ነገር ግን በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ባጋጠማት ከባድ ማዕበል ብሄራዊ ቡድኗ ወደ ኡራጓይ ሳይጓዝ ቀርቷል፡፡ በዚህ ምክንያት አፍሪካ በመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ የወከላት ሀገር የለም፡፡በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ግን ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ሮማንያ እና ዩጎዝላቪያ የተጣንለለውን የአትላንቲክን ውቅያኖስ በማቋረጥ በውድድሩ ተካፍለዋል፡፡ እነዚህ የአውሮፓ ሀገራት “ ኮንቴ ቨርዴ” በተባለችው ታዋቂ የጣሊያን የቅንጦት መርከብ ነው የተጓዙት፡፡ መርከቧ አራቱንም ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያውን የወርቅ ዋንጫ በሻንጣቸው የያዙትን የፊፋን ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ሪሜትን ጭምር ነበረ የያዘችው፡፡
በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ታዋቂዋ መርከብ ለሁለት ሳምንታት የስፖርት ካምፕ እና የሽርሽር መርከብ መስላ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ተጫዋቾች ለሳምንታት ከሜዳ እና ከኳስ ርቀው በባህር ላይ መቆየታቸው በአካላዊ ብቃታቸው ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሮባቸው ነበር፡፡
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ለሁለት ሳምንታት በዘለቀው ጉዞ ተጫዋቾች የአካል ብቃት ችግር እንዳይገጥማቸው ጠዋት እና ማታ ልምምዶችን ለመስራት ቢሞክሩም ያ ግን በቂ አልነበረም፡፡ “ኤስ.ኤስ. ኮንቴ ቨርዴ” መርከብ ውድ የቅንጡ መርከብ በመሆኗ የሚቀርቡት ምግቦች እጅግ ምርጥ እና የቪአይፒ መስተንግዶ መሆኑ ተጫዋቾች ሳያውቁት ክብደት እንዲጨምሩ አድርጓቸዋል፡፡ በወቅቱ የነበሩ የብሄራዊ ቡድን መሪዎች የተጫዋቾችን አመጋገብ ለማስተካከል ጥረት ቢያደርጉም በነበረው አሰልቺ ጉዞ ምክንያት ምግቡ ዋነኛ መዝናኛቸው በመሆኑ የታሰበው ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡ከ14 ቀናት አሰልቺ የባህር ላይ ጉዞ በኋላ የአውሮፓ ብሄራዊ ቡድኖች ኡራጓይ ሲደረሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫም በይፋ ተጀመረ፡፡ እ.አ.አ. ሐምሌ 13 ቀን 1930 በኡራጓይ መዲና ሞንቴቪዲዮ የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በፈረንሳይ እና በሜክሲኮ መካከል ተካሄደ፤ በላቲን አሜሪካዊቷ አገር ኡራጓይ የተካሄደው የመጀመሪያው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ለዘመናዊው እግር ኳስ መሠረት የጣለ ቢሆንም የውድድሩ ሁነቶች ግን ዛሬም ድረስ እጅግ አስገራሚ፣ አስቂኝ እና ውጥረት የበዛባቸው እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በወቅቱ ጨዋታዎችን የሚመሩት ዳኞች ሙሉ የስፖርት ትጥቅ ሳይሆን ሙሉ ሱፍ፣ ክራቫት እና ረጅም ሱሪ ለብሰው ነበር ጨዋታውን የመሩት፡፡ የኡራጓይ እና የአርጀንቲና የፍጻሜ ጨዋታ እጅግ አስፈሪ ውጥረት ነግሶበት እንደነበር የእግር ኳስ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ከዐስር ሺህ በላይ የአርጀንቲና ደጋፊዎች በጀልባ ወንዝ አቋርጠው “ድል ወይም ሞት” እያሉ ወደ ሞንቴቪዲዮ ገብተዋል፤ በዚያ አስፈሪ በነበረው ድባብ በስታዲየሙ መግቢያ ላይ በነበረው ፍተሻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሽጉጦች ከደጋፊዎች በፖሊሶች መወረሳቸውን የፊፋ ዶት ኮም መረጃ ያስታውሳል፡፡በኡራጓይ እና በአርጀንቲና መካከል በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ሁለቱም ሀገራት በራሳቸው ኳስ ነበር የተጫወቱ፡፡ በአርጀንቲና ኳስ በተጫወቱበት የመጀመሪያው አጋማሽ አርጀንቲና ሁለት ለአንድ እየመራች ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በራሷ ኳስ የተጫወተችው ኡራጓይ አሸንፋለች። አስተናጋጇ ኡራጓይ አርጀንቲናን አራት ለሁለት በማሸነፍ የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ በደጋፊዋ ፊት ባማንሳት ታሪክ ሠርታለች፡፡
የኡራጓይ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የነበረው ሄክተር ካስትሮ በለጋ እድሜው (በ13 ዓመቱ) በአደጋ ምክንያት የቀኝ እጁን አጥቷል። “ኤል ማንኮ” (አንድ እጁ) በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው ተጫዋቹ በፍጻሜው ጨዋታ የመጨረሻዋን እና የማሸነፊያ ግቧን በጭንቅላቱ በማስቆጠር ሀገሩን ሻምፒዮን አድርጓል።
በአሜሪካ እና በአርጀንቲና የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ወቅት አንድ የአሜሪካ ተጫዋች ጉዳት ይገጥመዋል። የቡድኑ የሕክምና ባለሙያ (ፊዚዮቴራፒስት) ጃክ ኮል ተጫዋቹን ለማከም ወደ ሜዳ እየሮጠ ሲገባ የያዘውን የሕክምና ቦርሳ በድንገት ይጥለዋል፤ በቦርሳው ውስጥ የነበረው የክሎሮፎርም ጠርሙስ ተሰባብሮ ትንፋሹን ስላፈነው የህክምና ባለሙያው በሜዳው ላይ እራሱን ስቶ በመውደቁ በቃሬዛ ወጥቷል፡፡ እነዚህ ታሪኮች የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ሲታወስ አብረው ከሚታወሱት የሜዳ ላይ ክስተቶች መካከል መሆናቸውን የፊፋ ዶት ኮም መረጃ አመልክቷል፡፡በ1930 እ.አ.አ በትንሽ ስሜት እና አቅም የተጀመረው ይህ ግዙፍ የእግር ኳስ ድግስ ዛሬ ላይ መላውን ዓለም የሚንጥ፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀልብ የገዛ፣ እጅግ ግዙፍ የቢዝነስ እና የባህል መድረክ ለመሆን በቅቷል። በመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ በአጠቃላይ 18 ጨዋታዎች ሲደረጉ 70 ግቦች ብቻ ደግሞ ከመረብ አርፈዋል፡፡
በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ግን የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር መጨመርን ተከትሎ አጠቃላይ 104 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል፤ የውድድሩ ቅርጽም እስካሁን ከነበረው በእጅጉ የተለየ ሆኗል፡፡ በኡራጋዩ የዓለም ዋንጫ በሮማንያ እና በፔሩ መካከል የተከናወነውን ጨዋታ 300 ተመልካቾች ብቻ ነበር የታደሙት፡፡ ይህም በግዙፉ የእግር ኳስ ድግስ ታሪክ እስካሁን የተመዘገበ ዝቅተኛው የተመልካች ቁጥር ነው። ዘንድሮ ግን በእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ ከ60 ሺህ በላይ ተመልካቾች በስታዲየም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


