የኮሪደር ልማት ማለት የአንድን ከተማ ወይም አካባቢ ገጽታ ለማዘመን፣ የትራፊክ ፍሰትን ለማሳለጥ እና ከዘመናዊ ከተሜነት ጋር የተሳሰረ ኑሮን ለመፍጠር የሚከናወን የተሟላ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና እድሳት ነው፡፡ ኮሪደር ልማት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች መተግበር ጀምሯል፡፡ ልማቱ ከተሞችን ምቹ የመኪና፣ ሳይክል እና የእግረኛ መንገዶች እንዲኖሯቸው አስችሏል፡፡ ደረጃቸውን በጠበቁ መብራቶች እንዲያሸበርቁ፣ በውኃ ማስወገጃ ሥርዓት እንዲዘምኑ… አድርጓል፡፡ ኮሪደር ልማት ከውበት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ልማቱ እየተከናወነባቸው ካሉ ከተሞች መካከልም ባሕር ዳር አንዷ ናት፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ በኵር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙን አነጋግራለች፡፡ አቶ ተሻገር እንደገለጹት ባሕርዳር የኮሪደር ልማትን ቀድመው ከጀመሩት የሀገሪቱ ከተሞች መካከል አንዷ ናት፤ ሥራውም ባለፈው ዓመት ነበር የተጀመረው፡፡ በፍጥነትም በርካታ ሥራ መሥራት ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ እንደ ባሕር ዳር የኮሪደር ልማት ያስፈልጋታል ተብሎ በዲዛይን የተጠና 31 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡
የኮሪደር ልማቱ ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ አየር ማረፊያ ተነስቶ በአሮጌው ዓባይ ድልድይ አድርጎ እስከ ዓባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ድረስ ያለውን ይሸፍናል፡፡
ሌላው ደግሞ ከኢላ ማደያ በአዲስ አበባ መውጫ አድርጎ በአዲሱ ዓባይ ድልድይ በኩል በገብርኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ አድርጎ ወደ ጎንደር ከሚወስደው መንገድ ጋር ይገናኛል፡፡
ከኤርፖርት መስመር ከኢላ ማደያ ተነስቶ በሰብስቴሽን መብራት ኀይል በኩል በልደታ የሚያልፍው ሌላው ምእራፍ ነው፡፡ ይህም ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሸፈነ የኮሪደር ልማት ነው፡፡
ሁሉንም በአንድ ጊዜ መሥራት ስለማይቻል በምዕራፍ በምእራፍ ከፋፍሎ እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የመጀመሪያው የኮሪደር ልማት በ2017ዓ.ም ነበር የተጀመረው፡፡ ቦታውም ከስካይ ሆቴል እስከ አጅፕ ነዳጅ ማደያ የሚደርስ ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው፡፡ የኮሪደር እና የጣና ዳር ልማት በሚልም ነው እቅድ ተይዞ የተሠራው፡፡ በዋናነት በዚህ መስመር ሦስት ሜትር ሰፋት ያላቸው የሳይክል እና ዝቅተኛው አምስት ሜትር የእግረኞች መንገድ፣ አራት ነጥብ ሦስት ሜትር ስፋት ያለው የአረንጓዴ ልማት ቦታዎች ተካተውበታል፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ጣና ከባሕር ዳር ከተማ ጋር የተገናኘበት ነው፡፡ በዚህም ጣናን ከከተማዋ ጋር በቀጥታ ለማገናኘትም(ለዕይታ ክፍት ለማድረግ) ዘጠኝ ቦታዎች ተከፍተዋል፡፡
እንደ አቶ ተሻገር ማብራሪያ ቀደም ሲል በአስፋልትም ሆነ በብስክሌት አልያም በመኪና ሲጓዙ ጣናን ማየት አይቻልም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን የጣና ውብ ገጽታ ለሕዝቡ ልዩ መስእብ ሆኗል፡፡ ነፋሻማ አየሩም ከጣና ወደ ከተማዋ መዝለቅ ጀምሯል፡፡ ቦታዎቹም ለመዝናኛ እና ለመናፈሻ ምቹ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ለአብነትም በአልማ እና በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መካከል፣ በአልማ እና በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን መካከል ፣ በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እና በባሕር ትራንስፖርት ድርጅት መካከል የተሠሩ መናፈሻዎች እና ሰሞኑን የተመረቀው የዘንባባ ፓርክ የመጀመሪያው ዙር ቱርፋቶች ናቸው፡፡ የአውቶቡስ፣ የታክሲ እና የሳይክል ማቆያዎች የተሠሩበት ምእራፍም ነው፡፡ አሁን ላይ ካፍቴሪያዎች ሁሉ ተከፍተው ሥራ ጀምረዋል፡፡የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ላይ የሕንጻዎች ግራ እና ቀኙ ተመሳሳይ መለያ ቀለም (ከለር ኮድ) ተመርጦ ተቀብተዋል፤ ይህም የከተማዋን ደረጃ ከፍ አድርጎታል፡፡ባለፈው ዓመት የተጀመረው ሁለተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማት ሁለት ኪሎ ሜትር አካባቢ የሸፈነ መሆኑን ሥራ አሥኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ ከተጀመሩት መካከልም ብዙዎቹ በተያዘው በጀት ዓመት ይጠናቀቃሉ፡፡ በዋናነት የሚያካትተው ከኤርፖርት – ኢላ ማደያ – ከድባንቄ መድኃኒዓለም አስፋልት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡
ሌላው ከአልማ – ወተር ፍሮንት ሆቴል የሚወስደው ነው፡፡ ሰፈሩ ቀደም ሲል የፈራረሱ ቤቶች የነበሩበት እንደ ነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ከመልሶ ማልማት ጋር ተያይዞ ከ250 በላይ ነዋሪዎች ተነስተዋል፡፡ ከተነሽዎቹ መካከል ከ150 በላይ የሚሆኑት በቀበሌ ቤት የሚኖሩ ነበሩ፡፡ እነዚህም ነዋሪዎች ትክ የመኖሪያ ቦታ እና ለባለይዞታዎች ካሳ ተሰጥቷቸው አካባቢው ሊለማ ችሏል፡፡በዚህም ከአልማ – ዋተር ፍሮንት በሚወስደው መንገድ የተሠራው የኮሪደር ልማት የባሕር ዳር ከተማ ደረጃዋን ከፍ ያደረገ እና ገጽታዋን የቀየረ ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በሁለተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማት እንደ አንደኛው ምእራፍ ሁሉ የአውቶቡስ፣ የሳይክል እና የታክሲ መቆሚያዎች፣ የካፍቴሪያ እና የፈጣን ምግብ መሸጫ ሱቆች ተካተውበታል፡፡
አሁን ላይ እየተሠራ የሚገኘው ሦስተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማት ከሁለቱ ትንሽ ሰፋ እንደሚል ሥራ አሥኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ የሚያካትታቸውም ከድሮው ጊዮን ሆቴል እስከ ገጠር መንገድ ያለው የሦስት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ በተመሳሳይ ከገጠር መንገድ እስከ ዘጌ መንገድ መገንጠያ ያለው ነው፡፡ በጣም ለየት የሚያደርገው የዘንድሮው ከጊዮን ሆቴል እስከ ገጠር መንገድ ያለውን በከተማው ኮንስትራክሽን ድርጅት ባለሙያዎች እየተሠራ መሆኑ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ወጪ ለመቆጠብ እንደረዳቸው ገልጸዋል፡፡
ሌላው ከአሮጌው ዓባይ ድልድይ እስከ ዓባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ያለው ሲሆን ከአባይ ማዶ ዲያስፖራ አካባቢ ሦስት ነጥብ አምስት የአስፋልት እና የኮሪድር ልማትም እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዓመት ወደ ዲያስፖራ ካለው መንገድ ውጪ ሁሉም እስከ ሰኔ 30 /2018 ዓ.ም ድረስ የሚጠናቀቁ ይሆናል፡፡
አቶ ተሻገር እንደአብራሩት የሦስተኛው ምእራፍ የኮሪደር አካል የሆነው ከጊዮርጊስ እስከ ፓፒረስ ያለው መንገድም በፍጥነት እየተሠራ ነው፡፡ በዚህ መስመር የማሕበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበርና ለልማቱም ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ አዋጥቷል፡፡ በጥቅሉ እስካሁን ባለው የኮሪደር ልማት ሥራ ማሕበረሰቡ ከ500 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈ በእውቀቱም እየተሳተፈ ነው የሚገኘው፡፡ከኮሪደሩ ልማት ጋር ራሱን የቻለ “የአረንጓዴ ልማት ኢንተርፕራይዝ” የሚባል የገቢ ማስገኛ መቋቋሙን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ የአረንጓዴ ልማት ቦታዎችን (green area)፣ መዝናኛ ስፍራዎችን፣ መናፈሻዎችን፣ ካፍቴሪያዎችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ እስካሁን በተሠሩት እና ቀጣይ ተሠርተው በሚጠናቀቁት የመዝናኛ ስፍራዎችም እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በወር የከተማ አስተዳደሩ ገቢ ሊያገኝበት እንደሚችል ነው ያብራሩት፡፡
ከሥራ እድል ጋር በተያያዘም እስካሁን ባለው የኮሪደር ልማት 32ሺህ ወጣቶች በጊዜያዊነት ተቀጥረዋል፡፡ ወጣቶችም በራሳቸው ወጪ አንድ መናፈሻ(ግሪን ኤሪያ) እያለሙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ከተማዋ በወጣቶች እየተገነባች እንዳለች እና የኔነት ስሜት እያዳበሩ እንዳሉ ማሳያ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡
ኮሪደር ልማት ካስገኛቸው ቱርፋቶች አንዱ የሥራ ባሕልን ማሻሻሉ እንደሆነም ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ በዚህም የኮሪደር ልማት ሠራተኞች ሥዓት ሳይገድባቸው እስከ ምሽቱ አራት እና አምስት ሰዓት ድረስ አምሽተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ይህም ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስችሏል፡፡በተያያዘም ከተማዋ በኮሪደር ልማቱ በመነቃቃቷ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደረጃቸውን የጠበቁ ትላልቅ ሆቴሎች እየተገነቡ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ በዚህም ከሰሞኑ ተጠናቆ የተመረቀው የፈለገ ጊዮን ሪዞርት ሆቴል አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በቀጣይም ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የሚሆኑ ሆቴሎች አሉ፡፡ የእነዚህ ሆቴሎች መገንባትም ከተማዋ ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች ምቹ በመሆን ለቱሪዝም መዳረሻ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡ መብራት፣ቴሌ እና የውኃ ፍሳሽ አገልግሎት ተቋማት ገና የኮሪደር ልማቱ ሲታቀድ አብረው የሚሠሩትን ዲዛይን ይዘው ለ30 እና ለ40 ዓመታት የሚቆይ የቱቦ ቀበራ ፣ የመስመር ዝርጋታ እያከናወኑ ናቸው፡፡
ይህ በመሆኑም እንደ በፊቱ አንዱ የሠራውን መሰረተ ልማት ሌላው ተቋም አያፈርስም፡፡ እንዲሁም ከተማዋ ደልዳላ በመሆኗ ቀደም ሲል የተፋሰስ ችግር ነበረባት፡፡ ታዲያ የኮሪደር ልማቱ ያለውን የተፋሰስ ችግር የሚቀርፍ፣ አንዱ የሠራውን ሌላው አለማፍረሱ የመንግሥት በጀት ያለአግባብ እንዳይባክን እንደ ሚያስችል ሥራ አሥኪያጁ ጠቁመዋል፡፡አጠቃላይ ባሕርዳር ላይ የሚሠራው የኮሪደር ልማት 31 ኪሎ ሜትር ሲሆን እስካሁን የተከናወነው ግማሹ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ ዓመትም ቀሪዎቹ እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡ ሕብረተሰቡም የሚሠሩ የኮሪደር ልማቶችን በባለቤትነት እንዲጠብቅ እና እንዲንከባከብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መረጃ
የኮሪደር ልማት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ
- የአገልግሎት ተደራሽነት፡ አስፈላጊ አገልግሎቶችን (እንደ መፀዳጃ ቤት፣ የሕዝብ ትራንስፖርት መጠበቂያዎች) በየአካባቢው በእኩል ደረጃ ተደራሽ ያደርጋል።
- የንግድ እንቅስቃሴን ማነቃቃት፡ ለገበያና ንግድ ሥራ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ያሳድጋል።
ዘላቂ የከተሜነት ዕድገት
- ጠንካራ መሠረተ ልማት፡ የሕዝብ ቁጥር መጨመርን እና የከተሞች ፈጣን መስፋፋትን ታሳቢ በማድረግ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ ዘላቂ የከተማ ኔትወርኮችን ይገነባል።
- ተምሳሌትነት፡ ከተሞች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ሀገሪቱን የሚመጥኑ ከተሞች እንዲሆኑ ያስችላል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


