ልጆች እንዴት ናችሁ? የሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል፤ መጭው የክረምት ጊዜ እየተማራችሁ የምትጫወቱበት እና የምታርፉበት ነው፤ ስለሆነም ስለጨዋታ የተወሰነ እንበላችሁ፡፡
የመደበኛው የትምህርት ጊዜ አልቆ የረጅም ጊዜ የእረፍት ወቅት ሲመጣ ልጆች በትምህርት ቤት ያገኟቸውን እውቀቶች እንዳይረሱ እና አእምሯቸው ይበልጥ ንቁ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። በእረፍት ጊዜ ልጆች ረጅም ሰዓት በስልክ ወይም በቴሌቪዥን መስኮት ከማሳለፍ ይልቅ አካላዊ እና አእምሮአዊ ብቃታቸውን የሚያሳድጉ ጨዋታዎችን መጫወት አለባቸው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የፈጠራ እና የስዕል ስራዎች ለእረፍት ጊዜ ፍጹም ምርጫዎች ናቸው። ልጆች በተለያዩ ቀለማት መሳል፣ በጭቃ ወይም በሌሎች ቁሶች ቅርጾችን መስራት ምናባቸውን እንዲያሰፉ እና የግራና ቀኝ አእምሯቸውን በእኩል እንዲያሠሩ ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በክረምት የእረፍት ወቅት በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ቀላል የሳይንስ ሙከራዎች ለምሳሌ ነገሮች በውኃ ላይ የመንሳፈፍ እና የመስመጥ ሁኔታን መፈተሽ የልጆችን የመመራመር ባህሪ ያጠናክራሉ።
በሁለተኛ ደረጃ የቦርድ እና የጠረጴዛ ጨዋታዎች ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር ያለውን ግንኙነት እያጠናከሩ አእምሮን ለማሰራት በጣም ጠቃሚ ናቸው። እንደ ሞኖፖሊ ያሉ የሂሳብ አጠቃቀምን የሚጠይቁ ጨዋታዎች፣ ቼዝ፣ እንዲሁም የተበታተኑ ምስሎችን ወይም የኢትዮጵያ ካርታን የሚያሳዩ እንቆቅልሾችን ማገጣጠም (Jigsaw Puzzles) የልጆችን የስትራቴጂ አወቃቀር እና ትዕግስት ያሳድጋሉ። የቃል ጨዋታዎች እና በትልልቅ ሰዎች የሚነገሩ ባሕላዊ ተረቶችም የልጆችን የቋንቋ እና የማዳመጥ ክህሎት በመገንባት በኩል ትልቅ ድርሻ አላቸው።
በመጨረሻም ከአካባቢ ጥበቃ እና ከአካል ብቃት ጋር የተያያዙ ከቤት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እጅግ ይመከራሉ። ለምሳሌ በጓሮ ውስጥ ከአፈር እና ከተክሎች ጋር መጫወት (Gardening) ልጆች ስለ ተፈጥሮ እንዲማሩ እና ኃላፊነትን እንዲለማመዱ ያደርጋል። እንደ ሩጫ፣ ድብብቆሽ፣ እቃቃ እና የተለያዩ የንቅናቄ ውድድሮች ደግሞ ልጆች ንቁ ሆነው እንዲሰነብቱ እና አካላዊ ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ይረዳል ይላል የኮተቤ መምህራን ዩኒቨርሲቲ ያወጣው “የመጫወት ተኮር ትምህርት (Play-Based Learning) ፖሊሲ ጥናት”።
ተረት
የተደበቀው ሀብት
አንድ በጣም ታታሪ የነበረ አባት ሦስት ሰነፍ ልጆች ነበሩት። አባትየው ሊሞት ሲል ልጆቹን ጠርቶ “ልጆቼ ሆይ! እኔ ካለፍኩ በኋላ በወይኑ እርሻችን ውስጥ የተቀበረ ትልቅ የወርቅ ሀብት አለ፤ ቆፍራችሁ አውጡት” አላቸው።
አባትየው ከሞተ በኋላ ልጆቹ ወርቁን ለማግኘት ጓጉተው የወይኑን እርሻ መሬት በሙሉ በጥልቀት መቆፈር ጀመሩ። መሬቱን በሙሉ አገላብጠው ቢቆፍሩትም ምንም ዓይነት የተቀበረ ወርቅ ሊያገኙ አልቻሉም። በጣም ተናደውም ሥራቸውን አቆሙ።
ነገር ግን መሬቱ በጥሩ ሁኔታ ተቆፍሮ እና ተለስልሶ ስለነበር በዚያ ዓመት የወይኑ እርሻ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጣም ብዙና ምርጥ ፍሬ አፈራ። ልጆቹ ፍሬውን ሸጠው ብዙ ገንዘብ አገኙ። ያን ጊዜ የአባታቸው “የተቀበረ ወርቅ” ማለት የሥራ እና የትጋት ውጤት መሆኑን ተረዱ። ትልቁ የወርቅ ሀብት ጠንክሮ መሥራት ነው። በጉልበትህ እና በላብህ የምታገኘው ውጤት ሁልጊዜም ይባርካል።
ሞክሩ
- ውኃ በጣም ሲቀዘቅዝ ወደ በረዶነት ይለወጣል፤ በጣም ሲፈላስ ወደ ምን ይለወጣል?
መልስ፦ ወደ እንፋሎት
- እኔ ክንፍ የለኝም ግን እበራለሁ፤ ዓይን የለኝም ግን አለቅሳለሁ። እኔ ማን ነኝ?
መልስ፦ ደመና
- በየብስ (በመሬት) ላይ ከሚኖሩ እንስሳት ሁሉ በጣም ፈጣን የሩጫ ፍጥነት ያለው እንስሳ ማን ይባላል?
መልስ፦ አቦሸማኔ
ነገር በምሳሌ
- “የወላጅ ምርቃት፣ የመንገድ ስንቅ”፡-ወላጆችን ማክበርና ማገዝ ሁልጊዜም መልካም ውጤት ያመጣል።
- “አያያዝ ያበላሻል፣ አያያዝ ያሳምራል”፡-አንድን ዕቃ ወይም የቤት ሥራ በጥንቃቄ ከያዝነው ያምራል፤ ካልተጠነቀቅንበት ግን ወዲያውኑ ይበላሻል፡፡
- “ከመናገር ማዳመጥ”፦ ከመናገራችን በፊት የሌሎችን ሀሳብ በትዕግሥት ማዳመጥ የበለጠ እውቀትን ይሰጠናል ማለት ነው።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


