በእጆቹ ደረጃ ወራጁ

0
4

የ31 ዓመቱ ኔፓላዊ ወጣት መቶ ደረጃዎችን “እጆቹን እንደ እግር”  ተጠቅሞ በ44 ነጥብ 71 ሰከንድ በመውረድ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ለክብረወሰን መብቃቱን ዩፒአይ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

የኔፓል ዜጋው ሀሪ ቻንድራ ጊሪ በእጆቹ እየተራመደ 100 ደረጃዎችን በ44 ነጥብ 71 ሰከንድ ፈጣን ሰዓት በመውረዱ ለክብረወሰን በቅቷል፡፡ ለዚህ ስኬት ከመብቃቱ በፊት ጠንካራ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቶ በመጨረሻ በቻይና ቾንግ ኪንግ ውስጥ በመከወን ክብረወሰኑን አስመዝግቧል፡፡

ወጣቱ ባለ ክብረወሰን እጆቹን እንደ እግር ተጠቅሞ ደረጃዎችን  መውረድ ከባድ እና ፈታኝ መሆኑን ነው የጠቀሰው፤ ያም ሆኖ ለክዋኔው ቻይና ታዋቂ ደረጃ ያላት ሀገር በመሆኗ ያለመወን ለመከወን እንደመረጣትም ተናግሯል፡፡

የወጣቱ ልዩ ክዋኔ ግብ በእጁ መቆም እና መራመድን በልምምድ ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ መከወን እንደሚቻል ለማመላከት መሆኑን ነው ያሰመረበት፡፡ ወጣቱ በእጆቹ ቆሞ ለመራመድ በቂ ቁጥጥር እና ከትክሻው እጆቹን በጥንቃቄ በማራቅ “መራመድ”ን ደጋግሞ በመስራት መለማመዱንም ተናግሯል፡፡ ሆኖም ሌሎች ህክምና እና የደህንነት መጠበቂያ በሌለበት እንዳይሞክሩት ምክሩን ለግሷል፡፡

ባለ ክብረወሰኑ ከዚህ ቀደም 50 ደረጃዎችን በእጆቹ በ12 ነጥብ 65 ሰከንድ በመውረድ፤ በእግሮቹ መካከል ኳስ ይዞ በእጆቹ 10 ሜትር ርዝመትን በ4 ነጥብ 49 ሰከንድ በመራመድ፤ 75 ደረጃዎችን በ25 ሰከንድ ፍጥነት በእጆቹ መውረድ የመሳሰሉ ክብረወሰኖች በስሙ መመዝገባቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 15   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here