ከድርቅ መላቀቅ ያልቻለችው ዓለማችን

0
117

በአሁኑ ጊዜ ድርቅ ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ እየፈተነ ያለ የአካባቢ እና የሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ሆኗል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት፣ የሳይንስ ተቋማት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች እንደሚያሳዩት ድርቅ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ እየተባባሰ ነው፡፡

ዓለም እየጨመረ በሚሄድ የውኃ እጥረት፣ የሙቀት መጨመር እና የምግብ ዋስትና ቀውስ ተፅዕኖ ሥር ትገኛለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ በጥር 2026 ባወጣው ሪፖርት ዓለማችን “ከውኃ ቀውስ አልፋ ወደ የውኃ ኪሳራ (Water Bankruptcy) ዘመን ገብታለች” ብሏል፡፡ ብዙ ሀገራትም የውኃ ሥርዓቶቻቸውን  ወደ ቀድሞ መደበኛ ሁኔታ መመለስ እየተሳናቸው ነው፡፡

ዘ ጋርዲያን ድርቅ ዛሬ በዓለም ላይ ካሉት ከባድ ችግሮች አንዱ መሆኑን ዘግቧል፡፡ በዘገባው እንደተመላከተው ድርቅ እርሻን ይጎደል፣ የምግብ ዋጋን ያንራል፤ የውኃ እጥረትን ያባብሳል፤ ረሃብንና መፈናቀልንም ያስከትላል፡፡ ግጭቶችን ያባብሳል፤ ኢኮኖሚን ያዳክማል፤ እንዲሁም በትውልዶች የሚታወስ ማሕበራዊ ጠባሳንም ያስከትላል፡፡

ድርቅ እንዴት ይከሰታል?

ድርቅ በአንድ አካባቢ ለረጅም ጊዜ ከመደበኛው በታች ዝናብ ሲኖር የሚፈጠር የውኃ እጥረት ነው፡፡ ችግሩም ቀስ በቀስ እየተጠናከረ ይመጣል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ የዓለምን ሙቀት በመጨመር የዝናብ ሥርዓትን ያዛባል፡፡ ሙቀት  ሲጨምር ከአፈር፣ ከሐይቆች እና ከወንዞች ውኃ በፍጥነት እና በከፍተኛ መጠን ይተናል፡፡ ይህም የውኃ እጥረትን ያባብሳል፡፡

የደን ጭፍጨፋም ዋነኛው የድርቅ መንስኤ ነው፡፡ ዛፎች የውኃ ዑደትን በመደገፍ በቂ ዝናብ እንዲኖር ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ደኖች ሲጠፉ ግን የአካባቢው እርጥበት ይቀንሳል፡፡

ትኩረቱን አካባቢያዊ ጉዳዮችን እና ተፈጥሮን አድርጎ መረጃን የሚያጋራው ኔቸር ድረገጽ እንዳስታወቀው እ.አ.አ በ2025 የዓለም መሬት 30 በመቶ ያህሉ በድርቅ ተጎድቷል፤ ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ሁለት በመቶው በከፍተኛ ድርቅ ተጽዕኖ ስር ነበር፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድርቅ ሪፖርት እንዳመለከተው እ.አ.አ ከ2023 እስከ 2025 ድረስ የታዩትን ድርቆች “በታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ድርቆች እጅግ አስከፊ ክስተቶች” ሲል ገልጿል፡፡ ከሪፖርቱ አዘጋጅ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ማርክ ስቮቦዳ “ችግሩ ተራ የዝናብ እጥረት አይደለም፤ በቀስታ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ አደጋ ነው” ብለዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በበኩሉ እንዳስታወቀው ድርቅ የምግብ ዋስትናን በጣም እየጎዳ ይገኛል፡፡ በተያዘው ዓመትም በ(2026) በድርቅ ምክንያት 363 ሚሊዮን ሰዎች ለከባድ ረሃብ ተጋላጭ ሊሆኑ  ይችላሉ፡፡ ከግጭትና ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጋር ተዳምሮ የረሃብ ቀውሱንም እያባባሰ ነው፡፡

ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳቸው አካባቢዎች መካከልም የአፍሪካ ቀንድ አንዱ ነው፡፡ (ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ) በቀንዱ ተደጋጋሚ በተፈጠረ የዝናብ እጥረት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብና ለመፈናቀል ተዳርገዋል፤ በሶማሊያ ብቻ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ከባድ የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡

በሶማሊያ እ.አ.አ ከ2025 እስከ 2026 ድረስ የተከሰተው ድርቅ እ.አ.አ በ2011፣ 2017 እና 2022 ከተከሰቱት ከባድ ድርቆች ጋር የሚመጣጠን መሆኑን የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) አስጠንቅቋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና አፕሊኬሽንስ ማዕከል (ICPAC) በበኩሉ በተለይም በደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ አብዛኛው የኤርትራ ክፍል፣ ሱዳን እና የኬንያ ምዕራባዊ እና የባሕር ጠረፍ አካባቢ ያሉ ቦታዎች የሚያገኙት ዝናብ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህም ድርቅን ያባብሳል፡፡

በተጨማሪም በድርቅ ምክንያት  በደቡብ አውሮፓ የወይራ ምርት በግማሽ ቀንሷል፣ የምግብ ዋጋም ጨምሯል፡፡ በአማዞን ወንዝ ተፋሰስ የውኃ መጠን በእጅጉ በመቀነሱ ዓሣዎች እየሞቱ ነው፡፡  የመጓጓዣ ችግር እና የመጠጥ ውኃ እጥረትም ተከስቷል፡፡

የአየር ንብረት ባለሙያዎች አሁን የጀመረው ኃይለኛ የኤል ኒኖ (El Niño) ክስተት እ.አ.አ በ2026 እና 2027 በብዙ የዓለም ክፍሎች ድርቅን ሊያባብስ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው፡፡ ይህም የምግብ ምርትን፣ የውኃ አቅርቦትን እና የሰዎችን ኑሮ የበለጠ ሊጎዳ ይችላል፡፡

የድርቅ ዳፋዎች

ድርቅ የተፈጥሮ አደጋ ብቻ አይደለም፤ ሕዝቦችን የሚያፈናቅል፣ ኢኮኖሚን የሚያዳክም፣ ፖለቲካዊ ቀውሶችን የሚያባብስ እና በትውልዶች አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋ ጠባሳን የሚተው ክስተት ነው፡፡ በታሪክ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ከባድ የድርቅ ወቅቶችም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ፣ ለሞት እና ለመፈናቀል ዳርገዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ፕሮግራም እንዲሁም የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እንዳስታወቁት እ.አ.አ ከ1968 እስከ 1974 የተከሰተው የሳህል ክልል ድርቅ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይዎት ቀጥፏል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳትም አልቀዋል፡፡ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በ1930ዎቹ እ.አ.አ በአሜሪካ ሜዳማ ክልሎች የተከሰተው አውሎ ነፋስ (Dust Bowl) በድርቅ እና በተሳሳተ የመሬት አጠቃቀም ምክንያት የተፈጠረ ከባድ አደጋ ነበር፡፡ በአደጋውም ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ያህል ሰዎች መኖሪያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ የእርሻ መሬቶች በአቧራ ተሸፍነው ስለነበር ምርት ቀንሷል፡፡ ይህ አደጋም በዓለም ላይ የአፈር ጥበቃ ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ ማድረጉን የአሜሪካ የድርቅ ቅነሳ ማዕከል (National Drought Mitigation Center) ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል፡፡

የዓለም ባንክ እንዳስታወቀው በታሪክ ከተመዘገቡት እጅግ ከባድ ድርቆች መካከል እ.አ.አ ከ2006 እስከ 2010 በሶሪያ የተከሰተው ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ድርቅ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ ተሰደዋል፡፡ የእርሻ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡ ድርቁ በሀገሪቱ ከነበረው ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ውጥረቶች ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ ግጭት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ እንዲሁም በሀገራችን በ21966ዓ.ም እና በ1977ዓ.ም የተከሰቱ ድርቆች ምን ያህል ሀገራችንን አጎሳቁሎ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡

ሌላው እ.አ.አ ከ1997 እስከ 2009 የአውስትራሊያ የሚሊኒዬም ድርቅ  በሀገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ረጅሙና ከባዱ አደጋ የደረሰበት ወቅት ነበር፡፡ በድርቁም የወንዞች የውኃ መጠን በጣም ቀንሷል፡፡ የግብርና ምርት እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚም ተጎድተዋል፡፡ ሁኔታውም ሀገሪቱ የውኃ አስተዳደር ፖሊሲዎቿን እንደገና እንድትቀርጽ አስገድዷታል፡፡

አሁናዊ ክስተቶች

የዓለም የአየር ንብረት ትንያ (ሜትሮሎጂ) ድርጅት (WMO) እንዳስታወቀው እ.አ.አ በ2026 ኃይለኛ የኤል ኒኖ  ክስተት የመፈጠር ዕድሉ 80 በመቶ መድረሱን አስጠንቅቋል፡፡ ይህም በአውስትራሊያ፣ በደቡብ እስያ፣ በመካከለኛው አሜሪካ እና በኢንዶኔዢያ ድርቅን ሊያባብስ ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር የሙቀት ማዕበሎችም እንደሚጨምሩ ገልጿል፡፡

በተያያዘም በላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ድርቅ፣ ከፍተኛ ሙቀትና ጎርፍ ተደራርበው የሚሊዮኖችን ሕይወት እየፈተኑ ነው፡፡ የዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅት የውኃ እጥረት፣ የምግብ አቅርቦት መቀነስ እና መፈናቀል እየጨመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በድርቅ ምክንያት በአሜሪካ የግብርና ምርት መጎዳቱን ሮይተርስ ዘግቧል፤ በሀገሪቱ ሰፋፊ ሜዳማ ክልሎች ያለው ድርቅ የ2026/27 የክረምት ስንዴ ምርትን በመቀነስ እ.አ.አ ከ1957 ወዲህ ዝቅተኛውን የምርት ግምት አስመዝግቧል፡፡ ይህ በዓለም የምግብ ዋጋ ላይ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥር ይችላል፡፡

በአጠቃላይ እ.አ.አ የ2026 የድርቅ ታሪክ እንደሚያሳየው ድርቅ ከአካባቢ ችግርነት ወደ ዓለም አቀፍ የልማት፣ የምግብ ዋስትና፣ የጤና እና የደኅንነት ቀውስ ተቀይሯል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው የዛሬው ጥያቄ “ድርቅ ይመጣል ወይ?” የሚል አይደለም፤ “እንዴት እንዘጋጅ?” የሚል ነው፡፡

ድርቅን እንዴት እንከላለከል?

ድርቅን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም፣ ተፅዕኖውን በእጅጉ መቀነስ እና ማሕበረሰቡ እንዲቋቋመው ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህም በመንግሥት፣ በማሕበረሰብ እና በግለሰቦች ትብብር ይሳካል፡፡

ሰዎች የደን ልማት ላይ በስፋት መሳተፍ እና ዛፎችን መትከል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ዛፎች የአፈርን እርጥበት ይጠብቃሉ፡፡ የውኃ ዑደትን በመደገፍ የዝናብ ሁኔታን ለማሻሻል ያግዛሉ፡፡ ይህን ውጤት ለማግኘትም የደን ጭፍጨፋን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

የውኃ ሀብት አስተዳደርን መንደፍ ደግሞ ሌላው መፍትሔ ነው፤ የዝናብ ውኃን በማሰባሰብ ለበጋ ወቅት ማከማቸት፣ ግድቦችንና የውኃ ማጠራቀሚያዎችን መገንባት፣ ውኃን በቁጠባ መጠቀም ጠቃሚ ነው፡፡ በዝናብ ብቻ ከመተማመን ይልቅ የመስኖ ግብርናን ማስፋፋትም ተገቢ ነው፡፡ ውኃን የሚቆጥቡ ቴክኖሎጂዎችን፣ ለምሳሌ ጠብታ መስኖን (drip irrigation) መጠቀም፣ እንዲሁም አነስተኛ ውኃ የሚያስፈልጋቸውን የሰብል ዝርያዎች መዝራት፣ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን ማከናወን፣ እርከን መሥራት፣ የዝናብ ውኃ ጥቅም ላይ ሳይውል እንዳይፈስ ቦዮችን መቆፈር እና  አፈር መሸርሸርን መከላከል ይገባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን በመከታተል ድርቅ ከመከሰቱ በፊት ዝግጅት ማድረግ፣ ለአርሶ አደሮች እና ለአርብቶ አደሮች ተገቢ መረጃ በወቅቱ ማድረስ ያስልጋል፡፡ የበካይ ጋዞችን ልቀት መቀነስ፣ ንጹህ የኃይል ምንጮችን መጠቀም እና የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎችን ማጠናከር ድርቅን ለመቋቋም እና ለመቀነስ ያስችላሉ፡፡

ሌላው የማሕበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን ሕዝቡ ስለ ውኃ ቁጠባና ስለ ድርቅ አደጋ እንዲያውቅ ትምህርት መስጠት ለነገ የሚተው ተግባር መሆን የለበትም፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የዝናብ ውኃ ማሰባሰብን ማስፋፋት፣ በድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎች የመስኖ ልማትን ማጠናከር፣ የደን ልማትን ማስፋፋት፣ አርሶአደሮችን ድርቅን የሚቋቋሙ ዘሮች እና ዘመናዊ የእርሻ ዘዴዎች እንዲጠቀሙ መደገፍ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ፣ ድርቅን ለመከላከል ቁልፉ ነገር ውኃን በጥንቃቄ መጠቀም እና ድርቅ ከመከሰቱ በፊት ተዘጋጅቶ መጠበቅ ነው፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 15  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here