ዘመናዊ የእርሻ አሠራርን በመተግበር ምርትና ምርታማነትን እናረጋግጥ!

0
6

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተበታተኑ የእርሻ ማሳዎችን በ2018/ 2019 የምርት ዘመን በኩታ ገጠም በማደራጀትየእርሻ ሥራውን ለማዘመን፣  ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ ተበጣጥሶ የሚገኝን መሬት በኩታ ገጠም ማደራጀትም ኾነ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን መጠቀምና ዘመናዊ የእርሻ ዘዴን መከተል ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው፡፡ የአርሶ አደሩን አላስፈላጊ ድጋም ይቀንሳል፡፡ የአርሶ አደሩን  በደቦ የመሥራት የቆየ ልምድን ይበልጥ በማጎልበት ተጋግዞ እንዲሁም ተደጋግፎ እንዲሠራ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መሬትን አሰባስቦ፣ በዘመናዊ መሣሪያ ተጠቅሞ በዘመናዊ ያሠራር ዘዴ ማምረት የሰብል እንክብካቤን ለማድረግ፣ የፀረ ሰብል ተባይን ለመጠቀም፣ ባለሙያ በየትኛውም ጊዜ ለሚያደርገው ሙያዊ ክትትልና ድጋፍም አመቺ ነው፡፡ ሰብልን  ሳይባክን  በወቅቱ በቀላሉ ለመሰብሰብም በእጅጉ ይረዳል፡፡

ይህ  ዘመናዊ  የእርሻ  ሥራ  በብዙ  የዓለማችን   ሀገራት ተተግብሮ  ውጤታማነቱ  ተረጋግጧል፡፡ ለምሳሌ በሕንድ፣ በፑንጃብና ሀርያና ግዛቶች አርሶ አደሮች መሬታቸውን በማሰባሰብና የእርሻ ሥራቸውን በትራክተር በማከናወን፣ ድካምን፣ ጊዜን እንዲሁም የምርት ብክነትን በመቀነስ፣ የምርት መጠንንና ጥራትን በመጨመር ከፍተኛ ውጤት አግኝተውበታል፡፡ ቻይናም ብትሆን የተበታተኑ የእርሻ ማሳዎችን በማሰባሰብና በዘመናዊ መሣሪያዎች ተጠቅማ በማምረት የምግብ ስብሏን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጋለች፡፡

ከዚህ አንጻር በተበጣጠሰ ኹኔታ የሚገኘውንና እጅግ ኋላ ቀር በኾነ ኹኔታ በበሬ እንዲሁም በፈረስ የሚታረሰውን ማሳ አሰባስቦ የእርሻ ሥራን በዘመናዊ መንገድ በማከናወን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑ እጅግ ይበል የሚያሰኝና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው፡፡ ከፍ ሲል የጠቃቀስናቸውና የሌሎችም ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ይህ ዘመናዊ አሠራር የምርትና ምርታማነት ዕድገት ማረጋገጫና በምግብ ሰብል ራስን መቻያ ኹነኛ ርምጃ እንደመሆኑ መጠን ለአፍታም ቸል ሳይባል በላቀ ትኩረት መቀጠል አለበት፡፡ዘመናዊ አሠራሩን ለመተግባር የተጀማመሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በተቀናጀ መንገድ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ማከናወን ይገባል፡፡

ትራክተሮችን ለማዘጋጀት፣ ነዳጅ ለማቅረብ፣ ምርጥ ዘርንና ማዳበሪያን በወቅቱ በበቂ መጠን ለማሠራጨት የሚደረገው ርብርብም ዘላቂ መኾን ይኖርበታል፡፡ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ እንደ በተመሳሳይ ማሳ ተመሳሳይ ሰብሎችን ማምረት፣ አረምን በወቅቱ ተከታትሎ ማረም፣ የኩትኳቶ ሥራን በጊዜው መሥራት፣ ሰብልን በየጊዜው መፈተሽና አጠራጣሪ ኹኔታ ሲኖር ማሳወቅ ያሉ ተግባራትን በትጋት ማከናወን አስፈላጊ ነው፡፡ከምንም ነገር በላይ ይህ ዘመናዊ ያሠራር ዘዴ በሚፈለገው ልክ ሊተገበርና ስኬታማ መኾን የሚቻለው በአርሶ አደሮች ንቁ ተሳትፎና ትጋት ስለሆነ አርሶ አደሮች  ያሠራሩን ጠቀሜታ ከፍተኛነት ተገንዝበው ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንዲነሱና  ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርጉ  መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አርሶ አደሮች ጠንካራውንና ለውጤት የበቃውን አርሶ አደር በማየት በመንፈሳዊ ቅናት ተነሳስተው ለላቀ ተግባርና ውጤት እንዲተጉ አንዳቸው ካንዳቸው ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ይገባል፡፡ ሌላው ትኩረት ሊያሻው የሚገባ ጉዳይ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ አርሶ አደሮች በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ ከማኅበራት እንዲሁም ከፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ከወዲሁ በዕቅድ ይዞ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

 

በኲር የሰኔ 15  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here