አዲሱ የሊጉ ንጉሥ

0
230

የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ በ2018 ዓ.ም የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማሸነፉን በይፋ አረጋግጧል፡፡ ክለቡ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከተፎካካሪው ነገሌ አርሲ ጋር ባደረገው የ36ኛ ሳምንት ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱን ተከትሎ ገና ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች እያሉት ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በታሪክ መዝገብ ላይ አዲስ ስም አስፍሯል፤ ለዓመታት የሊጉን ዋንጫ ሲናፍቅ ለነበረው ለሲዳማ ሕዝብ እና ለመላው የቡድኑ ደጋፊዎች አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

ሲዳማ ቡና በ1999 ዓ.ም በዳራ ወረዳ “ዳራ ከነማ” በሚል እንደተመሰረተ ከክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚሁ ዓመት በደቡብ ክልል የክለቦች ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ ታላቅ ስኬትን አስመዝግቧል፡፡ በሐዋሳ በተደረገው መላው የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ሀገሪቱ ሁለተኛ የሊግ እርከን አድጓል፡፡ ሳይውል ሳያድርም ስሙን ወደ “ሲዳማ ቡና” መቀየሩን መረጃዎች አስነብበዋል፡፡

በብሔራዊ ሊግ (የአሁኑ ከፍተኛ ሊግ) ለሁለት ዓመታት ጠንካራ ፉክክር ካደረገ በኋላ በ2001 ዓ.ም ወደ ፕሪሚየር ሊግ ተሸጋግሯል፡፡ ላለፉት 17 ዓመታት በሊጉ የቆየው ሲዳማ ቡና ዘንድሮ የሻምፒዮንነት ዘውድ ደፍቷል፡፡

በ2017 የክረምቱ የዝውውር ወቅት ከጊዜያዊ አሰልጣኙ አዲሴ ካሳ ጋር በስምምነት በመለያየት እና በምትካቸውም አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን በዋና አሰልጣኝነት በመሾም ነበር የክለቡ ወሳኝ የውድድር ዓመት የተጀመረው፡፡ ይህ ጅማሮም ለዘንድሮው የውድድር ዓመት የዋንጫ ጉዞ አስተማማኝ መሰረት የጣለበት ወሳኝ ወቅት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ክለቡ ዘንድሮ በሊጉ ካደረጋቸው 36 ጨዋታዎች 18ቱን አሸንፏል፤ ሰባቱን ሲሸነፍ፣ 11 ጨዋታዎችን ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል፡፡ የፊት መስመሩ ዘንድሮ በሊጉ እጅግ አስፈሪው እና የተጋጣሚን የኋላ ክፍል የሚያሸብር እንደነበር ቁጥራዊ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡  እስከ 36ኛ ሳምንት መርሀግብር ድረስ 42 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ይህም 44 ግቦችን ካስቆጠረው መቻል ቀጥሎ በሊጉ ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ ሁለተኛው ክለብ ሆኗል፡፡ የፊት መስመር ተጫዋቾች  ፈጣን ሩጫ፣ የቦታ አጠቃቀም ብቃት እና ከተከላካዮች ጀርባ የሚፈጥሩት ክፍተት የማጥቃት አቅማቸውን እጅግ ገዳይ አድርጎታል፡፡

በአማካይ ክፍሉ የነበሩት ፈጣሪ አማካዮች ኳስን በማረጋጋት፣ ሰንጣቂ እና ገዳይ ኳሶችን ለመስፍን ታፈሰ እና ለአቤል ያለው በመስጠት ቡድኑ በማንኛውም ጨዋታ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲኖረው አድርገዋል፡፡ በተለይም ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ተጋጣሚ ቡድንን በተደጋጋሚ ሲያፈራርስ  ዐይተናል፡፡

የኋላ ክፍሉም በቀላሉ የማይረበሽ ሲሆን በሊጉ አነስተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው ክለቦች ውስጥ ቀዳሚ ክለብ ነው-ሲዳማ ቡና፡፡ “ማጥቃት ጨዋታን ያሸንፋል፤ መከላከል ግን ዋንጫ ያመጣል” የሚለው የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን  የእግር ኳስ አስተሳሰብ ዘንድሮ በሲዳማ ቡና ጉዞ ላይ በተግባር ዐይተነዋል፡፡ ከተከላካዮች የሚጠበቀው የአካል ብቃት፣ የአየር ላይ ኳሶች ቁጥጥር እና ከስህተት የጸዳ የሽፋን አሰጣጥ ለቡድኑ አስተማማኝ ደጀን በመሆን ለዋንጫው ጉዞ ትልቁን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ እስከ 36ኛ ሳምንት መርሀግብርም 22 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩበት፡፡

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በውድድር ዓመቱ ተለዋዋጭ የታክቲክ ፍልስፍናዎችን በመተግበር  እና ተጭኖ በመጫወት ለተጋጣሚ አስቸጋሪ የሆነ ቡድን ፈጥረዋል፡፡ ተቃጣሚዎች ከተከላካይ መስመር ኳስ መስርተው በነጻነት እንዳይወጡ ማድረግ አሰልጣኙ በሲዳማ ቤት ሲተገብሩት የነበር ሀሳብ እንደነበር በዚህ ዓመት ተመልክተናል፡፡ ተጫዋቾች እስከ ጨዋታው ፍጻሜ ድረስ ትኩረታቸውን እንዳያጡ በማድረግ እና በተለይ ባለቀ ሰዓት ነጥባቸውን ለማስጠበቅ ጠንካራ ስነ ልቦና መገንባት ችለዋል፡፡

የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ዘንድሮ ያሳዩት ድጋፍ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በልዩ ሁኔታ የሚጠቀስ ነው፡፡ ክለቡ በሚጫወትባቸው ስታዲየሞች ሁሉ በባህላዊ አልባሳት፣ ልዩ በሆኑ ዜማዎች እና በሰንደቅ አላማዎች  በማሸብረቅ ለተጫዋቾቹ “12ኛው ተጫዋች” መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ የደጋፊዎች የማያቋርጥ ድጋፍ ቡድኑ ሜዳ ላይ በሚቸገርበት ወቅት እንኳ ተጨማሪ ጉልበት በመሆን  እንዲያሸንፍ አድርጎታል፡፡

ሲዳማ ቡና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የ2018 ዓ.ም የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነቱን ቢያረጋግጥም በውድድር ዓመቱ በደካማ ጎንነት የሚጠቀሱ ክፍተቶች እንደነበሩት ግን አይካድም፡፡ በተለይም ቡድኑ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የሚያሳየውን አስፈሪ ጥንካሬ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ መድገም ሲሳነው ተስተውሏል፡፡ ከፍተኛ የስነልቦና ችግር እና የትኩረት ማጣት እንደነበረበት ጥቂት በማይባሉ መርሀግብሮች ላይ ዐይተነዋል፡፡

በቀላሉ ነጥቦችን አሳልፎ እንዲሰጥ እና በተለይም በጠንካራ ተፎካካሪዎቹ ላይ የበላይነቱን ሙሉ በሙሉ እንዳይወስድ እንቅፋት ሲሆንበትም ተመልክተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ የኋላ ክፍል በተለይ በአንድ አንድ ክለቦች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ጥቃት ሲፈጸምባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በተለይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከሚጫወቱት  ኢትዮጵያ መድን እና መቻልን ከመሰሉ ጠንካራ ክለቦች ጋር በነበሩ ጨዋታዎች ላይ የሲዳማ ቡና ትልቁ ክፍተት ተጋልጧል፡፡

ቡድኑ በተወሰኑ ወሳኝ ጨዋታዎች ላይም የኋላ ክፍሉ የአቋም መዋዠቅ ገጥሞት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ከነገሌ አርሲ፣ ከአዳማ ከተማ፣ ከኢትዮጵያ ቡና እና ከመሳሰሉ ክለቦች ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች የክለቡ ድክመት በግልጽ መታየቱን ከሶከር ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ ሲዳማ ቡና ይህን ችግር በቀጣይ ካላስተካከለ በአህጉራዊው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል ብዙዎች ስጋት አድሮባቸዋል፡፡

ሲዳማ ቡና ዘንድሮ የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው በረጅም ጊዜ እቅድ፣ በጠንካራ ሥራ እና በጥሩ የቡድን መንፈስ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የክለቡ ትኩረት ወደ አህጉራዊው የውድድር መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ወክሎ በሚሳተፍበት የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ ላይ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ክለቡ ከአሁኑ ስብስቡን ማጠናከር እና ዝግጅት መጀመር ይኖርበታል- የእግር ኳስ ቤተሰቡ አስተያየት ነው፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here