የቻይና ኩንሻን ከተማ ከታች መሰረቱ ሰፍቶ አናቱ ጠቦ ወይም ቀጥኖ በ“ ፒራሚድ” ቅርጽ በተገነባው ባለ 18 ፎቅ የጋራ መኖሪያ ህንፃ መገኛነቱ ታዋቂ ሊሆን መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በሆካዮ ግዛት ኩንሻን ከተማ በ2013 እ.አ.አ በልዩ “ፒራሚድ” ቅርጽ ግንባታው የተጠናቀቀው የጋራ መኖሪያ ቤት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጐብኚዎችን ቀልብ መሳቡን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በትክክለኛው የ “ፒራሚድ” ህንፃ የኩንሻኑ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለሁለት ጐን ሽቅብ ወደ ላይ እየቀጠነ የሚሄድ ግንብ ተገንብቶላቸዋል፡፡ የመኖሪያ ክፍሎቹ ከላይ ወደታች በ45 ዲግሪ ወይም መታጠፊያ ማእዘን ተሰድረው ነው የተሰሩት፡፡ ያም ለተመልካች ዓይን ሳቢ አድርጓቸዋል፡፡
በፒራሚድ ቅርጽ የጋራ መኖሪያ ህንፃውን ንድፍ ለሰራው አካል የቻይና ነባር የተራራዎች ላይ ሩዝ ማልሚያ የእርከን ማሳ ለንድፉ መነሻ እንደሆነው ነው ያብራራው፡፡
የጋራ መኖሪያ ህንፃው ቅርጽ ልዩ እና ሳቢ ቢሆንም እያንዳንዱ ፎቅ ቤት ከላይ ወደታች ሰፊ በረንዳ እንዲኖረው አስገድዷል፡፡ ይህም የጋራ መኖሪያ ህንፃው ቅርጽ በራሱ የተለያዩ እንከኖች ወይም ጉድለቶች እንዲስተዋሉበት መንስኤ ሆኗል ነው የተባለው፡፡
በመሆኑም ከውጪ ፊት ለፊት ከተገነቡት ቤቶች ጀርባ ወይም የውስጥኛው ክፍሎች ብርሃን አልባ መሆናቸው፣ ዓየር እንደተፈለገ የማይንሸራሸርባቸው፣ በውጪኛው ገፅ ከሚታዩት ውጪ ለሚገኙት ክፍሎች የእሳት አደጋ ቢነሳ ለማጥፋት አስቸገሪ መሆናቸው በግንባታው እንከንነት መጠቀሳቸውን ድረ ገጹ በማደማደሚያነት አስነብቧል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


