ቅኔ ቃሉ የግዕዝ ነው፡፡ ቀነየ፣ ገዛ መገዛት ከሚል አንቀጽ ይረባል፡፡ ከተግባሩ አንጻር ደግሞ ቅኔ ማለት መገዥያ፣ ማምለኪያ፣ ማመስገኛ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ፈጣሪውን ስላመሰገነበት፣ በምስጋና ስለተገዛበት ቅኔን የጀመረው እሱ ነው ይባላል፡፡ በኋላም ደቀ እስጢፋ፣ ዩሐንስ ገብላዊ፣ ተዋነይ እና ሌሎች የቅኔ ሊቃውንት እያሰፉት እና ቅርጽ እና ስርዓት እያስያዙት ቀጥለዋል፡፡
“ቅኔን መልክ፣ ቅርጽ፣ ሥርዓት፣ ቤት ሰጥተው፣ በቁጥር ወስነው የአሁኑን የቅኔ ውበት የሰጡት ሐዊራ፣ መንክራ፣ እስክንድራ፣ ፓኦድራ፣ አቦድራ፣ ይባላሉ” በማለት ትርጓሜ ቅኔ ፈለገ ሕይወት በተሰኘው የጋራ መጽሀፋቸው አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑል እና ቀሲስ ከፍ ያለው መራሒ በ1992 ዓ.ም በሳተሙት መጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡
ዛሬ በሕዝብ የተለመደው ሰም እና ወርቅ ቅኔ እዚህ እንዲደርስ ብዙ ሊቃውንት ለዓመታት ተራቀውበታል፡፡
“ቅኔን በእሳት ሠረገላ ተቀምጠው፣ በነፋስ ክንፍ በረው፣ በጥልቁ ባሕር ላይ ያለ መርከብ ነው፣ ያለ ጀልባ ተመላልሰው፣ በደመና ተጭነው፣ ብዙ አስተምረው፣ ባሕሩን ገስጸው በታሪክ የሚመሰገኑት የሀገራችን ሊቃውንት ዋና ዋናዎቹ ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ደቅ እስጢፋ የተባለው የቅኔ ፈላስፋ ነበር፡፡በ1460 በአጼ በእደ ማርያም ዘመነ መንግሥት በሕይወት እንደኖረ ይነገርለታል፡፡ ሁለተኛው ተዋነይ ነው፡፡ ከ1701 እስከ 1723 ዓ.ም በሕይወት የኖረ የቅኔ ፈላስፋ ነበር፡፡ ሲበዛ የቅኔ ምትሀተኛ ነበር ይባላል፡፡ ሦስተኛው ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ ነው፡፡ ከ1687 እስከ 1726 ዓ.ም በሕይወት ኖሯል፡፡” በማለት ትርጓሜ ቅኔ ፈለገ ሕይወት የተሰኘው መጽሐፍ አስፍሯል፡፡
በቅኔ ምስጋና፣ ክብር፣ ደስታ፣ ኀዘን፣ መገፋት፣ ዘመን እና ታሪክ በአጠቃላይ በዓለም የሚታይና የሚከናወን የሕይወታ መልክ ሁሉ ይዳሰሳል፡፡ ቅኔ መፈላሰፊያ ነው፡፡ ቅኔ የትምህርት መንገድ ነው፡፡ ቅኔ ነገሮችን ማራቀቂያ ነው፡፡ ቅኔ አዕምሮን ማጎልበቻ ነው፡፡ ቅኔ የምስጢር ጥበብ ነው፡፡
ቅኔ ልዩ ልዩ መንገዶች አሉት፡፡ ሰም እና ወርቅ፣ ሰም ገፊ፣ ውስጠ ወይራ፣ አገናኝ፣ አታላይ፣ ጽድቅ፣ አንጻር፣ ሙሻ ዘር፣ ንጽጽር፣ ኅብር፣ስም ጥቅል፣ ውስጠ ዘ እና ሌሎችም ብዙ የቅኔ መንገዶች አሉ፡፡
ቅኔ ዓይነቶች /ክፍሎችም አሉት፡፡ ጉባኤ ቃና፣ ዕዝልና ግእዝ፣ ዘአምላኪየ፣ ሚበዝኁ፣ ዋዜማ፣ አጭር ዋዜማ፣ ዕጣነ ሞገር ግእዝ፣ ዕጣነ ሞገር ዕዝል እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
ቅኔ ሁልጊዜ አዲስ ነው፡፡ በሁኔታው፣ በጊዜው ታስቦ ይቀርባል፡፡ ካደረ በኋላ ወይም አንድ መድረክ ላይ ከቀረበ በኋላ በድጋሚ አይቀርብም፡፡ ሁልጊዜ እንደ ትኩስ ምግብ አዲስ ሆኖ ይቀርባል፡፡
በቅኔ ሃይማኖትን፣ ሥነ ምግባርን፣ ትሕትናን፣ ፍቅርን፣ ሞትን፣ ትምህርተ ሕይወትን፣ ጸሎትን፣ ተመስጦን አባቶች ሲያስተምሩ ኑረዋል፡፡ በቅኔ የፈለጉትን ማለት ይቻላል፡፡ ሊቃውንት በቅኔ ብሶታቸውንም ይገልጹ ነበር፡፡ ቅኔን ለምሥጋናም፣ ለዘለፋም፣ ለተግሣጽም፣ ውዳሴም፣ ለአቤቱታም መግለጫ አድርጎ መጠቀም ይቻላል፡፡
ከብዙ የቅኔ መንገዶች አንዱ ሰም እና ወርቅ ኢትዮጵያዊያን በብዛት የሚጠቀሙበት ሆኖ አገልግሏል፡፡ ፈደል ያልቆጠሩት ልብ ብርሀን ሰዎችም በሰም እና ወርቅ ግጥም ሀሳባቸውን ሲገልጹ ኖረዋል፡፡ ሰም እና ወርቅ ግጥም ብዙ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ በስፋት ሲቀርብ ቀጥሏል፡፡
የቤተመንግሥት ሰዎች፣ አዝማሪዎች፣ የንጉሥ ባለሟሎች፣ የቅኔ ሊቃውንት፣ ከበርቴዎች፣ ጭሰኞች፣ እና ሌሎችን ሰዎች ሰም እና ወርቅ ቅኔዎችን በማቅረብ ሀሳባቸውን ሲገልጹበት ኖረዋል፡፡
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የታወቁ የልጅ እያሱ አዝማሪ ነበሩ፡፡ እሳቸው በርከት ያሉ ሰም እና ወርቅ ቅኔዎችን በመቀኘት ይታወቁ ነበር፡፡ በልጅ ኢያሱ ዘመን ጉልህ ፖለቲካዊ ተሣትፎ ነበራቸው፡፡ ለልጅ ኢያሱም የተለየ አክብሮት ነበራቸው፡፡ በፍቅርም ውስጥ ምስጢርን ለማስቀመጥ ሰም እና ወርቅ ግጥሞች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ይልማ ገብረአብ ለኤፍሬም በሰጠው እልፍ አዕላፍ ዘፈን ውስጥ የሚወዳትን ፍቅረኛውን ደብቆ አስቀምጧታል፡፡ ጋዜጠኛ ደረጄ ኃይሌ ምስጢር እስኪያወጣ ድረስ ማንም እልፍነሽን አላወቃትም ነበር።
መውደዱን ሰው ቢገምት በሺ
እኔም እልፍ እላለሁ እልፍ አዕላፌ ነሽ
ብሎ በስውር ፍቅረኛውን አፋችን ውስጥ ሁልጊዜ እንድንጠራት አድርጓል፡፡
ይልማ ገብረአብ እንዲህ ዓይነት ሌላም ስራ አለው፡፡ ለሙሉቀን መለሰ በጻፈለት ዓይኔማ ወዳጅሽ ዘፈን ውስጥ ምስጢር ቋጥሮ አስቀምጧል፡፡ የይልማ የመጀመሪያ ፍቅረኛው ዓይናለም እዚህ ዘፈን ውስጥ አለች፡፡ በዚህ ዘፈን ፍቅሩን፣ ናፍቆቱን፣ ብሶቱን እና ቁጭቱን ለዓይናለም ሲያዜም እንሰማዋለን፡፡
በሌሎችም የሀገራችን ዘፈኖች ውስጥ ሰም እና ወርቅ ቅኔ ጉዳትን ቀንሶ፣ ሐሳብን አለስልሶ ለአድማጭ በማድረስ የሕዝብን ዕይታ እየገራ ቀጥሏል፡፡ ምናልባትም በወቅቱ በቀጥታ ቢቀርቡ ሊያስገድሉ የሚችሉ ሐሳቦች ተሸፍነው በቅኔ ይቀርባሉ፡፡
ሰም እና ወርቅ ሀሳብን ካለተጠያቂነት፣ ግጭትን ቀንሶ የማቅረብ ጥበብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያዊያን ቅኔ ያውቃሉ፡፡ “ይህ እማ እገሌን ለማለት ነው፤ እንዲህ የተባለው እኮ እንትና ነው” እያሉ የኪነ ጥበብ ስራዎችን ስውር ቅኔ ይፈታሉ፡፡
ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን የቅኔ ከዋክብት በሚል በ1990 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው በሰም እና ወርቅ ቅኔ የሚታወቁትን ወተዜር ፈንታን አንስተዋቸዋል፡፡ ወተዜር ፈንታ በአዴት ዙሪያ ይኖሩ የነበሩ መሀን ጋለሞታ ሴት ነበሩ ይባላል፡፡ የታወቁ የሰም እና ወርቅ ሙሾ አውራጅ ነበሩ፡፡
ዛሬ እሳቸው የተወለዱባት ቦታ ወተዜር ኪዳነ ምሕረት በመባል ትጠራለች፡፡ በመሳፍንቱ የአገዛዝ ዘመን አድገው እስከ አጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ድረስ በሕይወት ኖረዋል፡፡
እሪ ብየ ብጮህ ሴቱ ብቻ ወጣ
ኧረ ምነ ይሁን አገሬ ወንዳጣ
የሚለው ሰም እና ወርቅ ቅኔ የእሳቸው ነው፡፡ የተነገረበት አውድም እንዲህ ነበር፡፡ ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በተደረገ ጦርነት ብዙ ሰው ይሞታል፡፡ ቦታው ደግሞ ከባህርዳር ወጣ ብሎ የሚገኘው ወንድ አጣ የተባለው ቀበሌ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ስፍራው ወንዳጣ ተብሎ ይጠራ ጀመረ፡፡
እንጅባራ ላይ በተደረገ ጦርነት አጼ ቴዎድሮስ ከጎጃም ወደ በጌምድር ሲሻገሩ ሠራዊታቸው ከፍተኛ ዝርፊያ አድርጎ ነበር፡፡ የቴዎድሮስን ድርጊት በብርቱ የሚቃወሙት ወተዜር ፈንታ የሚቀጥለውን ቅኔ አሰሙ፡፡
አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ
በሉ እንዲህ ለብልቦ ቆጥቁጦ ይፍጃችሁ፡፡
በዚህ ንግግራቸው በኋላ ቴዎድሮስ ወደ ደብረ ታቦር ሲመለሱ ምርኮኛ ሆነው ወደዚያው ተጋዙ፡፡ በዚያም መንገላታት ደርሶባቸው ነበር ይባላል፡፡ በሒደት ግን የግጥም ችሎታቸው፣ አነጋገራቸው እና ምክራቸው ቴዎድሮስን ማራራት ጀመረ፡፡ በሒደትም የቴዎድሮስ ባለሟል ሆኑ፡፡ በየወሩ አንድ ማድጋ እህል እየተሰፈረላቸው መኖር ጀመሩ፡፡
ወተዜር ቴዎድሮስን እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ አልተለዩዋቸውም ነበር፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሲሞቱ የሚከተለውን ግጥም የተናገሩት እሳቸው ነበሩ፡፡
መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ አሉ ሲሉ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ጽፈዋል፡፡
አንድ የድሮ ተማሪ አዘና ወደ ሚባል ቦታ ለቅኔ ትምህርት ይሄዳል፡፡ ከዚያም በተማሪዎች ጎጆ እሳት ይነሳና ተማሪው በዚያው ይሞታል፡፡ በዚህ ልቧ ያዘነ እናት እንዲህ ብላ በሰም እና ወርቅ ለቅሶ ላይ በሙሾ ተቀኜች፡፡
ይማርልኝ ብየ ዋሸራ ሰድጄ
ቀለም ገባው አሉ እሳት ሆነ ልጄ፡፡
አማርኛ ቅኔ ከነመፍቻው የሚለው መጽሐፍ ያቀረበውን ቅኔ በመጥቀስ እንሰነባበት፡፡
ረዥም አይደል አጭር
ወፍራምም አይደል ቀጭን
ታግሎ የጣለኝ ከሰው ደጅ
እኔን ያኸል ነው እንጂ፡፡
ሰሙ ወይም ግልጹ መልእክት ከኔ የማይበልጥ የአካል ግዝፈት የሌለው አጭር፣ ቀጭን ሲሆን ታግሎ ጣለኝ፤ እኩያዬ የሆነ ሰው አሸነፈኝ ይላል፡፡ ምስጢሩ እኔን ያደከመኝና ያብረከረከኝ ረሀብ ነው፤ የትም ወድቄ የቀረሁት ችግር ጠንቶብኝ የምበላው እኸል አጥቼ ነው የሚል ነው፡፡
ማረፊያ
አማርኛ ቅኔ
አርባ ስድስት ዓመት የገዛኸው ንጉሥ፤
እንዳለህም ስጠኝ፤ እንደሌለህ ላልቅስ፡፡
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


