በክልሉ  ከ1 ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጐች የሥራ እድል ተፈጥሯል

0
32

የወጣቶችን የሥራ ተሳትፎ ማሳደግና ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ከኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎች መካከል ዋነኛ ስፍራ የሚይዝ ጉዳይ ነው። በ2018 በጀት ዓመት መንግሥት በሥራ ፈጠራ፣ በክህሎት ልማት እና በሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ላይ ያከናወነው የተቀናጀ እንቅስቃሴ የሚታይ ውጤት ማስመዝገቡን የፌዴራል መንግሥት አፈጻጸም ሪፖርት ያመለክታል።

የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት  በዓመቱ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል  4 ነጥብ 9 ሚሊዮን በሀገር ውስጥ እንዲሁም  600 ሺህ ዜጎች ደግሞ በሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ሆነዋል። በተጨማሪም ከ40 ሺህ በላይ ወጣቶች በርቀት ሥራ (Remote)  ገቢ ማግኘት ችለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ 13 በመቶ ማደጉን ሪፖርቱ ያሳያል። በሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትም 27 በመቶ እድገት መመዝገቡ መንግሥት በሥራ ገበያ ማስፋትና በሕጋዊ የውጭ ስምሪት ላይ የወሰደው አቅጣጫ ውጤት እያመጣ መሆኑ ተመላክቷል።

ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ማምረት  ሥራ ማስገባት የኢኮኖሚ እድገትን፣ የማኅበራዊ መረጋጋትንና ዘላቂ ልማትን የሚያጠናክር መሠረታዊ ጉዳይ  መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ ሥራ ያገኘ ወጣት ገቢ ያመነጫል፣ ቤተሰቡን ይደግፋል፣ ለመንግሥት የግብር ገቢ ያበረክታል፣ የፈጠራ ሀሳቦችን ያመጣል እንዲሁም የሀገሪቱን አምራችነት ያሳድጋል። በተቃራኒው የሥራ አጥነት መባባስ ድህነትን፣ ወንጀልን፣ ሕገ-ወጥ ስደትንና የሰው ኀይል ብክነትን በማባባስ በሀገራዊ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

በኢትዮጵያም በተለይ በከተሞች ከከፍተኛ ተቋማት ትምህርታቸውን ጨርሰው የተመረቁ ሥራ አጥ ወጣቶች ጉዳይ አሁንም የሚያሳስብ ችግር ነው። የትምህርት ማረጋገጫ ብቻውን የሥራ ዋስትና እንዳልሆነ ብዙዎች በተግባር እየተገነዘቡት ነው። ይሁን እንጂ በመደራጀት፣ አዳዲስ ክህሎቶችን በመማርና የተፈጠሩ ዕድሎችን በመጠቀም ሕይወታቸውን መቀየር የቻሉ ወጣቶችም አሉ።

የወጣት ሰናይት ነጋ ተሞክሮ ይህን በግልጽ ያሳያል። በባሕር ዳር ከተማ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለው ቤተሰብ ያደገችው ሰናይት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ባለማምጣቷ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በቱሪዝም ዘርፍ ተምራ በዲፕሎማ ተመርቃለች። ሆኖም በተማረችበት ሙያ ከመንግሥትም ሆነ በሌሎች ተቋማት ተቀጥራ የመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራትም  ባለማግኘቷ ለሦስት ዓመታት ያህል ሥራ አጥ ሆና ቆይታ ነበር። ከዚያ በኋላ በክፍለ ከተማዋ በተመቻቸ የሥልጠና ዕድል የልብስ ስፌት ሙያ  ሰለጠነች፡፡

ሰናይት ከስልጠና በኋላም ከአምስት ጓደኞቿ ጋር በመደራጀት የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ማምረት ጀመረች። ወጣቶቹ በመንግሥት የመሥሪያ ቦታም አግኝተዋል፡፡ እንደ ሰናይት ገለጻ ሥራው ገቢ ከማስገኘቱ በተጨማሪ በራሷ እንድትተማመን አስችሏታል። ሆኖም የመሸጫ ሱቅ እጥረት አሁንም ዋና ፈተናቸው በመሆኑ እንዲሰጣቸው ጠይቃለች፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ወጣት አሸናፊ ላቀው    በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ በከፍተኛ ውጤት ተመርቋል፡፡ ወጣቱ ለትምህርት ባለው ፍላጎት ተጨማሪ ሁለት ዲግሪዎችንና የማስተርስ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ ይሁንና  በተማረባቸው የትምህርት  መስኮች ተቀጥሮ የመሥራት ፍላጎት ቢኖረውም   ማግኘት አልቻለም። የኋላ ኋላ ግን ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በፓርኪንግ አገልግሎት ከዚያም በከተማ ጽዳትና ውበት ሥራ ተሰማርቷል።

እንደ አሸናፊ ገለጻ አሁን የሚያገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ የሕይወት ለውጥ ባያመጣም ከቤተሰብ ጥገኝነት  ወጥቶ በራሱ መተዳደር ጀምሯል። አሁንም የንግድ አዋጭ ጥናት(የቢዝነስ ፕሮፖዛል) በማዘጋጀት ብድር ለማግኘት ጥረት እያደረገ ቢሆንም የመያዣ ዋስትና መስፈርት ዋና እንቅፋት እንደ ሆነበት ጠቁሟል፡፡

ለወጣቶች የሚዘጋጅ የብድር አገልግሎት  የወጣቶችን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበና ተደራሽ ሊሆን እንደሚገባም አሸናፊ ጠይቋል። እንደ ወጣቱ ገለጻ መንግሥትና አጋር ተቋማት ከሥልጠና በኋላ በገበያ፣ በፋይናንስና በሥራ ቦታ ተደራሽነት ላይ የበለጠ ድጋፍ ቢያደርጉ ብዙ ወጣቶች ከሥራ ፈላጊነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት ሊሸጋገሩ ይችላሉ።ሥራን አለመናቅ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን መማርና በመደራጀት መሥራት ከሥራ አጥነት ወደ ምርታማነት የሚያሸጋግር  መንገድ በመሆኑ አቻዎቹ የእነሱን ተሞክሮ እንዲከተሉም ምክሩን ለግሷል፡፡

በአማራ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት ከአንድ ነጥብ አንድ  ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጿል። የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ ለበኵር እንደገለጹት  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  በ11 ወራት አንድ ሚሊዮን 96ሺህ  ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች  የሥራ ዕድል አግኝተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 876ሺህ 859 ቋሚ ሲሆኑ 219ሺህ 371 ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን ያገኙ ናቸው። ከተጠቃሚዎቹ 569ሺህ 490 ወንዶች ሲሆኑ 536ሺህ 740 ደግሞ ሴቶች ናቸው።  ክንውኑ ከ2017  በጀት ዓመት  የ11 ወራት ክንውን ጋር ሲነጻጸርም ከ142 ሺህ በላይ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ነው አቶ አንዳርጋቸው የጠቆሙት።

የሥራ እድሉ ከተፈጠረላቸው ውስጥ 655ሺህ 411 በከተማ እና  450 ሺህ 819 በገጠር የሚኖሩ ዜጎች ሲሆኑ ፤ከዚህ በተጨማሪም 5ሽህ 218 ተፈናቃዮች፣ 2ሽህ 853 አካል ጉዳተኞች እና 9ሺህ 65 ከስደት ተመላሾች ተጠቃሚ ሆነዋል።

እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለጻ  በክህሎት ልማት ዘርፍም 568ሺህ 116 ዜጎች የቴክኒካል ክህሎት እንዲሁም 974ሺህ 19 ሰዎች ደግሞ የኢንተርፕረነርሺፕ ስልጠና ተከታትለዋል። ስልጠናዎቹ በግንባታ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ፣ በመረጃና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታል ማርኬቲንግ እና በመሳሰሉት ዘርፎች ሥልጠና ማግኘታቸውንም  ነው ያብራሩ። የሙያ ስልጠናው ከገበያ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም በየሁለት  እና ሦስት ዓመቱ ቢሮው ወደ ሥራ ለማሰማራት የገበያ ጥናት እንደሚያካሂድ፣ ከኢንዱስትሪዎች፣ ከግል ዘርፍና ከመንግሥት ፕሮጀክቶች ጋር በትብብር የስልጠና ካሪኩለሞችን እንደሚያዘምን ተናግረዋል።

በኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፉም 64ሺህ 281 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመዋል። ለ56ሺህ 651 ኢንተርፕራይዞች ከ7ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል፤ 42 ሺህ 420 ኢንተርፕራይዞች ደግሞ የ8 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ማግኘታቸውንም ተናግረዋል። በተጨማሪም 33ሺህ 294 ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩ።

አቶ አንዳርጋቸው አክለውም በመሠረተ ልማት ዘርፍ 21 ሺህ 323 ሄክታር መሬት  በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ዜጎች ለሥራ ከተዘጋጀው 13ሺህ 565 ሄክታር መሬት  ለሥራ ውሏል፤ በዚህም 2 ሺህ 277 ሼዶች ለ7ሺህ 747 ኢንተርፕራይዞች እና 29ሺህ 903 አንቀሳቃሾች ተላልፈዋል ነው ያሉ። በሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትም 141ሺህ 505 ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ማንኛውም ወደ ውጭ  የሚሄዱ ዜጎች ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት  የ21 ቀናት  የቅድመ ስልጠና፣ የቋንቋ፣ የሙያ፣ የመብትና ግዴታ፣ የባህል እንዲሁም የደህንነት ግንዛቤ ስልጠና እንደሚያገኙ ነው የተናገሩ።

ይሁን እንጂ የክህሎት ስልጠና አቅም ውስንነት፣ የባዮሜትሪክስ አገልግሎት እጥረት፣ የፓስፖርት መዘግየት፣ የመረጃ ሥርዓት ክፍተትና የመሣሪያ እጥረት እንደ ዋና ተግዳሮቶች ተለይተዋል። ለእነዚህ የባለሙያ አቅም ግንባታ፣ የፌዴራል ተቋማት ትብብር ማጠናከር፣ የባዮሜትሪክስ መሣሪያዎችን ማስፋፋትና የመረጃ ሥርዓቱን ማሻሻል እንደ መፍትሔ ተጠቅሰዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመት(2019) ቢሮው ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የሙያ ስልጠናን ለማስፋት፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንን ለማጠናከር፣ የአገልግሎት ሪፎርሙን ወደ ተግባር ለማሸጋገርና የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማረጋገጥ ትኩረት እንደሚደርግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ የ2018 በጀት ዓመት ውጤቶች በሥራ ፈጠራና በክህሎት ልማት ዘርፍ መሻሻል መኖሩን ቢያሳይም የገበያና የብድር  ተደራሽነት፣ የፋይናንስ አገልግሎት፣  የቴክኒክ ድጋፍ እና የመሸጫ ቦታ በተያዘው በጀት ዓመትም የተጠናከረ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አቶ አንዳርጋቸው አስገንዝበዋል፡፡

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሐምሌ 6  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here