ባርባዶስ

0
55

ከነጭ የባሕር ዳርቻዎችና ከአረንጓዴ ተፈጥሮዋ ባሻገር፣ ባርባዶስ የቅኝ ግዛት ታሪክን ወደ ዴሞክራሲ ስኬት የቀየረች፣ በባህል፣ በቱሪዝም እና በሕዝቧ እንግዳ ተቀባይነት ዓለምን የምታስደንቅ ደሴት አገር ናት።

በካሪቢያን ክልል የሚገኙ ደሴት አገራት እያንዳንዳቸው የራሳቸው የተለየ ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሯዊ ውበት አላቸው። ከእነዚህ መካከል ባርባዶስ በስፋቷ ትንሽ ብትሆንም በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ካርታ ላይ ትልቅ ቦታ ያላት አገር ናት። በንጹህ የባሕር ዳርቻዎቿ፣ በቀለማት በተሞላ ባህሏ፣ በሙዚቃዋ፣ በስፖርቷ እና በታሪኳ የተነሳ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን ትስባለች።

ባርባዶስ በምሥራቃዊ የካሪቢያን ክልል፣ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ የምትገኝ ደሴት አገር ናት። ከሌሎች የካሪቢያን ደሴቶች ይልቅ ወደ ምሥራቅ ስለምትገኝ በቀጥታ የአትላንቲክ ማዕበሎችን ትቀበላለች። ይህም ለተለያዩ የባሕር ስፖርቶች ተስማሚ ያደርጋታል።

የአገሪቱ ስፋት 430 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ 34 ኪሎ ሜትር፣ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ 23 ኪሎ ሜትር ያህል ትዘረጋለች። ዋና ከተማዋ ብሪጅታውን ሲሆን የንግድ፣ የቱሪዝም እና የመንግሥት ማዕከል ናት።

በአብዛኛው ጠፍጣፋ መሬት ያላት ሲሆን በመሃል አካባቢ ዝቅተኛ ኮረብቶች ይገኛሉ። ከፍተኛው ስፍራ 340 ሜትር ያህል ከፍታ ያለው ማውንት ሂላቢ ነው።

 

ከጥንታዊ ሰፈራ እስከ ሪፐብሊክ

ከአውሮፓውያን መምጣት በፊት ደሴቲቱ በአራዋክ እና በካሪብ ጎሳዎች ተይዛ ነበር። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የፖርቱጋል መርከበኞች ደሴቲቱን በማየታቸው “ባርባዶስ” የሚለውን ስም ሰጧት።

በ1627 እንግሊዝ በይፋ ቅኝ ግዛት አደረገቻት። በመቀጠልም የሸንኮራ አገዳ እርሻዎች በስፋት ተስፋፉ፤ ለእነዚህ እርሻዎች ሥራ በግዳጅ ከአፍሪካ የተወሰዱ ባሪያዎችን ተጠቀሙ። ይህ ታሪክ የአገሪቱን ሕዝብ፣ ባህልና ማንነት በጥልቅ ቀይሮታል።

በ1826 ዓ.ም ባርነት ከተሰረዘ በኋላ ሕዝቡ የፖለቲካ መብትና የማህበራዊ ፍትሕ ትግል ጀመረ። በ1966 ነፃነቷን አገኘች፣ በ2021 ደግሞ የንጉሣዊ ሥርዓቱን ቀይራ ሪፐብሊክ ሆነች። ይህ ለአገሪቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ነበር።

 

ተፈጥሮ የሰጣት ውበት

ባርባዶስ በነጭ አሸዋ፣ በግልጽ ሰማያዊ ውሃ እና በኮራል ሪፎች የተከበበች ናት። የምዕራብ ዳርቻዋ ጸጥ ያለ ባሕር ስላላት ለመዋኛና ለቤተሰብ መዝናኛ ተመራጭ ናት። የምሥራቅ ዳርቻዋ ደግሞ በታላላቅ ማዕበሎች ስለምትታወቅ የሰርፊንግ ስፖርት ማዕከል ሆናለች።

ሀሪሰንስ ኬቭ በዓለም የሚታወቅ የኖራ ድንጋይ ዋሻ ሲሆን በውስጧ የውሃ ፏፏቴዎች፣ የመሬት ውስጥ ወንዞች እና ውብ የድንጋይ ቅርጾች ይገኛሉ።

በተጨማሪም የባሕር ኤሊዎች፣ በርካታ የዓሣ ዝርያዎች እና ውብ የኮራል ሪፎች የባሕር ሕይወቷን በልዩ ሁኔታ ያደምቃሉ።

 

የባርባዶስ ሕዝብና ባህል

የባርባዶስ ሕዝብ “ቤጃን” በመባል ይጠራል። አብዛኛው ሕዝብ ከአፍሪካውያን ዘር የመጣ ሲሆን የአውሮፓና የሌሎች ባህሎች ተጽዕኖ በግልጽ ይታያል።

እንግሊዝኛ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ቢሆንም፣ “ቤጃን ክሪኦል” የተባለ የአካባቢ ቋንቋ በሕዝቡ ዘንድ በስፋት ይነገራል።

የባርባዶስ ሰዎች በእንግዳ ተቀባይነታቸው፣ በትህትናቸው እና በደስተኛ አኗኗራቸው ይታወቃሉ። ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና እምነት በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው።

የሙዚቃና የበዓላት ሀገር

የባርባዶስ ባህል በሙዚቃ እና በዳንስ ይገለጻል። በየዓመቱ የሚከበረው “ክሮፕ ኦቨር” በዓል ከሀገሪቱ ታላላቅ ባህላዊ ዝግጅቶች አንዱ ነው። በዚህ በዓል ላይ የባህል አልባሳት፣ ዳንስ፣ ሙዚቃና የጎዳና ሰልፎች ይካሄዳሉ።

 

ምግብ

ብሔራዊ ምግባቸው “ኩ-ኩ እና ፍላይንግ ፊሽ” ነው። ከዚህ በተጨማሪ የባሕር ምግቦች፣ የተለያዩ ወጦችና የሐሩር ፍራፍሬዎች በስፋት ይመገባሉ።

 

ኢኮኖሚ

ቱሪዝም የአገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው። በተጨማሪ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ፣ ቀላል ኢንዱስትሪዎች እና ግብርና የኢኮኖሚዋ ምሰሶዎች ናቸው።

 

ስፖርት

ክሪኬት የባርባዶስ ተወዳጅ ስፖርት ሲሆን በዓለም ደረጃ የታወቁ ተጫዋቾችን አፍርታለች። በተጨማሪም የውሃ ስፖርቶች፣ ጎልፍ እና አትሌቲክስ ተወዳጅ ናቸው።

ባርባዶስ የባሕር ዳርቻዎች ውበት ብቻ የሚገልጻት አገር አይደለችም። ከቅኝ ግዛት ወደ ሪፐብሊክ የደረሰችበት ታሪኳ፣ የባህል ብዝሃነቷ፣ የሕዝቧ ትጉህነት፣ የተፈጥሮ ውበቷ እና በዓለም አቀፍ ቱሪዝም ያላት ስፍራ ባርባዶስን የካሪቢያን ውቅያኖስ ከሚያበሩ ዕንቁዎች አንዷ አድርጓታል። ወደ ባርባዶስ የሚጓዝ ሰው የሚያገኘው ውብ የባሕር ዳርቻ ብቻ ሳይሆን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ ሰውነትን እና ተፈጥሮን በአንድ ላይ ያዋሃደ ልዩ ተሞክሮ ነው።

 

አጫጭር እውነታዎች

ባርባዶስ በካሪቢያን ከፍተኛ የንባብና የጽሕፈት ደረጃ ካላቸው አገራት አንዷ ናት።

ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፈችው ዘፋኝ ሪሃና የባርባዶስ ተወላጅ ናት።

በዓለም ላይ ረም (Rum) ማምረት ከጀመሩ ቀዳሚ አገራት መካከል ትገኛለች።

ብሔራዊ መፈክሯ “Pride and Industry” ሲሆን በአማርኛ “ኩራትና ትጋት” ለማለት ነው።

ምንም እንኳን ትንሽ ደሴት ብትሆንም በዓለም ከሚታወቁ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ ናት።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሰኔ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here