እስከአሁን ከተሰሩት የሰዓት አይነቶች ከተለመደው የጊዜ መስፈሪያ በተጨማሪ 63 የተለያዩ “ውስብስብ” መለኪያ፣ መለያ፣ ማንቂያ… ያለው “በርክሌይ ግራንድ ኮምፕልኬሽን ”የተሰኘው የኪስ ሠዓት ቀዳሚ ሊሆን መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሰሞን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በጊዜ አለካክ ጥበብ “ሆሮሎጂ” “ኮምፕልኬሽን” ወይም ውስብስብነት ከተለመደው ሰዓት፣ ደቂቃ እና ሰከንድ ውጪ ያሉ እንደማንቂያ ድምፅ (አላርም)፣ የሩጫ መከታተያ (ስቶፕዎች)፣ የሙቀት መጠን፣ ወር ፣ዓመተ ምሕረት፣ የልብ ትርታ… የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ መልኩ በርክሌይ ግራንድ ኮምፕልኬሽን 63 ውስብስቦችን በመያዙ ቀዳሚ ሊሆን ችሏል፡፡
በስዊዘርላንድ በ2015 እ.አ.አ ሰዓት አምራቹ ቫቼሮን ኮንስታንቲን ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ በልዩ መስፈርት ለግሉ በኪስ የሚያዝ ሰዓት እንዲሰራለት ያዛል፡፡ ከታዘዙት መስፈርቶች ሰዓቱ የሚይዛቸው የሄብራይክ የቀን መቁጠሪያን ጨምሮ በርካታ ዝግጅቶችን በአንድ የጊዜ ቅደም ተከተል የሚያሳይ ሰሌዳ… ይገኝበታል፡፡
የኪስ ሰዓቱ ዲያሜትር/ የመሀል ለመሀል ርዝመት/ ሁለት ኢንች ሆኖ የውጪው ሽፋን እና መያዥያው ከነጭ ወረቅ የተሰራ ሲሆን ክብደቱ 960 ግራም ነበር፡፡
የኪስ ሰዓቱ ቀደም ብሎ ቀዳሚ ከነበረው ፓቴክ ፍሊፕ ካሊብሬ 89 (33 ውስብስብ) ከነበሩት ሰዓት እጥፍ የሚጠጋ ብልጫ (63) ያለው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
የኪስ ሰዓቱን የሰሩት ባለሙያዎች ኃላፊ ዶሚኒክ በርናዝ ለፎርብስ መጽሄት የሰጡትን አስተያየት ጠቅሶ ድረ ገጹ እንዳሰፈረው እያንዳንዱ ውስብስብ ልዩ ስኬት ነው፤ 63ቱንም በአንድ ላይ በኪስ ሰዓቱ ውስጥ ማካተትም በእጅጉ ፈትኗቸዋል፡፡
ባለሁለት ጐኑ የኪስ ሰዓት ከ2870 ጥቃቅን ሜካኒካል ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን ዋጋውም በባለሙያዎች እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር መገመቱን ድረ ገጹ በማጠቃለያነት አስፍሯል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


