ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ መቋቋሙ እና ሥራ መጀመሩ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሁም አንድነትን ለመገንባት ትልቅ ትርጉም አለው። መሠረታዊ የልዩነት ነጥቦች ላይ መነጋገር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሕገ-መንግሥት፣ ሰንደቅ ዓላማ እና በሌሎች ሀገራዊ ምልክቶች እንዲሁም በፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ ያሉትን ልዩነቶች፣ ብሎም አለመግባባቶች በውይይት ለመፍታት መንገድ ይከፍታል።
ምክክር ለዘመናት የቆዩትን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በኃይል የመፍታት ባህልን በመቀየር፣ ሀሳብን በሀሳብ የመሞገትና የመደራደር ባህልን ያዳብራል፤ ሀገራዊ መግባባትን ይፈጥራል፡፡ በተለያዩ ኃይሎች መካከል በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት እና መግባባት እንዲፈጠር ያግዛል።
ችግሮችን በመመካከር የመፍታት አማራጭ በተጨማሪም የሕግ የበላይነትን እና ዲሞክራሲን ያጠናክራል፡፡ አካታች በኾነ ውይይት የሚደረስባቸው ውሳኔዎች የሕዝብ ውክልና ስለሚኖራቸው፣ ለጠንካራ እና ታማኝ የመንግሥት ተቋማት ግንባታ መሠረት ይሆናሉ። የሰላም እና የልማት ጉዞን ያፋጥናሉ፡፡
የሀሳብ ልዩነት የወለዳቸው ግጭቶች በንግግር ሲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም ሲሰፍን ሀገራችን ትኩረቷን እንዲሁም ሀብቷን ወደ እድገትና ልማት እንድታዞር ያስችላታል።
ችግሮችን በምክክርና በውይይት የመፍታት ባህልን ማዳበር ለአንድ ማህበረሰብም ሆነ ለሀገር በርካታ ዘላቂ ጥቅሞች አሉት። ከሁሉም በላይ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል፡፡ በኃይል ወይም በጉልበት የበላይነት የሚፈቱ ችግሮች ጊዜያዊ እፎይታ እንጂ ዘላቂ ሰላም አያመጡም። በምክክር የሚደረግ ስምምነት ግን የችግሮችን ሥረ-መሠረት መርምሮ ስለሚፈታ ድጋሚ ግጭት እንዳይፈጠር ያደርጋል።
ልዩነቶችን በምክክር መፍታት መከባበርንና መተባበርን ለማጎልበት ይረዳል፡፡ የመደማመጥ እና ልዩነቶችን አክብሮ የመኖር ባህልን ይገነባል። አላስፈላጊ የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመትን ይከላከላል፡፡ አለመግባባቶች ወደ ጦርነትና ግጭት እንዳያደጉ ይከላከላል፤ የዜጎችን ሕይወት፣ ሀብትና ንብረት ይታደጋል።
ውሳኔዎች ሙሉ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ኹነኛ ሚና ይጫዎታል፡፡ ሰዎች በውይይቱና በምክክሩ ሂደት ሲሳተፉ፣ በሚደረሰው ውሳኔ ላይ የባለቤትነት ስሜት ይኖራቸዋል። ይህም ውሳኔዎች በተግባር እንዲተርጎሙና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ችግሮችን በምክክርና በውይይት መፍታት አካታች ሥርዓትን ለመገንባት በእጅጉ ያግዛል፡፡ በምክክር ወቅት የሁሉም ወገን ድምፅ እንዲሰማ ዕድል ስለሚከፍት፣ ማህበራዊ ፍትሕንና አካታችነትን ያረጋግጣል። ችግሮችን በምክክር የመፍታት ልምድ የሰለጠነና ዘመናዊ ማህበረሰብ መገንቢያ ዋና መሳሪያ ነው፡፡
ግጭቶች በኃይል ሲፈቱ የሚከተለው ጥፋት ሰፊ ሲሆን፣ ምክክር ግን በጦርነትና በግጭት የሚጠፋውን የዜጎች ሕይወት፣ የአካል ጉዳት፣ የዜጎች መፈናቀል እንዲሁም የቤተሰብ መበተን ያስቀራል። የምጣኔ ሀብትና የመሠረተ ልማት ውድመትን ይከላከላል፡፡ ለዓመታት የተገነቡ መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ሕክምና ጣቢያዎችና ፋብሪካዎች እንዳይወድሙ ያደርጋል። በተጨማሪም ለጦርነት የሚወጣውን ግዙፍ ሀብት ወደ ልማትና ለዜጎች ደኅንነት እንድናውለው ያስችላል። ሀገራዊ መፍረስንና የፖለቲካ ቀውስን ይታደጋል፡፡
ምክክር የጋራ መግባባት በመፍጠር የሀገርን አንድነትን ያስከብራል። ትውልድ ተሻጋሪ የጠላትነትና የቂም በቀል ስሜትን ይቀንሳል፡፡ በምክክር የሚገኝ መፍትሔ ፍትሕንና እርቅን ስለሚያመጣ ቂምን ያከስማል።የሀገርን ዓለም አቀፍ ገጽታ ይገነባል፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ያሰፍናል፡፡ ዓለም አቀፍ ገጽታው የተገነባ፣ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት ሀገር ደግሞ የውጪ ባለሀብቶችን በመሳብ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን (ኢንቨስትመንት) ያፋጥናል፤ ጎብኝዎችን ይስባል፡፡ ይሄ ደግሞ የሀገርን ምጣኔ ሀብት ከውድቀት ከማዳኑም በላይ ሀገር በዕድገት እንዲሁም በልማት ጎዳና በፍጥነት እንድትጓዝ ምቹ ኹኔታን ይፈጥራል፡፡ በአጠቃላይ የሀገራዊ ምክክር ጠቀሜታ ፈርጀ ብዙ እንዲሁም እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለሆነም ችግሮችን በምክክር መፍታት ይቻል ዘንድ ምክክሩ የቱንም ያህል ጊዜ ቢወስድ፣ የቱንም ያህል ጥረት ቢጠይቅ ለምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


