በፈጠራ ዘርፉ ሴቶች መበረታታት አለባቸው

0
143

ታዋቂዋ የአገውኛ (የአዊ) ባህላዊ ሙዚቃ ድምጻዊት አቡኔ አበጀ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በተለይም በአገውኛ ቋንቋ እና ባህል ላይ ተፅዕኖ የፈጠረች እና በርካታ ፈተናዎችን አልፋ እውቅና ያገኘች ጠንካራ አርቲስት ናት። አቡኔ ሙዚቃ በጀመረችበት ወቅት በባህላዊ ማህበረሰብ ውስጥ ሴት ልጅ መድረክ ላይ ወጥታ ስትዘፍን እንደ “ባለጌ” ወይም “ስነ-ምግባር የጎደላት” ተደርጋ የምትወሰድበት የተሳሳተ አመለካከት ሰፊ ነበር። ይህ አይነቱ ስነ-ልቦናዊ ጥቃት በርካታ ሴቶች የፈጠራ ብቃታቸውን እንዲደብቁ ያደርጋል።

አቡኔ አበጀ ጥበብን በጀመረችበት ወቅት የአገውኛ (አዊ) ሙዚቃዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት የመደመጥ እና ትኩረት የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነበር።  በወቅቱ የነበረው የሙዚቃ ገበያ በዋናነት በአማርኛ ሙዚቃዎች ላይ ያተኮረ በመሆኑ በክልላዊ ቋንቋ እና ባህል ተነስቶ ሀገር አቀፍ ተቀባይነትን ማግኘት እጅግ ፈታኝ ነበር። አቡኔ በማንነቷ እና በባህሏ በመተማመን የአገው ህዝብን ጥንታዊና ውብ ባህላዊ ውዝዋዜ እንዲሁም ዜማዎች ይዛ በመነሳት የአገውኛ ሙዚቃ በኢትዮጵያ መድረኮች ላይ ቦታ እንዲኖረው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጋለች። በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ሴቶች በሙዚቃ ስራ ላይ በስፋት እንዲሰማሩ የነበረውን ባህላዊ ጫና እና የተሳሳተ አመለካከት በመስበር ሌሎች ወጣት የአገው ሴቶች ወደ ጥበቡ እንዲገቡ በር ከፍታለች። አቡኔ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ትላልቅ ተቋማት ድረስ ከፍተኛ ጫና ማሳለፏን እና እጅ አልሰጥም በሚል መንፈስ ዛሬ ላይ ያለችበት ደረጃ መድረሷን ትናገራለች፡፡

ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ማህበራዊና የቤተሰብ ጫናዎች ሴቶች በኪነጥበብ ዘርፉ ያሰቡት ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ዋነኛ መሰናክሎች ናቸው።

ቢሃይንድ ዘ ሲንስ (Behind the Scenes Ethiopia) የተሰኘው የጥናት እና ምርምር ፕሮጀክት ከአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በኪነጥበብ የፈጠራ ዘርፍ የሴቶችን ሚናና የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች የሚያሳይ የምርምር ውጤት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅርቧል።

በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምር ድርጅት (OSSREA) የ”ከመጋረጃው በስተጀርባ” ፕሮጀክት ተመራማሪ  አዲሱ ጸጋዬ (ደ/ር) በኢትዮጵያ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩ ወጣት ሴቶች የሚጋፈጧቸውን መዋቅራዊ የጾታ ኢ-ፍትሃዊነቶች በባህር ዳርና ሌሎች ከተሞች እንደሚስተዋሉ ይፋ አድረገዋል። በአማካይ 4 ነጥብ 2 በመቶ ለሀገራዊ ጥቅል ምርት (GDP) አስተዋፅኦ ያለው ይህ ዘርፍ የሴት ባለሙያዎችን ፋይናንስ፣ ስራ ዕድል እና እውቅና የሚያገል መዋቅር እንዳለው እና ሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ በስፋት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን በጥናቱ በቁጥር አስደግፈው አሳይተዋል። የአፍሪካ የፈጠራ ዘርፍ እስከ 2040 ዓ.ም ተጨማሪ 20 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ እና 20 ሚሊዮን አዳዲስ ስራዎችን የመፍጠር አቅም እንዳለው በጥናቱ ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ትልቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረቱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ወሳኝ መሆናቸውን አሳስበዋል።

ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ብዙ ጊዜ በድብቅ ስለሚፈጸሙ በማስረጃ እጥረት ሳቢያ የፍርድ ሂደቱን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። በኪነጥበብ ተቋማት እና በስራ ቦታዎች ላይ ፆታዊ ትንኮሳን የሚከላከሉ ጥብቅ ህጎችና መመሪያዎች መዘጋጀት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ማህበረሰቡ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ከመውቀስ ይልቅ የደህንነት እና የስነ-ልቦና ድጋፍ የሚሰጥበት መዋቅር ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በመቀረጽ ላይ ባለው አዲሱ የክሬቲቭ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ውስጥ ወጣት ሴት ባለሙያዎችን ከስራ ቦታ ትንኮሳ የሚጠብቁ፣ የተመጣጣኝ ክፍያ መብታቸውን የሚያረጋግጡ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ተቋማዊ የስራ ከባቢ የሚፈጥሩ አስገዳጅ የህግ አንቀጾች እንዲካተቱ በጥናቱ ጠንካራ የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።

ወይዘሮ ደስታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው በዘርፉ ጥናት አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያን የፈጠራ ኢንዱስትሪ በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ዘርፎች በመለየት ሴቶች በስፋት የሚሳተፉባቸው መደበኛ ባልሆኑ ዘርፎች (እንደ እደ-ጥበብ) የገቢ እና ተቋማዊ እውቅ እና ክፍተት ያለባቸው መሆኑን አሳይተዋል። ጥናቱ መደበኛ ያልሆኑ ስራዎችን ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ በማሸጋገር የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ አቅርቦትን በማመቻቸት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ መክረዋል።

የፕሮጀክቱ ኃላፊ ጌትነት ታደለ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው ጥናቱ ለሶስት ዓመታት በመካሄድ ወጣት ሴቶች በፈጠራ ዘርፍ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች እና ያሉ እድሎችን ለመለየት መቻሉን ገልጸዋል። በጥናቱ የተሳተፉ አብዛኞቹ ሴቶች በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ካሰቡት ደረጃ ሳይደርሱ እንደሚቀሩ የገለጹት ፕሮፌሰሩ 90 በመቶ የሚሆኑት “ጥበብ ጠርታኛለች፤ በሥራውም እረካለሁ” በማለት በዘርፉ ለመቀጠል ያላቸውን ፅናት ማሳየታቸውን አመልክተዋል።

ፕሮፌሰሩ አክለውም የፈጠራ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ እድገት እና ለሰላም ግንባታ ያለውን አስተዋፅኦ በመገንዘብ ሴቶችን ማበረታታት፣ መደገፍ እና ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር እንደሚገባ ጠይቀዋል። ጥናቱ በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ወልቂጤ፣ ሐዋሳ እና አዳማ ከተሞች ከ500 በላይ ተሳታፊዎችን በማካተት የተካሄደ ሲሆን የጥናቱ ውጤት ፖሊሲዎችን ለማሻሻል እና የአሰራር ለውጦችን ለማጠናከር እንደሚያግዝም ነው ፕሮፌሰሩ የጠቆሙት።

አንጋፋው የፈንድቃ ባህል ማዕከል መስራች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያ አርቲስት መላኩ በላይ በፓናል ውይይቱ ላይ በዘርፉ ውስጥ ያሉ ሴቶች የሚጋፈጡትን ስውር ጥቃትና መፍትሄዎቹን በተመለከተ ተናግሯል። አርቲስት መላኩ በመድረኩ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት በኢትዮጵያ የባህል እና የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይም በባህል ምሽት ቤቶች እና በጭፈራ  ዘርፍ የሚሰሩ ሴት አርቲስቶች ለከፍተኛ የቃላት፣ የስነ-ልቦና እና የአካል ጥቃቶች የተጋለጡ መሆናቸውን በግል ተሞክሮው አስደግፎ አብራርቷል። ማህበረሰቡ ለሴት የባህል ተወዛዋዦች እና ድምጻውያን ያለው የተሳሳተና ዝቅ አድርጎ የመመልከት አመለካከት ሴቶቹ በነፃነት ብቃታቸውን እንዳያሳዩ እና ለተለያዩ ብዝበዛዎች እንዲጋለጡ በር እየከፈተ መሆኑን በቁጭት ገልጿል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ እንደ ፈንድቃ ባህል ማዕከል ያሉ ተቋማት ለሴት አርቲስቶች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ከማንኛውም ትንኮሳ ነፃ የሆነ እና እኩል ክፍያ የሚያረጋግጥ የስራ ከባቢ ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሷል። አርቲስት መላኩ በማጠቃለያው የሴት ባለሙያዎችን መብት እና ክብር ለማስጠበቅ የግል ማዕከላት ጥረት ብቻ በቂ ባለመሆኑ በጥናቱ የቀረቡት ምክረ-ሀሳቦች በአዲሱ ሀገራዊ የክሬቲቭ ፖሊሲ ውስጥ ተካተው መንግስታዊ እና ህጋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስቧል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) እንደገለጹት የኪነጥበብ ዘርፉን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ ተከታታይ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ አሰራሮችን ለማስፋት የጥናቱ ግኝቶች ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። በክልሉ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች በኪነጥበብ ዘርፍ የሥራ እድል ያገኙ ቢሆንም ዘርፉ ባለው አበርክቶ ልክ በጥናት እና ምርምር የተደገፈ አለመሆኑ ክፍተት እንዳለውም ጠቁመዋል።

ሴቶች ወደ ኪነጥበብ ዘርፍ እንዳይቀላቀሉ ወይም በዘርፉ እንዳይዘልቁ ከሚያደርጉ ተግዳሮቶች መካከል የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ጫና፣ የፈጠራ ሥራን በተገቢው መልኩ አለመገንዘብ እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ዋነኞቹ መሆናቸውን አስረድተዋል። በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር  በጥበቡ ዘርፍ ያሉ የጠለያዩ ባለሙያዎች ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ከውይይቱ በኋላ አዲስፖሊሲ መረቀቁን እና በቅርቡ እንደሚጸድቅ ይፋ አድረገዋል፡፡ በዚህም በዘርፉ የሚስተዋሉ የስርዓተ ጾታ፣  የፋይናንስ እና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

የጥናት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በኪነጥበብ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ከ70 በመቶ በላይ ሴቶች በሥራ ቦታ የሚሰነዘሩ ያልተገቡ ፆታዊ ጥያቄዎችን  ባለመቀበላቸው ብቻ የተገቡትን የሥራ ዕድል፣ የፊልም ሚና ወይም የሙዚቃ ኮንትራት ያጣሉ፡፡

በዩኔስኮ (UNESCO) ዓለም አቀፍ የኪነጥበብ ሪፖርት መሠረት በባህልና ፈጠራ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት እና የመሪነት ቦታዎችን የያዙት ሴቶች ከ30% በታች ናቸው፤  ይህ ደግሞ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚከላከሉ የውስጥ መመሪያዎች እንዳይወጡ ትልቅ ማነቆ ሆኗል፡፡

በአማራ ክልል የተካሄዱ የቅርብ ጊዜ ማህበረሰብ-ተኮር ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 64.8 በመቶ የሚሆኑት  ለአካለ መጠን የደረሱ ሴቶች ሴቶች በሕይወታቸው ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ የፆታ ማሸማቀቅ፣ አካላዊ ወይም ስነ-ልቦናዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡  ይህ ችግር ምሽት ላይ በሚሰሩ ሴት አርቲስቶች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ይጎላል፡፡

 

የፈጠራ መብት አዋጁ ምን ይላል?

በኢትዮጵያ የፈጠራ መብትን ለመጠበቅ የወጣው ዋናው ሕግ የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዋጅ ቁጥር 123/1987 ነው።ከዚህ አዋጅ ውስጥ አንድ ፈጠራ የፓተንት (የፈጠራ መብት) ጥበቃ ለማግኘት ማሟላት ያለበትን መሠረታዊ መስፈርት የሚደነግገው አንቀጽ 3 የሚከተለውን ይላል፦ አንቀጽ 3፦ ፓተንት የሚሰጥባቸው ፈጠራዎች አንድ ፈጠራ አዲስ ከሆነ፣ የፈጠራ ሥራ ደረጃን የሚያሳይ እና በኢንዱስትሪ ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ከሆነ የፓተንት መብት ይሰጠዋል።፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 27  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here