የማይበጠሰዉ ፍቅር

0
192

የዓለም ጤና ድርጅት ስለ ጡት ማጥባት አይተኬ ሚና “ጡት ማጥባት ለሕጻናት የተፈጥሮ ስጦታ፣ ለእናት ደግሞ የፍቅር መገለጫ ነው” ሲል ያስነብባል፡፡

በተመሳሳይ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) “የእናት ፍቅር በእቅፍ ይጀምራል፤ በጡት ማጥባት ይጠነክራል” በማለት ነው የጡት ማጥባትን አበርክቶ የሚያስገነዝበው፡፡

ጡት ማጥባት ለሕጻናት የተሟላ ጤንነት ከማበርከቱ በተጨማሪ የእናት እና ልጅን ጥልቅ ፍቅር ይበልጥ የሚያጠነክር ክር ስለመሆኑ ማንሳታችን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ጡት ማጥባት ሕጻናት ቢያንስ እስከ ሁለት ዓመታቸው የሚበረከትላቸው የየዕለት የእናት ስጦታ ቢሆንም ይበልጥ ትኩረት ለመስጠት ደግሞ በየዓመቱ ከነሐሴ 01 እስከ 07 የጡት ማጥባት ሳምንት በሚል በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እና በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) አዘጋጅነት መከበር የጀመረው እ.ኤ.አ በ1992 ሲሆን፣ ዘንድሮም (በ2026) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ ይከበራል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ሳምንት የእናቶችን እና ሕፃናትን ህይወት የመታደግ ብሔራዊ ጥረት አካል በመሆን በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ነው፡፡ ዘንድሮ ለ28ኛ ጊዜ ከነሐሴ 01 እስከ ነሐሴ 07/2018ዓ.ም ድረስ በግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

ዋና ዓላማውም ማኅበረሰቡ ስለ እትብት ትስስር፣ ስለ ተፈጥሯዊው የጡት ወተት ጥቅሞችና አመጋገብ ግንዛቤን ማሳደግ፣ እናቶች ያለ ምንም ስጋት እና ጫና ልጆቻቸውን በነፃነት እንዲያጠቡ ለማበረታታት፣ እንዲሁም የታሸጉ የወተት ምርቶች (Formula milk) የሚያስከትሉትን የጤና እና የኢኮኖሚ ጉዳቶች በመቀነስ የተፈጥሮን ስጦታ የመንከባከብ ባሕልን ለማስፋፋት ነው።

በዚህ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነት ላይ በመመርኮዝ፣ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግብ እና አመጋገብ ትምህርት ክፍል መምህርት ወ/ሮ ገነት እንዳልክ ለበኩር በስልክ በሰጡት ማብራሪያ፣ የእናት ጡት ማጥባት ተፈጥሮ ለሰው ልጅ የሰጠችው ወደር የማይገኝለት ትልቅ ስጦታ መሆኑን አብራርተዋል።

ወ/ሮ ገነት እንዳሉት  እናቶች የጡት ወተት ምርታቸው እንዲጨምርና ጥራቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል የራሳቸውን አመጋገብ ማስተካከል፣ ሙሉ በሙሉ ጤናማ መሆን እና በቂ የፈሳሽ መጠን (በተለይም ንጹህ ውኃ) መውሰድ አለባቸው። እናት ጡት የምታጠባውም በግዴታ ወይም በልማድ ሳይሆን በፍቅር እና በደስታ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ “የስነ-ልቦና ሁኔታዋ በቀጥታ ከሆርሞን ፈሳሽ እና ከወተት ምርት ጋር የተያያዘ ነው” ሲሉ ወ/ሮ ገነት አስገንዝበዋል።

እንደ መምህርቷ ማብራሪያ ሕፃናት ዕድሜያቸው አንድ ዓመት ሳይሞላ የላም ወተት እንዲጠጡ መስጠት ፈጽሞ አይመከርም። የላም ወተት የሕፃናትን ያልበሰለ ጨጓራና ኩላሊት ሊጎዳ፣ እንዲሁም ለከፍተኛ የአለርጂ (የቆዳ መቆጣት) እና የደም ማነስ ችግር ሊዳርጋቸው ይችላል፤ በመሆኑም እናቶች ከዚህ ድርጊት መቆጠብ አለባቸው።

ወ/ሮ ገነት አክለውም፣ ጡት ማጥባት ለሕፃኑ ብቻ ሳይሆን ለእናቲቱም የሚያበረክታቸውን የአካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቅሞች ይዘረዝራሉ፡፡ ሕፃኑ ጡት በሚጠባበት ወቅት በሚመነጨው ኦክሲቶሲን በተባለ ሆርሞን ምክንያት የማህፀን ጡንቻዎች በፍጥነት በመኮማተር ከወሊድ በኋላ የሚኖርን የደም መፍሰስ መከላከሉ እና ማህፀንም ወደ ቀደመ መጠኑ እንዲመለስ ማድረጉ አንደኛው ነው፡፡

ጡት የሚያጠቡ እናቶች በጡት ካንሰር፣ በማህፀን ካንሰር፣ በዓይነት ሁለት ስኳር እና በከፍተኛ የደም ግፊት የመያዝ ዕድላቸው እጅግ አነስተኛ ስለመሆኑም መምህርት ገነት ያነሱት ሌላው የጡት ማጥባት ገጸ በረከት ነው።

በእርግዝና ወቅት የተጠራቀመውን ተጨማሪ ስብ በፍጥነት በማቃጠል እናቶች ከወሊድ በኋላ ወደ ነበራቸው የሰውነት ቅርጽና ክብደት እንዲመለሱ እና በጡት ማጥባት ወቅት በሚፈጠሩ ሆርሞኖች ምክንያት በእናትና በልጅ መካከል ጥልቅ የመዋደድ ትስስር በመፍጠር እናቶችን ከወሊድ በኋላ ከሚከሰት ድብርት መታደጉ በተጨማሪነት ያነሷቸው ጠቀሜታዎች ናቸው።

ወ/ሮ ገነት  የጡት ወተት ለሕፃኑ የመጀመሪያው ተፈጥሯዊ ክትባትና የተመጣጠነ ምግብ ነው። ይህንንም እንደሚከተለው ያብራሩታል፤ የእናት ጡት ወተት ለሕፃናት ዕድገት የሚያስፈልጉትን ፕሮቲኖች፣ ቫይታሚኖች፣ ቅባቶችና የውኃ መጠን በክትክክለኛው መጠን የያዘ አቻ የሌለው ምግብ ነው። በተለይም ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 2 – 3 ቀናት የሚወጣው ወፍራም ቢጫ ወተት (እንገር) ከፍተኛ መጠን ያለው በሽታ ተከላካይ ጸረ እንግዳ አካሎችን (አንቲ ቦዲ) የያዘ በመሆኑ ፈጽሞ ሳይደፋ ለሕፃኑ መሰጠት አለበት።

የጡት ወተት በቀላሉ የሚፈጭ በመሆኑ ሕፃናትን ከሆድ ድርቀት፣ ከጋዝ እና ከተቅማጥ በሽታዎች ይከላከላል። በጡት ወተት ውስጥ የሚገኙት ዲ ኤች ኤ እና ኤ አር ኤ  የተባሉ ልዩ ቅባቶች የሕፃናትን የአዕምሮ እና የዓይን ዕይታ ዕድገት ያፋጥናሉ።

እንደ ወ/ሮ ገነት ማብራሪያ  በጡት ወተትና በታሸገ (የፋብሪካ) ወተት ያደጉ ሕፃናት በግልጽ የሚታዩ ልዩነቶች አሏቸው፤ የእናት ጡት የጠባ ሕፃን ጡት ካልጠባ (የታሸገ ወተት ከሚጠጣ) ሕፃን ጠንካራ የበሽታ መከላከል አቅም አለው፤ ለተቅማጥና ሳንባ ምች አይጋለጥም። ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች እና ተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድሉም ዝቅተኛ ነው።በተጨማሪም የተሻለ የአዕምሮ ዕድገት (IQ – የአዕምሯዊ ዕውቀት መለኪያ) ይኖረዋል። የታሸጉ እና በፋብሪካ ዉጤት ያደገ ህጻን መደበኛ ዕድገት ቢኖረውም ተፈጥሯዊ የአዕምሮ አበልፃጊ ቅባቶችን አያገኝም። ለአስም እና ለተለያዩ አለርጂዎች የመጋለጥ ዕድሉም ከፍተኛ ነው። ለምግብ አለመስማማት ችግሮችም ይጋለጣል።

በተመሳሳይ የእናት ጡት ያልጠባ ሕጻን በአዋቂነት ዕድሜው ለውፍረት፣ ለስኳርና ደም ግፊት የመጋለጥ እና ተዛማጅ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድሉም ከፍተኛ ነው።

ወ/ሮ ገነት አክለውም ሕፃናት ከተወለዱበት ሰዓት ጀምሮ እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ብቻ መመገብ አለባቸው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ውኃ፣ ሻይ፣ ወይም ሌላ ተጨማሪ ምግብ መስጠት የሕፃኑን ጤና አደጋ ላይ ይጥላል።

ሕፃኑ ስድስት ወር ሲሞላው ግን ተገቢና የተመጣጠነ ተጨማሪ ምግቦችን ከመጀመር ጎን ለጎን ጡት ማጥባቱን እስከ ሁለት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ መቀጠል ያስፈልጋል።

“ከቤት ውጭ የሚሠሩ እናቶችም ቢሆኑ ወተታቸውን በጽዳት አልበው አየር በማይገባበት ዕቃ በማስቀመጥ መጠቀም ይችላሉ፤ የታለበ ወተት በክፍል ሙቀት (Room Temperature) ውስጥ እስከ አራት ሰዓት፣ በማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ውስጥ ደግሞ እስከ አራት ቀን እና ከዚያም በላይ በማቆየት መጠቀም እንደሚችሉ” ነው የተናገሩት።

እናቶች የሰውነት አቋም (ቅርጽ) ይለወጣል በማለት ልጆቻቸውን ከማጥበት መቆጠብ እንደሌለባቸው ያነሱት ባለሙያዋ በሚያጠቡበት ወቅት አቀማመጣቸውን እና የአጠባብ ሥርዓታቸውን በማስተካከል የሰውነት አቋማቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ወ/ሮ ገነት አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ፣ “የእናት ጡት ማጥባት እናቶች ለልጆቻቸው የሚሰጡት ትልቁ የፍቅርና የጤና መሰረት በመሆኑ፣ እናቶች ራሳቸውን በመንከባከብ፣ በቂ ፈሳሽና የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ፣ ልጆቻቸውን በፍቅርና በደስታ ሊያጠቡ ይገባል” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

(ሰናይት በየነ)

በኲር የነሐሴ  4  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here