ሾተላይ ምንድን ነው?

0
314

የደም ዓይነት ስንል ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ እና ኦ የሚባሉትን ብቻ ማሰብ የተለመደ ነው። ከእነዚህ በተጨማሪ ግን በደም ውስጥ አር ኤች የሚባል ሌላ አስፈላጊ መለያ አለ። ሰው እንደ ደሙ ዓይነት አር ኤች ፖዘቲቭ (Rh+) ወይም አር ኤች ኔጌቲቭ (Rh-) ሊሆን ይችላል።

እርግዝና ወቅት የእናት እና የፅንስ አር ኤች ሁኔታ አለመጣጣም ከተፈጠረ የጤና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፣ በመሆኑም Rh ምን እንደሆነና ለእናትና ልጅ ጤና ያለውን ጠቀሜታ ማወቅ ወሳኝ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዲያ ሾተላይ (በተለምዶ ሰራቂያን የሚባለው) ብዙ ጊዜ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፍርሃትን የሚያስከትል ቃል ነው። አንዳንዶች በዘር የሚተላለፍ ችግር፣ ሌሎች ደግሞ እንደ እርግማን ይመለከቱታል።

ሾተላይ በባሕላዊው እና በዘመናዊ የሕክምና መስኮችም የየራሱ ዕይታዎች አሉት።

በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት እማሆይ ክቤ የሺዋስ ከ15 ዓመታት በፊት በተጠሩበት ሁሉ ጊዜ ሳይገድባቸው ፈጥነው ለመድረስ የሚቀድማቸው አልነበረም፡፡ ጥሪው ደግሞ ነፍሰጡሮችን ባላቸው ልምድ በሰላም ለማገላገል ነው፡፡

እማሆይ ክቤ በልምድ በርካታ ነፍሰጡሮችን እንዳገላገሉ  ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱም አልፎ አልፎ  ሾተላይ /ሰራቂያን/ ያጋጥማቸው እንደ ነበር አንስተዋል፡፡ እማሆይ እንደሚሉት  በእሳቸው ዘመን አንዳንድ እናቶች ሾተላይን በዘር እንደ ሚተላለፍ እና እንደ ርግማን ይቆጥሩት ነበር። ሁኔታው ከእርግዝና ወራት ጀምሮ የሚታወቅ ከሆነ ነፍሰጡሯ  በሰላም እንድትገላገል የተለያዩ ባሕላዊ መፍትሔዎችን ይሞከሩ ነበር። ለምሳሌ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል የተባለ የእጽዋት ስር ነፍሰጡሯ እንድታኝክ ይደረጋል፣ ምጥ ሲጀምራት ደግሞ  ብረት ምጣድ በማንኳኳት ትኩረቷን መሳብ እና የመሳሰሉ ተግባራት ይከናወኑ ነበር፡፡

ከባሕላዊ ልምድ በተለዬ ስለ ዘመናዊው ሕክምና ሳይንስ ማብራሪያ  የሰጡን ደግሞ ባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው መዳን ጠቅላላ ሆስፒታል የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር በሙሉ ፋሲካ ናቸው።

ከበኵር ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሙያዋ እንዳስገነዘቡት በአንዳንድ ነፍሰጡሮች ላይ የሚከሰተው ሾተላይ ብዙ ጊዜ ጽንሱ እንዲጨናገፍ እና ከተወለደም በኋላ ቢሆን ሕጻኑ እንዳያድግ የሚያደርግ የጤና እክል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከወሊድ ጋር ተያይዞ ሾተላይ ተብሎ በሕብረተሰቡ የሚጠራው ክስተት በቀጥታ እንደ በሽታ መቆጠር የለበትም።

አራቱ የሰው ልጆች የደም አይነቶች (ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ እና ኦ) እያንዳንዳቸው በሁለት ዓበይት መደብ ይከፈላሉ፡፡ አር ኤች ፖዘቲቭ (Rh+) እና አር ኤች ኔጋቲቭ (Rh-) በመባል።

ሾተላይ የሚከሰተው ደግሞ አንዲት እናት የደም አይነቷ አር ኤች ኔጌቲቭ ሆኖ ከዚህ በፊት አር ኤች ፖዘቲቭ የሆነ ደም ወደ ሰውነቷ ሲገባ ነው፤ በዚህ ጊዜ ደሟ ውስጥ አር ኤች ፖዘቲቭ  የሆኑ የደም ህዋሶችን የሚያጠፋ ንጥረ ነገር በደሟ ውስጥ ይመረታል።

ዶክተር በሙሉ እንዳብራሩት ንጥረ ነገሩ አንዴ ከተመረተ በደሟ ውስጥ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ይኖራል። በመሆኑም በማህጸኗ ውስጥ የያዘችው ጽንስ የደም ዓይነቱ አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ የተመረተው ንጥረ-ነገር ጽንሱን እንደ ባእድ አካል ስለሚቆጥረው ያጠቃዋል።

በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ የምትይዘው ጽንስ የደም ዓይነቱ አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ አስፈላጊውን ሕክምና ካልተደረገላት ይሞትባታል። የደም ዓይነቱ አር ኤች ኔጋቲቭ ከሆነ ግን በጤና ይወለዳል። በተጨማሪም ሕጻኑ በሕይወት እንዲወለድ የአባት የደም አይነት አር ኤች ኔጋቲቭ መሆን አለበት፡፡

ሾተላይ በተለይ ነፍሰጡሯ አር ኤች ነጌቲቭ  ሆና ጽንሱ  አር ኤች ፖዘቲቭ ሲሆን ሊፈጠር እንደሚችል የጠቆሙት ዶ/ር በሙሉ  በእርግዝና፣ በወሊድ፣ በመጨንገፍ፣ በደም መፍሰስ፣ በሆድ ጉዳት ወይም የጽንሱ ደም ከእናቱ ደም ጋር ሊገናኝ በሚችልበት ሌላ ሁኔታ የጽንሱ ቀይ የደም ህዋሳት ወደ እናቱ ደም ሊገቡ ይችላሉ።

በዚህ ጊዜ የነፍሰጡሯ የሰውነት መከላከያ ሥርዓት የጽንሱን አር ኤች ፖዘቲቭ እንደ ባዕድ ነገር ሊቆጥረውና ፀረ-እንግዳ አካል ሊያመነጭ ይችላል። ፀረ-እንግዳ አካሉ ወደ ጽንሱ ሲደርስ የጽንሱን ቀይ የደም ህዋሳት ሊያጠፋ ይችላል ነው ያሉት ዶ/ር በሙሉ። ይህም በጽንሱ ላይ የደም ማነስ፣ ከባድ የአራስ ቢጫ በሽታ፣  የልብ ችግር እና  የጽንስ ሞትን  ሊያስከትል ይችላል።

ሾተላይ በዘር ይተላለፋል? በማለትም በኵር ለዶ/ር በሙሉ ጥያቄ አንስታለች፤ “ሾተላይ በዘር ከወላጅ ወደ ልጅ የሚተላለፍ አይደለም። በዘር የሚወረሰው አር ኤች ኔጋቲቭ ወይም አር ኤች ፖዘቲቭ ባህርይ ነው። ችግሩ የሚፈጠረው ታዲያ ይህ የደም ባህርይ ከእናት የሰውነት መከላከያ ምላሽ ጋር ሲገናኝ ነው። ስለዚህ አንዲት ሴት አር ኤች ኔጋቲቭ በመሆኗ ብቻ ልጇ ችግር ይደርስበታል ማለት አይደለም” ነው ያሉት።

እንደ ዶ/ር በሙሉ ማብራሪያ በቅድመ-ወሊድ ክትትል ወቅት የእናት የደም ቡድን እንዲመረመር ይመከራል። አር ኤች ነጌቲቭ  የሆኑ ሴቶች ደግሞ በሚመለከታቸው ጊዜ የበሽታ መከላከያ ፀረ-ሰው ፕሮቲን /Anti-D immunoglobulin/ መከላከያ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።   ስለዚህ እናቶች ቀድመው መመርመራቸው የችግሩን አደጋ ለመቀነስ ዋናው መንገድ ነው።

በተጨማሪም እናቶች በወሊድ ክትትል ወቅት የተለያዩ የደም ፀረ-ሰው ምርመራዎችን ማድረግ እንዳለባቸውም ዶ/ር በሙሉ ይመክራሉ።

ሾተላይ የአንድ ቤተሰብ የግል ችግር ብቻ አለመሆኑን ያነሱት ዶ/ር በሙሉ፤ በጤናው ዘርፍ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ̋ለዚህም በቅድመ-ወሊድ ክትትል ጊዜ የደም ምርመራ በተገቢው  መደረጉ፣ ፀረ ሰው መድኃኒት በበቂ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገኝ ማድረግ፣ የጤና ባለሙያዎችን ዕውቀት ማሳደግና ለሴቶች በቂ ግንዛቤ መስጠት ችግሩን ለመቀነስ ወሳኝ ናቸው” ብለዋል።

ከእማሆይ ክቤ ልምድ እንደምንረዳው የሾተላይ ጉዳይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የነበረ እና አሁንም ያለ መሆኑን  ነው። የባሕላዊ (የልምድ) አዋላጆች በወቅቱ በነበራቸው ዕውቀትና ልምድ እናቶችን ለመርዳት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። ይሁንና ዛሬ የደም ቡድንና የአር ኤች እና የፀረ-ሰው ምርመራ፣  በዘመናዊ የሕክምና ክትትልና ምርመራ /Anti-D immunoglobulin/ በመሳሰሉ የሕክምና ዕውቀቶች የችግሩን ምክንያት በሳይንሳዊ መልኩ ለመለየትና ለመከላከል ዕድል ሰጥተዋል።

ስለዚህ ባህላዊ እምነቶችን ከሕክምና ዕውቀት ጋር በማጣመር ለማኅበረሰቡ ትክክለኛ መረጃ ማድረስ ያስፈልጋል። በተለይ ነፍሰጡሮች “በቤተሰባችን ሾተላይ አለ” በሚል ፍርሃት ብቻ ሳይወሰኑ የደም አይነታቸውንና አር ኤች ሁኔታቸውን በሕክምና ማረጋገጥ እንዳለባቸው ዶ/ር በሙሉ ተናግረዋል።

“ሾተላይን ለመከላከል የሚያስፈልገው ፍርሃት ሳይሆን መረጃ፤ እርግማን መፈለግ ሳይሆን ምርመራ፤ የማይቀር እጣ ፈንታ ነው ብሎ ማመን ሳይሆን በጊዜው መከላከል ነው” በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

መረጃ

  • ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 10 ነፍሰ ጡሮች አንዷ የ አርኤች ነጌቲቭ የደም አይነት አላት።
  • የደም አይነቷ ኔጌቲቭ የሆነ ሁሉም እናት ስለመከላከያ ክትባት/ መርፌ/ ማወቅ ይኖርባታል፡፡
  • ሾተላይ ያለባቸው እናቶች የመጀመሪያ እርግዝናቸው ላይ ችግር ሳይከሰት ቢቀር ቀጣይ እርግዝና ግን ፤ ያለ ህክምና እርዳታ የከፋ ይሆናል።

       በመሆኑም መርፌውን

በእርግዝና ጊዜ 28 ሳምንት ላይ

ከወሊድ በኋላ በ 72 ሰአት ውስጥ እንደገና መውሰድ ይኖርባቸዋል።

 

ምንጭ፡- በኢትዮጵያ ሆስፒታሎች የተደረጉ ጥናቶች

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here