የነገይቱ ኢትዮጵያ የሕልውና መሠረት!

0
16

ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ጠብቃ ያቆየችው የተፈጥሮ ሀብት እና የደን ሽፋን በጊዜ ሂደት በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ክፉኛ ተጎድቶ ቆይቷል። የአፈር መሸርሸር፣ የደን መጨፍጨፍ፣ የውሃ አካላት መድረቅ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣው የድርቅ ስጋት የዜጎችን እለታዊ ህይወትና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ሲፈታተኑ የኖሩ አጣዳፊ ችግሮች ናቸው። ይሁን እንጂ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተጀመረውና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በማስተባበር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ይህንን ታሪካዊ ስብራት በመጠገን ወደ አዲስ የነገ ተስፋ ያሸጋገረ አገራዊ ንቅናቄ ሆኗል። አረንጓዴ አሻራ ተራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፤ የሀገርን ህልውና የማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም እና ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚን የመገንባት ታላቅ ስትራቴጂያዊ ራዕይ ነው።

የዚህ ታላቅ መርሃ ግብር ቀዳሚውና ዋናው ምሰሶ አካባቢያዊ ዘላቂነትን ማረጋገጥ ነው። የደን ሽፋናችንን ወደ ተሻለና ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ በተደረገው አገር አቀፍ ጥረት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል። እነዚህ የተተከሉ ችግኞች የአፈር መበስበስንና በጎርፍ መታጠብን በመከላከል የመሬትን ለምነት ከመጠበቅና ወደነበረበት ከመመለሳቸውም በላይ፣ የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጎለብትና ምንጮች፣ ጅረቶች እንዲሁም ሀይቆች እንዳይደርቁ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ፣ ዛፎች ካርቦንዳይኦክሳይድን በመምጠጥ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የአየር ንብረት መዛባት በመቋቋም እና ግሪንሃውስ ጋዞችን በመቀነስ በኩል የአካባቢ ጥበቃ አርአያ ሆና እንድትወጣ አስችሏታል። ብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ለዱር እንስሳትና ለአእዋፍ ተፈጥሮአዊ መጠለያ በመፍጠር ረገድም የተገኘው ውጤት ትልቅ ነው።

በሌላ በኩል የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር በመደገፍ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። መርሃ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች ላይ ብቻ ሳይወሰን እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ አፕል እና ቡና ያሉ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬና የንግድ ተክሎች ላይ ትኩረት በማድረጉ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መንገድ ከፍቷል። ከችግኝ ማብቀል፣ ተከላና እንክብካቤ ጋር ተያይዞ ለሺዎች በሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች ዘላቂና ጊዜያዊ የሥራ እድሎችም ተፈጥረዋል። ይህ ጥረት ወደፊት የደን ምርቶችን እንደ እንጨት፣ የመድኃኒት ዕፅዋት እና የቱሪዝም መስክ በማስፋፋት የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ታላቅ መሠረት ጥሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳውም እጅግ ጥልቅ ነው። ከጫፍ እስከ ጫፍ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ — የመንግስት ሰራተኞች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎችን  በአንድ ዓላማ ስር ተሰልፈው የተሳተፉበት መንገድ የማህበረሰቡን የጋራ ሃላፊነትና አንድነት በማጠናከር የባለቤትነት ስሜትን ከፍ እንዲል አስችሎታል። ንጹህ አየርና የተጠበቀ አካባቢ በመፍጠር ረገድ ለሕዝብ ጤና የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ሲሆን፣ ሀገራችን የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የምታደርገውን ጉዞም ያፋጥነዋል።

በደቡብ ኮሪያ፣ ብራዚልና ቻይና የተመዘገቡ ስኬቶች እንደሚያሳዩት፣ ጠንካራ የደን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ የኢኮኖሚ ጥንካሬን ያረጋግጣል። በሀገራችንም ባለፉት ዓመታት ትኩረት የተሰጠው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋናችንን ማሳደግ ችሏል። በተለይም እንደ አማራ ክልል ባሉ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ያሳተፉ የተፋሰስ ልማቶችና ገቢ ተኮር ችግኞች መተከላቸው የግብርና ምርታማነትንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

አረንጓዴ አሻራ የዛሬን ችግር ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድ ንጹህ አየር፣ ለም አፈርና የተጠበቀ ተፈጥሮን እንደ ታላቅ ውርስ ለማስተላለፍ የተጣለ የሕይወት መሠረት ነው። በእርግጥ እንደ ችግኞች የመጽደቅ ምጣኔን ማሳደግ፣ የውሃ አቅርቦትና የረጅም ጊዜ ክትትልን የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ የተመዘገቡት ውጤቶች ግን እጅግ ተስፋ ሰጪ ናቸው።

ስለሆነም፣ አረንጓዴ አካባቢን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ የአንድ ወቅት ዘመቻ ሳይሆን የልጆቻችን ነገ እና የሀገራችን ዘላቂ የወደፊት እጣ ፈንታ ነው። ስለሆነም የእለት ተእለት ባህላችን ሊሆን ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋ የተተከሉ ችግኞችን በመጠበቅ፣ በማጠጣትና በመንከባከብ ንቁ ሚናውን ሊወጣ ይገባል። አረንጓዴ አሻራችን የህልውናችን መገለጫ ነውና፤ ተፈጥሮን በመንከባከብ የነገይቱን ኢትዮጵያ በጋራ እንገንባ!

 

በኲር የነሐሴ  18  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here