በተስፋ እና በስጋት የተገመደው መኸር

0
6

መግቢያ

አርሶ አደሩም ከልምድ ያገኘውን ዕውቀት እና ከባለሙያ ያገኘውን ምክረ ሐሳብ በመጠቀም በዝናብ መዘግየት ምክንያት የገጠመውን ችግር ለመቋቋም እየተረባረበ እና ተግዳሮቶችንም በጥበብ እያለፈ ይገኛል።

በትንታኔያችን የ2018/19 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ አጠቃላይ ገጽታ፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችን እና ተስፋዎችን እንዳስሳለን።

በያዝነው የምርት ዘመን በአማራ ክልል የዝናብ ወቅት በብዙ አካባቢዎች ዘግይቶ ነው የጀመረው። ይህን መነሻ በማድረግ ታዲያ አርሶ አደሮች ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ዙሪያ ነዋሪው አርሶ አደር ዓለምአይጠገብ ፈንቴ ተሞክሮ ደግሞ አንዱ ማሳያ ናቸው። አርሶ አደሩ ለበኩር በስልክ በሰጡት አስተያየት አንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸውን በተለያዩ ሰብሎች ሸፍነዋል።

ዝናብ ዘግይቶ ከጀመረባቸው አካባቢዎች  አንዱ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ድርቅ የሚቋቋሙ ሰብሎችን መዝራት፣ ውኃን በማቆር እንዳይባክን ማድረግ፣ ዘወትር የማሳ አሰሳ ማድረግ ደግሞ ተግባራዊ እያደረጓቸው ከሚገኙ አማራጮች መካከል ይጠቀሳሉ።

አቶ በዛብህ ጌታነህ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ናቸው። ቡድን መሪው ለበኩር በስልክ እንዳሉት በ2018/19 የምርት ዘመን ወደ 120 ሺህ 638 ሄክታር ማሳ በዘር በመሸፈን በዚህም አንድ ነጥብ 89 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እስካሁንም 105 ሺህ 622 ሄክታር(88 በመቶ) ያህሉ በዘር ተሸፍኗል።

እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ በዘር ለመሸፈን የታቀደው መቶ በመቶ ላለመሳካቱ ምክንያቱ የዘንድሮው መደበኛ የዝናብ ስርጭት አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ የኤልኒኞ ክስተቱም የዘር ጊዜ እንዲገፋ ምክንያት ሆኗል፤ በተለይ ቆላማዎቹ አካባቢ ላይ ችግሩ ከፍ ያለ ነው። ዝናቡ የተዛባ መሆኑም የእርጥበት እጥረትን አስከትሏል፡፡  ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ በተለይ የጥራጥሬ ሰብሎችን ለመዝራት አስቸጋሪ አድርጎታል።

ቡድን መሪው እንዳሉት ዝናቡ ከመጣም በኋላ ስርጭቱ የተዛባ መሆኑ የብቅለት ችግር አስከትሏል፣ ችግሩን ለመቀነስ ደግሞ የእርጥበት ማቆር እና እርጥበት በማሳ የመያዝ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው።

ችግሩ በሁሉም አካባቢ የተከሰተ ቢሆንም ቆላው ላይ ይብሳል። እሱን መሠረት በማድረግ በማሳ ውስጥም በማሳ ዳርም እርጥበት የሚይዙ ስልቶችን በማከናወን ወደ ማሳ የሚገባ ዝናብ እንዳይወጣ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

“በዚህ አግባብ በተሠራው ሥራ ደግሞ ወደ 14 ሺህ 747 ሄክታር ማሳ ታይሪጂንግ (በትልም በትልም ውኃ ማሳ ውስጥ እንዲቀር ማድረግ) በሚባል የእርጥበት ማቆሪያ ዘዴ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል” ብለዋል።

በተመሳሳይ ሦስት ሺህ 765 ያህል ሄክታር ማሳ ላይ ጎርፍ በመቀልበስ ጎርፉን ማሳ ውስጥ ማስገባት፣ ደጋፊ መስኖ (ሰፕሊመንተሪ ኢሪጌሽን) እና መሰል የውኃ ዕቀባ ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የዝናብ እጥረቱ ያስከተለው ሌላው ችግር የተባይ ክስተት ነው። የዝናብ መጥፋት፣ መብዛት እና መቆራረጥ ለተባይ እና ለአረም ምቹ ነው። በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት ደግሞ በሁለት ወረዳዎች (ድሃና እና ዝቋላ) መደበኛ ተባዮች በተለይ ፌንጣ ወደ አንድ ሺህ 334 ሄክታር ማሳ ላይ ተከሰቶ ነበር፤ የኬሚካል ግዥ ተፈጽሞ ርጭት በማካሄድ ችግሩን ለመቆጣጠር ጥረት ተደርጓል።

እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ ለ46 ሺህ ያህል አርሶ አደሮች በአጠቃላይ የግብርና ሥራዎች ዙሪያ ግንዛቤ ተፈጥሯል። በተለይ ኢልኒኞን በተመለከተ ግንዛቤን በመፍጠር አርሶ አደሩ ችግሩን መቋቋም የሚችሉባቸውን መውጫ መንገዶችን መሠረት ያደረገ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጓል።

“ችግሩ እንደተፈጠረ በመጀመሪያ ዕቅድ አዘጋጀን፤ ድርቅን የሚቋቋሙ እና ፈጥነው የሚደርሱ የሰብል ዝርያዎችን አቅርበናል፤ ሦስት ሺህ 417 ያህል ኩንታል ማሳ ፈጥነው የሚደርሱ እና ድርቅን የሚቋቋሙ ዘሮችን ከረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን ተደራሽ አድርገናል” ብለዋል።

በአጠቃላይ ከ59 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ፈጥነው በሚደርሱና ድርቅን በሚቋቋሙ የሰብል ዘሮች ለመሸፈን ጥረት ተደርጓል። በቆላው አካባቢ ዕንቁ ዳጉሳ እና ማሾ (በውስን እርጥበት የተሻለ ምርት የሚሰጡ) በመዝራት ችግሩን ለመቀነስ ተችሏል። በተመሳሳይ በደጋው አካባቢ ምስር፣ በዝናብ እጥረት ወቅት የሚዘሩ የሽምብራ ዝርያዎች፣ ገብስ፣ ጤፍ (በተለይ ጸደይ የሚባለው የጤፍ ዝርያ) እና ስንዴ አርሶ አደሩ የእርጥበት መያዣ ስልቶችን አቀናጅቶ በመሥራት ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

እንደ የሰብል ልማት ቡድን መሪው ሦስት ሺህ 417 ያህል ኩንታል ምርጥ ዘር ተሰራጭቷል፤ የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ከ13 ሺህ 953 ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ ደርሷል።

በተመሳሳይ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ደጀኔ ከበደ ለበኵር በስልክ እንዳሉት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በመኸር እርሻው ከ58 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ባለው 58 ሺህ 132 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል።

ከዚህም ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል። ይሁን እንጂ የዝናቡ ስርጭት በዕቅዱ ላይ ስጋት ፈጥሯል። ባቲ ዙሪያ፣ ባቲ ከተማ፣ ደዋጨፋ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የዝናብ እጥረቱ ከፍተኛ ነው።

ችግሩን ለመቋቋም ታዲያ በተዋረድ ታች ድረስ ግብረ-ኀይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል። አርሶ አደሮች ፈጥነው የሚደርሱ እና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን እንዲዘሩ እና በአካባቢው ያሉ የውኃ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ መፈጠሩን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ የክረምት ወቅት የግብርና ተግባራትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ በየዞኑ ያሉትን ተስፋዎች እና ፈተናዎች በአንድ አውድ ለማስተሳሰር ክልሉ ሰፊ ስትራቴጂ ነድፏል። ክልሉ ዘንድሮ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን አቅዷል። ከዚህም 205.2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ወደ ሥራ ገብቷል።

የቢሮ ኃላፊው የክልሉን የሰብል ልማት በሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች ከፍለውታል። አንደኛው የምግብ ዋስትና ሲሆን 61 በመቶውን ይሸፍናል። ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ግብዓት ሲሆን 31 በመቶ ድርሻ አለው። ሦስተኛው ደግሞ ለኤክስፖርት የሚውል ምርት ሲሆን ቀሪውን ስምንት በመቶ ይይዛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተከሰተው የዝናብ ስርጭት መዛባት ምክንያት ሊኖር የሚችለውን ስጋት ለመቀነስ የተለያዩ መፍትሔዎች እየተተገበሩ መሆኑን አቶ ደረጄ ተናግረዋል። አሁናዊ የሰብሉን ቁመናም “መልካም ነው” ብለውታል።

በተለይ ደግሞ እርጥበት የማሰባሰብ፣ ውኃን የመያዝ እና የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በደጋፊ መስኖ የመጠቀም ሥራዎችም እየተሠሩ ይገኛሉ። “አሁን ሁላችንም አርሶ አደሩን የምንደግፍበት፣ ያሉንን አቅሞች ሁሉ ተጠቅመን ተገቢውን የማሳ እንክብካቤ ሥራ የምንሠራበት ነው” ብለዋል።

አቶ ደረጄ ሌላው በልዩ ትኩረት ያነሱት ጉዳይ የኩታ ገጠም (ክላስተር) እርሻን ነው። ከታቀደው መሬት ውስጥ ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታሩን በኩታ ገጠም ለማልማት ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ያህሉ ማሳ በዚሁ መንገድ ለምቷል። በምርት ዘመኑ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታሉ ተሰራጭቷል። ከ309 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርም ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ሆኗል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀገራችን ግብርና ከዕድሜው ጋር ያልተጓዘ እና ከበሬ ጫንቃ ላይ ያልተላቀቀ ነው። ይህ ባሕላዊ ጉዞው ታዲያ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንኳን አላስቻለውም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው የእርሻ ሜካናይዜሽን ጉዞ ደግሞ ለዘርፉ ትልቅ መነቃቃት ሆኖታል።

እንደ አቶ ደረጄ ማብራሪያ ዘንድሮ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በትራክተር ታርሷል። ይህ ከጠቅላላው እርሻ 24 በመቶውን ይሸፍናል። መንግሥት ደግሞ የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ባንኮችም ለአርሶ አደሩ ብድር እያመቻቹ ነው።

ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው አሁናዊ የአንድ ሄክታር ማሳ ምርታማነት 33 ነጥብ ዘጠኝ ኩንታል ነው። በዘንድሮው የምርት ዘመን ደግሞ 36 ነጥብ ሰባት ኩንታል በሄክታር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ነው።

 

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የነሐሴ  25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here