የጋብቻ ውል

0
413

አዲስ ዓመት ሲመጣ በርካቶች የተለያዩ  እቅድ ይነድፋሉ፡፡ ከነዚሕም አንዱ ጋብቻ ነው፡፡ ጋብቻ ለመመስረት ሲታሰብ ደግሞ    ሕጋዊ  ማድረግ ሌላው የእቅዱ አካል እንዲሆን የሕግ ባለሙያው አቶ ጊዜው ገነት ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጊዜው እንደሚገልፁት የጋብቻ ሕግ  የራሱ የሆነ የጋብቻ አዋጅ አለው።  በኢትዮጵያ የአዋጅ ቁጥር የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 የሚባል የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አለ። በተመሳሳይ  የአማራ ክልልም  ራሱን የሆነ አዋጅ ቁጥር 79/1995 የተባለው የጋብቻ ሕግ አለው።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ   ጋብቻ ማለት ለአካለ መጠን የደረሱ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ለዘለቄታው አብሮ ለመኖር የግል ሀሳባቸውን በራሳቸው ነፃ ምርጫ በሕግ ለማዋሃድ ፈቅደው እና ወደው በይፋ የሚመሰርቱት ግንኙነት ወይም ደግሞ በዚያው ግንኙነት አማካኝነት የሚዋቀር ሕጋዊ የሆነ ተቋም ነው።

የጋብቻ ውል ለምን አስፈለገ?

ባሉያው እንደሚገልፁት ጋብቻ ሲፈፀም ሕጋዊ ውል ለምን አስፈለገ? የሚለው ሲታይ  አዋጁም የወጣበት ዋና ምክንያት ጋብቻ የማህበረሰብ እና የመንግሥት ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ተቋም በመሆኑ ነው። ሌላው ደግሞ የልጆች ደህንነት እና አስተዳደግ  ጥበቃን በተመለከተ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከክልሉ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተስማምቶ ለመተግበር እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ የሚነሱ ክርክሮችን ፍታዊ በሆነ መልኩ እንዲዳኙ ለማድረግ ነው።

የጋብቻ አይነቶች

ጋብቻ በተለየ ሁኔታ  በተለይም በዋናነት በሦስት አይነት መልኩ ጋብቻ ሊፈጸም ይችላል። አንደኛው አሁን ስልጣን የተሰጠው አካል በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚደረግ የጋብቻ አይነት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሃይማኖትን መሰረት አድርጎ እንደየእምነቱ የሚፈጸም ጋብቻ ነው። ሦስተኛው  በባህል ስርዓት የሚፈጸም ጋብቻ ነው።

በአሁን ባለው ቴክኖሎጂ ደግሞ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1370/2017 በፊት /ወሳኝ ኩነት/ በሚባለው መመዝገብ አለባቸው፡፡ እነዚህ ሁሉም የጋብቻ ዓይነቶች በሕግ ፊት ተመሳሳይ ውጤት ያላቸው ናቸው።

ጋብቻ ለመፈጸም የሚያስፈልጉ  ቅድመ ሁኔታዎች

በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግም ሆነ በአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ ጋብቻ ለመፈጸም የሚያስፈልጉ  ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠውለታል፡፡ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ የሁለቱ ተጋቢዎች ነፃ ፈቃድ ነው። ጋብቻ ወዶ እና ፈቅዶ በራስ ፍላጎት እና ነፃ ፈቃድ  መመስረት ስላለበት እንደ ቅድሞ ሁኔታ ይቆጠራል።

ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ እድሜ ነው። ኢትዮጵያ ሕፃናት ብላ የምትጠራቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉትን ነው። ስለዚህ ጋብቻ ሕፃናት ሊመሰርቱ አይችሉም ማለት ነው። ስለዚህ ጋብቻ ፈቃድ እና እድሜን በቅድመ ሁኔታዎች የግድ ሊያሟሉ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።

የጋብቻ ውጤት

የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት “ጋብቻ ውጤት አለው” ሲባል በዋናነት ሁለት ዋና ዋና ውጤቶች አሉት። እነሱም ግላዊ ውጤት እና የንብረት ውጤት ናቸው፡፡ ግላዊ ውጤት ሲባል ጋብቻ የሚመሰረተው በሁለቱ ተጋቢዎች መካከል በመከባበር፣ በመተጋገዝ እና በመደጋገፍ  ኑሯቸውን እንዲመሰርቱ ለማድረግ ነው። ስለሆነም ባል እና ሚስት በጋራ ተስማምተው ንብረታቸውን… እያንዳንዱ በተለይም ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት አመራር ነው። በሌላ በኩል መተጋገዝ እና መደጋገፍ የሚባለው ባል እና ሚስት በዋናነት የሚጋቡት አንዱ የአንዱን ፈቃድ ለመፈጸም  ነው። ስለዚህም ሁለቱም የመኖሪያ ስፍራቸውንም በጋራ ይወስናሉ ማለት ነው።

የንብረት ውጤት የሚባለው ደግሞ የንብረት አስተዳደርን የተመለከተ ነው። ባል እና ሚስት እኩል ኃላፊነት ስላለባቸው በንብረት ላይም የራሳቸውን ንብረት በራሳቸው ወደው እና ፈቅደው የሚያስተዳድሩበት ሁኔታ አለ ማለት ነው።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ንብረት ሲባል የግል፣ የውርስ፣ ከጋብቻ በፊት የነበረና የግሌ ንብረት ፣ተብሎ ከተመዘገበ ባል ወይም ሚስት ያንን በግሏ የምታስተዳድርበት ወይም በግሉ የሚያስተዳድርበት  ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል የጋራ ንብረት አለ። በጋራ ንብረት ላይ ባል እና ሚስት ንብረታቸውን እኩል ያስተዳድራሉ ማለት ነው። ባል… ባል ስለሆነ ብቻ ንብረት እንደግል የሚያስተዳድርበት፣ ሚስት ስለሆነች ብቻ በንብረቷ ላይ የማታዝዝበት ወይም ሌላ ነገር የማታደርግበት ሁኔታ የለም። ስለዚህ ንብረቱ በጋራ ይተዳደራል ማለት ነው።

የንብረት ውጤት  መጀመሪያ ላይ ሲጋቡ አንድ ሰው ከወላጆቹ የወረሰው ወይም ደግሞ ሚስት ከወላጆቿ የወረሰችው ንብረት ሊኖራቸው ይችላል። ስለዚህ ያንን ንብረት የጋራ ማድረግ ከፈለገች/ገ የጋራ ንብረታችን በጋራ ሊስተዳድር ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል። በሌላ በኩል ግን ሠርተን የምናገኘውን ንብረት የጋራ እናደርጋለን፣ ይህ ንብረት ግን የግል ነው ብለው ካስመዘገቡ የግል የመጣ ንብረት የግል እንደሆነ ይቀጥላል ማለት ነው። ነገር ግን ብዙ  ከዛ የሚገኘው ፍሬ የጋራ የሚሆንበት፣ በተለይም ደግሞ ዓላማው ለቤተሰብ አገልግሎት የሚውልበት ሁኔታ አለ።

የጋብቻ ውል በሕግ ፊት ላይፀና የሚችልባቸው መንገዶች

የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት በሕግ ፊት የጋብቻ ውል ላይፀና የሚችልባቸው  አያሌ ሁኔታዎች አሉ። የመጀመሪያው ነፃ ፈቃድ ሳይገኝ ሲቀር ነው። ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል ወዶ እና ፈቅዶ ነው መመስረት ያለበት። ይሁንና ጋብቻው የተፈጸመው በአንደኛው አስገዳጅነት  ከሆነ አንደኛው  እንዳይፀና ያደርገዋል ማለት ነው።

የጋብቻ ውል በሕግ የማይፀናበት ሌላው ምክንያት እድሜ ነው፤ የተጋቢዎቹ እድሜ ከ18 ዓመት በታች ከሆነ በሕግ ፊት ውል መፈፀም ስለማይችሉ እንዲሁም ወደው እና ፈቅደው ስለማይፈርሙ ጋብቻ ላይፀና የሚችልበት ሁኔታ ነው። ሦስተኛው ደግሞ በስጋ ወይም በጋብቻ ዝምድና ላይ የተመሰረተ ካለ ጋብቻ የሚፈርስበት ወይም ደግሞ የማይፀናበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው።

የንብረት ውርስ

የጋብቻ ውላቸውን በሕግ ፊት የፈፀሙ ጥንዶች አንደኛው  በሞት ሊለይ ይችላል፡፡  በኢትዮጵያ የውርስ ሕግ መሰረት አንድ ሰው ወዲያውኑ እንደሞተ የውርስ ሕግ  ተግባራዊ ይሆናል። ባለሙያው አቶ በጊዜው እንደሚገልፁት ይህ ማለት ንብረትን ለማስተዳደር ለምሳሌ በባል ስም ተመዝግቦ የነበረ ሀብትና ንብረት  ካለ ሚስት  የጋራ ሀብቷ ስለሆነ ንብረቱን ለማስተዳደር ትችላለች፡፡ ስለዚህ በፍትሃብሔር ሕግ መሰረት  ንብረቱ ወደ ወራሾቹ ወዲያውኑ ይተላለፋል።

ለዚህ ምክንያቱም ንብረቱ እንዳይባክን ፣ ከዛ ውጭ ደግሞ ልጆቹ ወይም ደግሞ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ከሆኑ  በአንደኛው ወገን መሞት ምክንያት ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የቤተሰብ ሕጉ ጥበቃ ያደርጋል። በዚህ መሠረት ልጆችን ለማስተዳደር የሞግዚትነት እና አስተዳዳሪነት ባል ከሞተ ሚስት ታወጣለች፣ ሚስት ከሞተች ደግሞ ባል ያወጣና ልጆቹን የመንከባከብ ኃላፊነት ይጣልበታል፡፡ እንዲሁም ልጆቹ  ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ ማስተዳደር ስለማይችሉ ሞግዚት ወይም አስተዳዳሪ ተብለው  በፍርድ ቤት የሚፈቀድላቸው ያንን ንብረት ያስተዳድራሉ ማለት ነው። ያንን ንብረት ካስተዳደሩ ደግሞ ልጆቹን በአግባቡ የመንከባከብ እና የማሳደግ ኃላፊነት ይኖርበታል ማለት ነው።

የሕግ አንቀፅ

  • የጋብቻ ዝምድና በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 8 እና 9 ስር እንደተደነገገው ሁለት የዝምድና አይነቶች አሉ፡፡ እነሱም የስጋ እና የጋብቻ ዝምድና ናቸው፡፡
  • የስጋ ዝምድና ሲባል በቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 8 መሠረት ቀጥታ የስጋ የስጋ ዘመዳሞች (በወላጅና በተወላጆች/አባት እና ልጅ/እናት እና ልጅ/አያት እና የልጅ ልጅ) እና ወደ ጎን በሚቆጠሩ የሥጋ ዝምድና አንድ ወንድ ከእህቱ ወይም ከአክስቱ እንዲሁም አንዲት ሴት ከወንድሟ ወይም ከአጎቷ ጋር የተከለከለ  ነው፡፡
  • የጋብቻ ዝምድና ደግሞ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 9 መሠረት ቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች (ባል ከሚስቱ እናትና፤ ሚስት ከባል አባት) ወደ ጎን በሚቆጠር የጋብቻ ዝምድና፣ ባል ከሚስቱ እህት ወይም ሚስት ከባሏ ወንድም ጋር ዘመድ እንደሆኑ ከቤተሰብ ሕጉ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here