በትምህርት ዓለም ውስጥ የስኬት ማማ ላይ መውጣት የተፈጥሮ ክህሎትን ብቻ ሳይሆን የማይበገር ጽናትን፣ ከፍተኛ መስዋዕትነትን እና ግልጽ ዓላማን ይጠይቃል። በ2018 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የማጠናቀቂያ ፈተና 587 ነጥብ 17 ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት በክልል ደረጃ የአንደኝነትን ደረጃ የተቀዳጀው ሙባረክ ሙሐመድ ለዚህ ሕያው ማረጋገጫ ነው።
ሙባረክ ትምህርቱን የጀመረው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ሳንጃ ከተማ ነበር። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ባለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሁልጊዜም በክፍሉ አንደኛ ደረጃን አስጠብቆ እንደዘለቀ ያስታውሳል፡፡ ይህ የትጋት ውጤት ሙባረክን በክልል ደረጃ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ወደሚሰበሰቡበት ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲያቀና መንገድ ከፈተለት።
ሙባረክ እንደ እርሱ ከ9ኛ ክፍል ከየአካባቢው የመጡ ጎበዝ ተማሪዎች በተሰበሰቡበት ግቢ ውስጥ የነበረው ከፍተኛ ውድድር መጀመሪያ ላይ የነበረውን አእምሮአዊ ዝግጅት ፈትኖት እንደነበርም ያስታውሳል። ሆኖም ሙባረክ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በጽናት አልፎ ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በነበረው ቆይታ በክፍሉ ሁልጊዜም አንደኛ በመውጣት የላቀ ብቃቱን አስመስክሯል።
ተማሪው ለዚህ ታላቅ ውጤት ያበቃውን የጥናት ስልት ማንኛውንም ርዕሰ ጉዳይ ከማንበቡ በፊት የሚያውቀውን ነገር በጭንቅላቱ ያሰላስላል፤ ከዚያም ከትምህርቱ ማወቅ ያለበትን ዋና ዋና ሀሳቦች መጨበጡን ለራሱ ይጠይቃል። ከንባብ በኋላም ዋና ዋና ነጥቦችን ያዘጋጃል። ንባቡን ሲያጠናቅቅ የክለሳ ጊዜ በመመደብ መልሶ እራሱን በመጠየቅ ያጠናቅቃል፡፡ ከዚያም የተለያዩ ፈተናዎችንና ጥያቄዎችን እንደ ሚሠራ አብራርቷል።
ከግል ጥረቱ በተጨማሪ ለዚህ ውጤት ያበቁት የወላጆቹ ያልተገደበ ድጋፍ፣ የመምህራን ከፍተኛ እንክብካቤ፣ የደሴ ከተማ ማህበረሰብ ለትምህርት ያለው አዎንታዊ አስተያየት እና የጓደኞቹ ማበረታታት እንደሆነ ሙባረክ ተናግሯል፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ ለቴክኖሎጂ እና ለኢንጂነሪንግ ዘርፍ ልዩ ፍላጎትና ዝንባሌ ያለው ሙባረክ በቀጣይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን በመከታተል ሀገሩን በቴክኖሎጂ ዘርፍ የማገልገል ትልቅ ህልም አለው። ሙባረክ እንደ ሚለው ማንኛውም ተማሪ ውጤታማ ለመሆን መጀመሪያ ራሱን ማዳመጥ እና የሚስማማውን የጥናት መንገድ መከተል እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ ”ጥናት ሁልጊዜ የሚያስደስት ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ እየመረረንም ልናጠና እንችላለን፤ ዓላማ ስላለንም ወደ ኋላ ማለት የለብንም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያለ መስዋዕትነት ድል የለም፤ ማንኛውንም ትልቅ ነገር ለማሳካት መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት መክፈል አለብን” በማለት እርሱን ለውጤት ያበቃውን መንገድ አጋርቷል፡፡
በተመሳሳይ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ በሚገኘው የአገውምድር 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዋ ሕዳሴ ዘመኑ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና 583 በማምጣት በሀገር ደረጃ ከሴቶች ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግባለች፡፡
ለፈተናው ልዩ ትኩረት በመስጠት ቀድማ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋ እንደነበርና በዚህም የድካሟን ፍሬ እንዳገኘች ለአሚኮ የተናገረችው ሕዳሴ ዘመኑ፤ ከ11ኛ ወደ 12ኛ ክፍል ስታልፍ ባስመዘገበችው ከፍተኛ ውጤት በስሟ ቤተ መጻሕፍት ተሰይሞላታል፡፡
በቀጣይ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትምህርቷን በመከታተል ለሀገሯ የበኩሏን ማበርከት እንደምትፈልግም ገልጻለች፡፡ ለውጤት ያበቃት የመምህራንና የወላጆቿን ምክር ወደ ተግባር መቀየሯ፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀሟ እንደሆነም ተናግራለች፡፡
ሌላው ውጤታማ ተማሪ አብርሐም ደይኖ ይባላል፡፡ የአብርሐም የትምህርት ጉዞው ቀጥተኛ አልነበረም። ከመጽሐፍ በፊት የእርሻ ሥራን ማወቅ የግድ የሆነበት ልጅ ነበር።
አብርሐም የተወለደው፣ ያደገውና እስከ 11ኛ ክፍል የተማረው በደጋዳሞት ወረዳ ዳባ ባጫ ቀበሌ ነው።
የአብርሐም የትምህርት ጉዞ ከእርሻ ሥራ የተነጠለ አልነበረም። ከልጅነቱ ጀምሮ ቤተሰቡን በእርሻ ሥራ ማገዝ የዕለት ተዕለት ተግባሩ ነበር።
“ትምህርቴን የተከታተልሁት ከሥራ ጋር ነው” የሚለው አብርሐም፣ ይህ ሁኔታ ግን በትምህርቱ ላይ ጫና ፈጥሮ ትምህርቱን እንዲጠላ እንዳላደረገው ከበኵር ዝግጅት ክፍል ጋር በስልክ ባደረገው ቃለ ምልልስ ጠቁሟል።
አብርሐም በክልሉ በተከሰተው የሰላም እጦት ትምህርት በአካባቢው ተቋርጦ ቆይቷል። በዚያ ወቅት ብዙ ጓደኞቹ ከትምህርት ተለይተው ወደ ችርቻሮና ወደ ሌሎች ሥራዎች ገቡ። አንዳንዶቹም ተስፋ ቆረጡ። አብርሐም ግን ከትምህርት ገበታው እንደማይለይ በውስጡ እምነት ነበረው።
አካባቢው ሰላም ይሆናል፤ ትምህርት ይቀጥላል” የሚል፡፡
በዚያ ወቅት መጽሐፍ ከፍቶ ማንበብ ግን ቀላል አልነበረም። እንደ አርሶ አደር ሥራውን ይቀጥላል፤ ማንበብ የሚባለው ግን ከሕይወቱ ርቆ ነበር።
በዚያ ጊዜ ግን ጉብዝናውን የሚያውቁ መምህራን ተስፋ እንዳይቆርጥ ደውለው “አይዞህ አንብብ!” በማለት ሲያበረታቱት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ እሱም እነሱን ላለማሳዘን “እያነበብሁ ነው” ይላቸው እንደነበር ይናገራል። እውነቱ ግን በዚያ ወቅት ማንበብ እንደማይችል ነበር።
ያለ ትምህርት ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው አብርሐም ተስፋውን የሚያለመልም ብስራት ሰማ፡፡ በ11ኛ ክፍልን ባስመዘገበው የላቀ ውጤት አማካኝነት የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለጎበዝ ተማሪዎች በሰጠው እድል ተመርጦ በዋናው ግቢ በ2018 የትምህርት ዘመን መከታተል ቻለ።
አብርሐም በትምህርት ጉዞው በጋጠሙት መሰናክሎች ሁሉ ከዓላማው እንዲያፈነግጥ አልፈቀደም። ሙሉ ትኩረቱን ለትምህርት ማድረግ ቻለ። 12ኛ ክፍልን ለመፈተን ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ግቡ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት አልነበረም። “መጀመሪያ ትምህርቴን መቀጠል፤ ከዛም ማለፍ አለብኝ” የሚል ነበር፡፡ የፈተና ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ ግን የማለፍና የመውደቅ ስጋት ቀስ በቀስ ተወገደ። በምትኩ “የተሻለ ውጤት ማምጣት እችላለሁ” የሚል ሐሳብን ያዘ።
የተቋረጠውን ትምህርት ለማካካስ ያገኘውን ጊዜ በቻለው መጠን ተጠቀመበት። ውጤቱም 533 ሆነ። ይህ ቁጥር ለአብርሐም የፈተና ውጤት ብቻ አይደለም፤ ከሁለት ዓመት በኋላ የተገኘ ተስፋ፣ ከእርሻ ሥራ ጋር የተደረገ ትግል፣ ከጦርነት ጋር የተጋፈጠ ወጣትነትና ያልተሰበረ ተስፋ ውጤት ነው።
አብርሐም ይህን ውጤት በራሱ ጥረት ብቻ እንዳላገኘ ያምናል። መምህራንን፣ የወረዳውን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ተቋማት አመራሮችን በልዩ ሁኔታ ያመሰግናል።
አብርሐም እንደሚገልፀው መምህራኖቹ ራሳቸው በችግር ውስጥ ሆነው ለእሱና ለጓደኞቹ ተስፋ እንዳይቆርጡ ስልክ ደውለው ያበረታቷቸው ነበር። የወረዳና የዞን የትምህርት አካላትም በተደጋጋሚ እየጎበኙና እያወያዩ ድጋፋቸውን ይገልጹላቸው ነበር።
“የነሱ ማበረታታት ከማስተማርም በላይ የሆነ ድጋፍ ነበር” ሲል ያመሰግናል።
ለወደፊቱ የኢንጂነሪንግ ዘርፍን እንደሚፈልግ ይናገራል። በተለይም የሚፈልገው የኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ መስክ ነው። ይህን ዕድል ካላገኘም በሌሎች የኢንጂነሪንግ ዘርፎች ለመሥራት ፍላጎት አለው።
በአሁኑ ጊዜ ግን የመጨረሻ ዕቅዱ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግን መማር እንደሆነ ተናግሯል።
ከእርሻ መሬት የተነሳው ይህ ወጣት ወደ ቴክኖሎጂው ዓለም ለመግባት ያለው ፍላጎት፣ የሕይወቱን ሌላ ምዕራፍ ለመጀመር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
አብርሃም የራሱን ታሪክ በማውሳት በአሁኑ ችግር ውስጥ ላሉ ተማሪዎች አንድ ጠንካራ መልዕክት አለው።
“ችግር ትምህርትን ሊያቋርጥ ይችላል፤ ሁኔታዎች ሊያዘገዩት ይችላሉ፤ ጦርነትም ቢሆን ለዓመታት ሊያቆመው ይችላል። ነገር ግን ሰው በራሱ ውስጥ ያለውን የመማር ፍላጎት እስካልገደለ ድረስ መንገዱ እንደገና ሊከፈት ይችላል።ሰላም እስካለ ድረስ ተስፋ ሳንቆርጥ መማር አለብን” ይላል።
ከእርሻ ሥራ ወደ ትምህርት፣ ትምህርት ከመቋረጥ ወደ መመለስ፣ ከጦርነት ጥላ ወደ ትምህርት እድል የተጓዘው የአብርሐም ታሪክ ትምህርት ሁልጊዜ በተመቻቸ ሁኔታ እንደማይመጣ ያስታውሳል። አንዳንዴ መንገዱ ይቋረጣል፤ አንዳንዴ ዓመታት ይጠፋሉ፤ አንዳንዴም ሰው ተስፋውን ሊያጣ ይችላል። ነገር ግን የአብርሐም ታሪክ አንድ ነገር ይናገራል፦ መንገድ ቢዘጋም፣ ተስፋ እስካለ ድረስ ሌላ መንገድ ሊከፈት ይችላል።
መረጃ
- የትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተመዘገቡት 563 ሺህ 960 ተማሪዎች መካከል 550 ሺህ 210 የሚሆኑት ፈተናውን ወስደዋል።
• ከእነዚህም ውስጥ 70 ሺህ 544 ወይም 12.8 በመቶ የሚሆኑት ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ማለፍ ችለዋል።
• በ2017 ዓ.ም ያለፉ ተማሪዎች ምጣኔ 8.9 በመቶ ነበር።
• የማለፊያ ምጣኔው በትምህርት ዘርፎች ሲታይ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ 16.6 በመቶ፣ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8.33 በመቶ ተማሪዎች ማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል።
• በከፍተኛ ውጤት ደረጃ በተፈጥሮ ሳይንስ በወንዶች በኦሮሚያ ክልል የአዳማ ኦዳ ስፔሻል ቦርዲንግ ትምህርት ቤት ተማሪ 591.6 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል።
• በሴቶች ደግሞ ከአማራ ክልል እንጅባራ አገው ምድር ትምህርት ቤት ተማሪ 583 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት ይዛለች።
• በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በወንዶች ከፍተኛው ውጤት 576 እንዲሁም በሴቶች 569 ሆኖ ተመዝግቧል።
• 88 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፍ ሲችሉ፣ በአንጻሩ 565 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ ማሳለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


