በአዲሱ ዓመት ሰላምን እናስፍን!… የዋጋ ንረትን እንግታ!

0
52

የዋጋ ንረት ከምጣኔ ሀብት ችግርነት አልፎ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ እየሆነ ነው። በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ገቢያቸው ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ  የዕለት ተዕለት ወጪያቸው በፍጥነት ስለሚጨምር በእጅጉ እየተጎዱ ነው፡፡ በበዓላት ወቅት ደግሞ የዋጋ ጭማሪው በጣም ይጋነናል።

የኑሮ ውድነት የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ማኅበራዊ ደኅንነትን፣ የቤተሰብን እና የአዕምሮ ሰላምን ያሳጣል፡፡ የዋጋ ንረት ዜጎች አስፈላጊውን የተመጣጠነ ምግብ  እንዳያገኙ ያደርጋል፤ ለትምህርት እና ለጤና የሚያውሉት ወጪ ስለሚቸግራቸው ለጭንቀት እንዲሁም ለጤና መቃወስ ይጋለጣሉ። ይህ ሁኔታ በቤተሰብ ውስጥ አለመግባባትን  በማስከተል ለማኅበራዊ ሕይወት መናጋት ምክንያት ይሆናል፡፡ ተካፍሎ የመብላትን፣ የመረዳዳትን፣ የመጠያየቅን፣ በዓላትን አብሮ የማሳለፍን መልካም ዕሴት ይሸረሽራል፤ ሕዝቡ ሳይወድ በግድ የግለኝነት አስተሳሰብ እንዲያዳብር ያስገድዳልና፡፡

በመሆኑም የኑሮ ውድነቱን መንስኤዎች መርምሮ መፍትሄ መሻት ግድ ከሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ያለ ቅጥ እየናረ ያለው የኑሮ ውድነት የተለያዩ ርስ በርስ የተሳሰሩ መንስኤዎች እንዳሉት የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ጫና፣ የብር የመግዛት አቅም  መዳከም፣ የምርት እና የአቅርቦት አለመጣጣም፣ የማጓጓዣ ወጪ መጨመር እና የገበያ ቁጥጥር ክፍተትአ እንዲሁም የሰላም መታጣት  እየተስተዋለ ላለው የዋጋ ንረት አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ችግሮች ናቸው።

ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ከውጭ በሚገቡ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒት እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች ላይ ጥገኛ ናት። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እና የብር የመግዛት አቅም መውረድ ደግሞ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች ዋጋ ጣሪያ እንዲነካ አድርጓል። በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚመረተው ምርት ከሸማቹ ፍላጎት ጋር አለመመጣጠኑ እና የማጓጓዣ ወጪዎች በየጊዜው ማሻቀባቸው የዋጋ ንረቱን አባብሰውታል። ገበያው ፍትሐዊ በሆነ የገበያ ሥርዓት እንዲመራ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ አለመቻሉ እና ሸቀጦችን በመጋዝን የመደበቅ አባዜ አለመወገም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ፈጥሯል።

በሀገራችን እየተስተዋለ ያለው  ግጭትም የማምረትን እንዲሁም የተመረተውን የማጓጓዝ ሂደትን ክፉኛ እያደናቀፈው ይገኛል። ሰላም በሌለበት  ማሳን ማረስ፣ ማምረት፣ የተመረተውን መሰብሰብ፣ የተሰበሰበውን ወደ ገበያ ማውጣት በእጅጉ ከባድ ይሆናል። መንገድ ሲዘጋ የማጓጓዣ ወጪው ይንራል። የሰላም መታጣት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን፣  ከጎብኚዎች እንዲሁም ከወጪ ንግድ የሚገኝ ገቢን በማዳከም  የውጭ ምንዛሪ የማመንጨት አቅምን በእጅጉ ያዳክማል።

ስለሆነም በአዲሱ ዓመት እነዚህን ችግሮች በመፍታት ገበያውን ለማረጋጋት መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ሸማቹ የራሱን  ርምጃዎች በመውሰድ ገበያውን ለማረጋጋት መጣር ይኖርበታል፡፡ ወጪዎችን በዝርዝር መመዝገብ እና ቢቀሩ የማይጎዱ ወጪዎችን መቀነስ፣ በተናጠል በችርቻሮ  ከመግዛት ሰብሰብ ብሎ ከአከፋፋዮች፣ ከሸማች ማኅበራት እንዲሁም ከአርሶ አደሩ መግዛት የዋጋ ንረት ችግሩን ያቃልላል። ብክነትን መቀነስ፤ የቤት ውስጥ ፍጆታን በአግባቡ ማስተዳደርም ይገባል።

መንግሥትም ለችግሩ መፈታት ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፤  የአጭር እንዲሁም የረዥም ጊዜ መፍትሄዎችን በመለየት፡፡ ከአጭር ጊዜ መፍትሔ አንጻር ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚደረገውን ማኅበራዊ ድጋፍ ማጠናከር፣ ገበያውን ከደላሎች እና ከሕገ-ወጥ ነጋዴዎች አጽድቶ  በገበያ ሥርዓት እንዲመራ መሥራት ይኖርበታል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በዝናብ ላይ የተመሠረተውን አመራረት በመስኖ እርሻ መተካት፣ የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ምርት ማሳደግም የዋጋ ንረት ችግሩን ለማቃለል በዘላቂነት ሊወሰድ የሚገባው መፍትሄ ነው።

የወጪ ንግድን ማብዛት እንዲሁም የገቢ ንግድን መቀነስም ሌላው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚረዳ መፍትሄ ነው፡፡ የወጪ ንግዱን ከቡና እና ቆዳ ምርት በተጨማሪ  ሌሎች የኢንዱስትሪ እና የግብርና ውጤቶችን በስፋት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ አቅምን ማጎልበት ይገባል። ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እና አስተማማኝ እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ማስፈንም የዋጋ ንረትን ለመግታት ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ስለሆነም በአዲሱ ዓመት ሰላምን በማስፈን የዋጋ ንረትን ለመግታት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል፡፡

በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here