የሊዮኔል ሜሲ እና የክርስቲያኖ ሮናልዶ የሁለት አስርት ዓመታት ገናናነት ማብቃቱን ተከትሎ የእግር ኳሱ ዓለም አዲስ ንጉሥ ለመሾም በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል። ይሁን እንጂ የ2026ቱ የባሎንዶር ሽልማት ከወትሮው የተለየ ትኩረት የሳበው በሰሜን አሜሪካ ምድር በተካሄደው 23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ተመሳሳይ ዓመት መደረጉ ነው።
የ2026ቱ የባሎንዶር ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በለንደን ከተማ በለንደን ፓላዲየም ቴአትር ይካሄዳል። የዘንድሮው ባሎንዶር በተጫዋቾች የግል አስደናቂ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ በክለብ ስኬት እና በቅርቡ በተጠናቀቀው ታላቁ የዓለም ዋንጫ አህጉራዊ ተጽዕኖ ላይ ተመስርቶ የሚወሰን ብርቱ ፉክክር ሆኗል።
የእግር ኳስ ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳስመሰከረው የዓለም ዋንጫ በሚካሄድበት ዓመት የባሎንዶር ሽልማት የሚወሰነው በክለብ ውድድሮች በሚቆጠሩ ግቦች ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ታላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በሚታየው ወሳኝ ብቃት ነው። እናም የ2026ቱ የባሎንዶር አሸናፊ ዕጣ ፈንታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ስታዲየሞች ውስጥ በፈጠሩ አስማታዊ ምሽቶች የሚወሰን ይሆናል።
ለሽልማቱ የታጩ 30 ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ተጫዋቾች (የፈረንሳዩ ኮከብ ኪሊያን እምባፔ፣ የባርሴሎናው ታዳጊ ላሚን ያማል እና የባየርን ሙኒኩ የግብ ማሽን ሀሪ ኬን) ስማቸው በተደጋጋሚ በስፋት እየተነሳ ይገኛል፡፡ ይህንን እውነታ መሰረት በማድረግ ስንመረምር ኪሊያን ምባፔ ሽልማቱን ለማንሳት በቀዳሚነት ይቀመጣል። እምባፔ በሪያል ማድሪድ ቤት ያሳየው አስደናቂ የውድድር ዘመን እንዲሁም ክለቡ ያለው የሚዲያ ተጽዕኖ ለሽልማቱ ትልቅ ግምት እንዲያገኝ አድርጎታል። ቢቢሲ ባወጣው መረጃ መሰረት በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እና በክለብ ቤት የነበረው ስኬት ለሽልማቱ ቀዳሚ ተጠቃሽ ሲያደርገው በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በአጠቃላይ 66 ግቦችን እና 15 ግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል በአጠቃላይ 82 የግብ ተሳትፎዎችን አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል ላሚን ያማል ገና በታዳጊነት ዕድሜው በአውሮፓ እግር ኳስ እና በዓለም ዋንጫው ላይ ያሳየው አስደናቂ ተፅዕኖ የዓለምን ትኩረት ስቧል። ከባርሴሎና ጋር በላሊጋው ካሳየው ድንቅ ብቃት በተጨማሪ የስፔንን ብሔራዊ ቡድን በመምራት በዓለም ዋንጫው መድረክ ላይ ያሳየው ስኬት ለሽልማቱ ትልቅ ግምት እንዲያገኝ አድርጎታል። በውድድር ዘመኑ 25 ግቦችን በማስቆጠር እና 18 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት በአጠቃላይ በ43 ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን ገና በታዳጊነቱ በሜዳ ላይ የሚፈጥረው አደገኛ እንቅስቃሴ እና ያሳየው ብስለት ልዩ መመዘኛ ሆኖ ቀርቧል።
ሀሪኬን ባለፈው የውድድር ዘመን ለባየርን ሙኒክ እና ለሀገሩ ያስመዘገበው 73 ግቦች (በክለቡ ብቻ በ51 ጨዋታዎች 61 ግቦች አስቆጥሯል፤ ሰባት ግብ የሆኑ ኳሶችን አቀብሏል)። ይህ በክለብ ደረጃ ያሳየው ፍጹም የበላይነት ድምጽ ሰጪዎችን ለመማረክ ዋነኛው መሳሪያ ሆኖለታል።
ይህንን ዘውድ ለመድፋት የሚደረገው ጉዞ ለዕጩዎቹ ቀላል አይደለም። የመጀመሪያው ተግዳሮት የተጫዋቾቹ የቡድን ስኬት እና የግል ክብር አለመመጣጠን ነው። ለምሳሌ ኬን በግል ድንቅ ቢሆንም ትልልቅ አህጉራዊ ዋንጫዎችን አለማንሳቱ ድምጽ ሰጪዎች ላይ ጥርጣሬ ሊፈጥር ይችላል። በአንጻሩ ባለፈው ዓመት የሽልማቱ አሸናፊ የነበረው ኡስማን ዴምቤሌ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማሸነፉ ሽልማቱን እንዲያሸንፍ አድርጎታል። ሌላው ሽልማቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቡድን ዋንጫዎች ይልቅ ለግል አስደናቂ ብቃቶች ትኩረት እንዲሰጥ የሚጠይቁ የተጫዋቾች ግፊት እና የሚዲያ ዘመቻዎች መበራከታቸውን ስካይ ስፖርት አስነብቧል፤ እናም ዘንድሮ የዓለም ዋንጫው ውጤት እና የተጫዋቾች የግል ተፅዕኖ የድምፅ አሰጣጡን ሂደት ሙሉ በሙሉ ሊቀይረው ይችላል።
በሌሎች ዘርፎች በሚደረጉት ሽልማቶች በሴቶች ባሎንዶር የሦስት ጊዜ አሸናፊዋ አይታና ቦንማቲ ከዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ ውጭ ሆናለች፡፡ የሁለት ጊዜ አሸናፊዋ አሌክሲያ ፑቴላስ ለዘንድሮው ባሎንዶር ቀዳሚዋ ተገማች ናት። የማንቸስተር ሲቲዋ የግብ ማሽን ኻዲጃ ባኒ ሾው እና የአርሴናሏ አሌሲያ ሩሶ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ሆነው መቅረባቸውን የሴቶች እግር ኳስ ጋዜጠኞች አመልክተዋል ።
የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝ እጩዎችን በተመለከተ በወንዶች የአርሴናሉ አለቃ ሚኬል ፣ የፒኤስጂው አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ፣ የስፔን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሉዊስ ዴ ላ ፉኤንተ እና የባየርሙኒኩ አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ በዕጩነት ቀርበዋል ። በሴቶች ደግሞ የባርሴሎናው ፔሬ ሮሜው እና የሊዮኑ ጆናታን ጊራልዴዝ ቀዳሚዎቹ እጩዎች መሆናቸውን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አመልክቷል ።
ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች በሚሰጠው የኮፓ አዋርድ ላሚን ያማል እና ፓው ኩባርሲ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው እጩዎች መካከል እንደሚገኙ የላ ሊጋ ስፖርት ተንታኞች አመልክተዋል ። ባሎንዶርን የሚወስኑት በፊፋ ደረጃ የመጀመሪያዎቹ 100 ሀገራት ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች በመሆናቸው ከአውሮፓ ውጪ ያሉ አህጉራት ተወካዮች ለዓለም ዋንጫ ተጽዕኖ ያላቸው አመለካከት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ስለዚህ አሸናፊው የሚወሰነው በሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ጋዜጠኞች የግል ምርጫ እና በአህጉራዊ ውድድሮች ክብደት ስሌት ጭምር ነው።
ጎል ዶት ኮም ባወጣው መረጃ ሊዮኔል ሜሲ አሁንም በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ የድሮው ዘመን ዝና እና ስም በድምፅ አሰጣጡ ላይ የራሱ የሆነ የጥላ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ስጋት ፈጥሯል። በተጨማሪም እንደ ሮድሪ እና ኤርሊንግ ሃላንድ ያሉ ከዋክብት በድምፅ አሰጣጡ ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ ፉክክሩን እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ተገማች እንዳይሆን አድርጎታል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


