ተፈጥሯዊ ጥሪ

0
146

የወር አበባ አማካይ ከ11 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል በሴቶች ሊከሰት የሚችል ተፈጥሯዊ ዑደት ነው፡፡ ይህ በየወሩ በአማካይ ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት የሚከሰተው የወር አበባ  ከ45 እስከ 55 ዓመት  ድረስ ይቆያል፡፡ የወር አበባ በየወሩ በመደበኛ  ሁኔታ ከ21 እስከ 35 ባሉት ቀናት መካከልም ይከሰታል፡፡   በአማካይ ግን የሚከሰተው በየ28 ቀናቱ ነው።

የወር አበባ ኡደት  ሊከሰት ለሚችል እርግዝና  ተፈጥሯዊ ቅድመ ዝግጅት ነው። ሴት ልጆች ታዲያ በወር አበባ ወቅት ከሚኖረው ውጥረት እና ህመም ባሻገር የንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ ካልተጠቀሙ ልብሳቸው እንዳይነካ መሳቀቅ ሌላው በውስጣቸው የሚያስጨንቅ ሸክም ነው፡፡  ድንገት  ልበሳቸው ላይ ከታየም ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑን በውል ያልተገነዘቡ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ይቀራሉ፡፡

የዓለም ባንክ መረጃ እንደ ሚያመላክተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 500 ሚሊዮን ሴቶች በቂ የወር አበባ ንፅሕና መጠበቂያ(ሞዴስ)፣ ሳሙና ፣ ውኃ እንዲሁም የንጽሕና መጠበቂያቸውን የሚቀይሩበት ምቹ ቦታ እንደማያገኙ ጠቁሟል፡፡

ኤ.ኤች.ኤፍ የተባለ የግብረሰናይ ድርጅት ባወጣው መረጃ ደግሞ በኢትዮጵያ 25 በመቶ ሴቶች  የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ (ሞዴስ) ተጠቅመው እንደማያውቁ አመላክቷል፡፡ ከእነዚህም ከአራት ሴት ተማሪዎች አንዷ በወር አበባ ሳቢያ ከትምህርት ገበታዋ እንደምትቀር አክሏል፡፡  ይህም በሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሣትፎ ብሎም የትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈ ነው፡፡

የጤና ሚኒሥቴርም የወር አበባ አጠቃቀምን አስመልክቶ የተለያዩ መመሪያዎችን አዘጋጅቶ በጉዳዩ ላይ  ግንዛቤ የማሳደግ፣ የተዛባ አመለካከትን የመቀየር፣ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ክፍሎች በትምህርት ቤቶች እንዲዘጋጁ የማድረግ፤ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በሀገር ውስጥ እንዲመረት እና ሌሎች ሥራዎችን አጋር ድርጅቶችንና ባለድርሻዎችን በማስተባበር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል፡፡

በሌሎች ሀገራት ያለውን ተሞክሮ ስንመለከት ለአብነት ኡጋንዳ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅን በማስገንዘብ  ረገድ በርካታ ውጥኖች ተሳክቶላታል። “የወር አበባ ንጽሕና አስተዳደር (MHM) በትምህርት ቤቶች” መርሃ ግብር ዓላማው በትምህርት ቤቶች ውስጥ የትምህርት አቅርቦትን፣ የወር አበባ መጠቀሚያ ምርቶችን የማግኘት እና የተሻሻሉ የንጽሕና አጠባበቅ ተቋማትን ለማቅረብ እያገዘ ነው። ይህ ተነሳሽነት በትምህርት ቤት ልጃገረዶች መካከል መቅረትን በእጅጉ ቀንሷል፤  የትምህርት ውጤታቸውንም አሻሽሏል።

በህንድ ደግሞ የተለያዩ ድርጅቶች በየዓመቱ ግንቦት 28 የሚከበረውን  “የወር አበባ ንጽሕና ቀን” ዘመቻ ግንዛቤ ያስጨብጣሉ፡፡ እንደ  ሳሲ ያሉ ማህበራዊ ኢንተርፕራይዞች ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ (ሞዴስ) በማምረት ከወር አበባ ጋር ተዛማጅ የጤና ትምህርት በገጠር ላሉ ሴቶች ይሰጣሉ።

በአማራ ክልል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክስታይል ኢንጅነሪንግ መምህርት  በለጠች ዓለሙ የአብዛኞቹ ችግር የሆነውን የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ (ሞዴስ) በቀላሉ የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፡፡ ባለሙያዋ እንደሚሉት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ (ሞዴስ) የማምረትና የማሰራጨት ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።

ወ/ሮ በለጠች እንደሚሉት ምርቶቹ በብዛት የትምህርት ተቋማት እና በጎ አድራጊ ድርጅቶች በትእዛዝ እያሠሩ  በትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች፣ ለተፈናቃዮች እና ድጋፍ ለሚሹ አካላት በነጻ እያከፋፈሉ ናቸው። ይህም ተጠቃሚዎች  ትምህርታቸውንና መደበኛ ሥራቸውን በምቾት እንዲያከናውኑ እፎይታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ምርቱ አንዴ ከገዙት ደግመው አጥበው የሚጠቀሙበት ነው።

ወ/ሮ በለጠች ለዚህ ሥራ የመነሻ ምክንያት የሆናቸው በሥራ ቦታቸው እና በሌሎች አጋጣሚዎች ያስተዋሉት ክስተት ነው፡፡ “እስኪ ሴት ልጅ ወይም እህት እንዳለው ሰው ወደ ቤት ውስጥ ተመልከቱ፡፡  የወር አበባ ለማየት የደረሰች ሴት ያለችበት ቤተሰብ  የወር የቤት ወጪ ሲታሰብ አንዱ ይሄ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ የሚያደርግ  አባል የለም፡፡ ወጪው (የሚገዛበት ዋጋ) ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ ቤተሰብ ይህን ወጪ አስቦ ካልገዛ ደግሞ በተለይ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ከመሄድ መቅረትን ይመርጣሉ” በማለት ጠቁመዋል፡፡

ባለሙያዋ በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ መምህርት በመሆናቸው  የተማሪዎችን እና  የሌሎች ሴቶችን ፍላጎትና ችግር በደንብ ለማወቅ ዕድል ስላገኙ  የንጽሕና መጠበቂያውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታትም መረጃዎችን በመሰብሰብና ጥናት በማድረግ ላይ እንደቆዩ ያስታውሳሉ። ወደ ተግባር ለመግባት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ  ያገኙት የቴክስታይል ዕውቀት በተለይም የጨርቆችን ዓይነት ለመለየት እድል ፈጠረላቸው፡፡

በዘርፉ ባላቸው ዕውቀት እና  ልምዳቸው በመታገዝ ሴቶች በወር አበባ ወቅት ንጽሕናቸውን    ሊጠብቁበት ያሚያስችለውን ሞዴስ አመረቱ፡፡ ሙያውንም በግላቸው  ብቻ ለመሥራት ሳይሆን ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር  በቀላሉ በራስ አቅም መሥራት የሚያስችል  ሙያዊ ስልጠናዎችን በባሕርዳር ጣና ኃይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በጎንደር፣ ደሴና አካባቢዎች በመዘዋወር መስጠት ችለዋል።

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ ስልጠናው በሁለት አይነት መልኩ ይሰጣል፡፡ በግል ወይም በረጅ ድርጅቶች  አማካኝነት ሰልጣኞች ስልጠናውን ወስደው የራሳቸውን ፈጠራ ጨምረው  እንዲያዘጋጁ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው። ሌላው በትምህርት  ቤቶች መምህራን ሰልጥነው መልሰው ለተማሪዎች ስልጠና እንዲሰጡ የሚያስችል ነው፡፡

በዚህ የስልጠና መርሐ ግብር  ሰልጣኝ ተማሪዎችም በተመረጡ ጨርቆች ተጠቅመው በመርፌ እና ክር ለራሳቸው የሚገለገሉበትን የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ሞዴሶችን የሚሠሩበትን መንገድ እንዲያዳብሩ ታሳቢ ያደረገ ነው።

ወ/ሮ በለጠች እንደሚሉት  ባለፈው   ዓመት የሙያ ፍቃድ በማውጣት በግላቸው በገዙት አንድ ማሽን  ታጥቦ ድጋሚ አገልግሎት የሚሠጥ  የንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ የማምረት ሥራ ጀምረዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ተጨማሪ የልብስ ስፌት እና ኦቨር ሎክ( Overlock) ማሽኖችን ገዝተው በመጠቀም በስፋት ማምረት ችለዋል። በየጊዜው የሚመረቱት በመጠን ፣ በዓይነት እና በጥራት መስፈርቶች የተሻሻሉ ናቸው፡፡ ምርቶችም  የሚሠሩበት ጨርቅ ቶሎ ታጥበው የሚጠሩ እና የሚደርቁ ናቸው፡፡

በቅርቡ የተጀመረው  አዲሱ ደግሞ የውጪው  ታጥቦ ድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ የውስጡ ፈሳሽ ሳቢ ክፍል ደግሞ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ    የሚጣል ነው።

የወር አበባ የንጽሕና መጠበቂያው ማንኛውንም ጨርቅ ተጠቅሞ  መሥራት እንደማይቻል ወ/ሮ በለጠች ጠቁመዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ   አራት የጥራት መስፈርቶች ያሉት ነው፡፡ እነዚህም መጀመሪያ ጨርቁ ሲመረጥ  ፈሳሽ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑ፣ የጨርቁ ታጥቦ ቶሎ የመድረቅ ብቃት፣ ጨርቁ ሽታ የማያመጣ  እንዲሁም የቆዳ አለርጂና ኢንፌክሽን የማያመጣ (አስተማማኝ) መሆኑ  ነው፡፡

ወ/ሮ በለጠች እንደሚገልጹት  እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ሞዴሶች የጤና ስጋቶችን ከመቀነስ ባሻገር ፈሳሽ የመያዝ መጠናቸው ከ80 እስከ 100 ሚሊ ግራም  በመሆኑ ልብሴ ይነካል አይነካም የሚል ስጋትም አይፈጠርም። ከዚህ ባለፈ  የሚታጠቡ  ሞዴሶች ቢጣሉም ስለሚበሰብሱ በ20/30 ከፕላስቲክ የፀዳ አካባቢ መፍጠር ለሚለው እንቅስቃሴ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ የንጽሕና መጠበቂያው ማንኛውም ሰው ሰልጥኖ መሥራት የሚችለው ከመሆኑ ባሻገር አካባቢው በሚገኝ 80 ከመቶ ጥጥ እና ቀሪው ደግሞ ፈሳሹኑን የሚይዝ ፓሊስተር ጨርቅ በመምረጥ የሚዘጋጅ ስለሆነ ሁሉም ለመሥራት እንዲተጋ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ በቀጣይም ምርቱን ህብረተሰቡ በቀላሉ ገበያ ላይ እንዲያገኘው እንዲሁም በዘርፉ መሥራት የሚችሉትን አሰልጥኖ ከሞዴስ በተጨማሪ የሕጻናት ዳይፐሮችን በሚታጠብ ጥሬ እቃ በመሥራት  ወደ ገበያ የመግባት ዓላማ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

መረጃ

ለሴት ወጣቶች ጠቃሚ ምክሮች

  1. እራስዎን ያስተምሩ፡- በወር አበባ ዑደት እና ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ ሲመጣ ምን እንደሚደረግ፣  ወቅቶች ተፈጥሯዊ እና ጤናማ የሕይወት ክፍል መሆናቸውን ይረዱ።
  2. ዑደትዎን ይከታተሉ፡- የወር አበባ ቀን መቁጠሪያን ይያዙ ወይም የወር አበባዎ መቼ ሊመጣ እንደሚችል ለመተንበይ የወር አበባ መከታተያ መተግበሪያን ይጠቀሙ። ይህ በጊዜ ሂደት በዑደቱ ውስጥ ያሉ ማናቸውንም ጉድለቶች ወይም ለውጦች ለመለየት ይረዳል።
  3. ለወር አበባ ዝግጅት:-  ሞዴስ እና የህመም ማስታገሻ መድሀኒት ካሉ አስፈላጊ ነገሮች ጋር ኪት ያሰባስቡ፣ ስለዚህ የወር አበባዎ ሲመጣ ዝግጁ ይሁኑ።
  4. ንጽህናን መጠበቅ; -ንፁህ እና ምቹ ሆነው ለመቆየት በየጊዜው ገላዎን ይታጠቡ እና እንደ አስፈላጊነቱ (በየ 4-8 ሰዓቱ) የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ይለውጡ።
  5. ከታመነ አዋቂ ጋር ተነጋገሩ፡– የወር አበባዎ ምንም አይነት ስጋቶች ወይም ጥያቄዎች ካሉዎት ከወላጅ፣ ተንከባካቢ ወይም የጤና እንክብካቤ ባለሙያ ጋር ለመነጋገር አያመንቱ።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here