ተናፋቂዉ መስከረም

0
127

የክረምቱ የተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ተጠናቆ ትምህርት መጀመሩን መስከረም አብስሯቸዋል፡፡    ፀጥ ረጭ ብለው የከረሙ የትምህርት ቤት ግቢዎች ተነፋፍቀው በከረሙ ተማሪዎች ጨዋታ፣ ጫጫታ፣ ደስታ እና ፈንጠዝያ ደምቀዋል። የናፍቆት ሰላምታ፣ አዲስ ተስፋ እና ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን የተሰነቀ ትልቅ ራዕይ በየግቢው ይስተጋባል። ጓደኛሞች ሲገናኙ የሚታየው መተቃቀፍና ፊታቸው ላይ የሚነበበው ብሩህ ፈገግታ ትምህርት ቤት ለልጆች ከእውቀት መገበያያነትም ባለፈ ሁለተኛ ሞቃታማ ቤታቸው መሆኑን በግልጽ ያሳያል። እኛም በዚህ የደስታ ድባብ ውስጥ ሆነው በመጀመሪያው የትምህርት ቀን በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የዕውቀት ፋና የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተገኙ ከአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

የትምህርት ቤት መከፈትን በናፍቆት ሲጠብቁ የነበሩት ተማሪዎች ደስታቸውን ከመግለጽ ባሻገር ዘንድሮ ጤናማ የ”እኔ እበልጥ” ፉክክርን ከወዲሁ አውጀዋል። ካነጋገርናቸው ተማሪዎች መካከል እሌኒ ኤርሚያስ ትገኝበታለች። ተማሪዋ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ጓደኞቿን በማግኘቷ ደስታዋን እርሷ ከምትገልፀው በላይ ገጽታዋ ያሳብቃል፡፡ እሌኒ ባለፈው ዓመት ከ3ኛ ወደ 4ኛ ክፍል የተዘዋወረችው ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ነው፡፡  ዘንድሮም  በደንብ አጥንታ 1ኛ ደረጃ ለመውጣት አቅዳለች፤ እቅዷንም ለማሳካት ተግታ ትምህርቷን በመከታተል በፕሮግራም ለማጥናት መዘጋጀቷን  በልበ ሙሉነት እና በትልቅ መነሳሳት ተናግራለች።

የእሌኒ የክፍል ጓደኛና አቻዋ አስያ ጡሃ በበኩሏ ባለፈው ዓመት ከክፍሏ አንደኛ ደረጃን በመያዝ  በከፍተኛ ውጤት ያለፈች ተማሪ ናት። አስያ የክረምቱ የረፍት ጊዜ ተጠናቆ ከጓደኞቿ ጋር ዳግም በመገናኘቷ መደሰቷን ገልጻለች፣ በትምህርት ዘመኑም   ደረጃዋን አስጠብቃ እንደምትቀጥል ቃል ገብታለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክራ ትምህርቷን እንደ ምትከታተል ነው የገለችውአሳውቃለች፡፡

የሁለቱ ተማሪዎች ንግግር የዘንድሮው የአራተኛ ክፍል የትምህርት ገበታ ላይ ጠንካራ ፉክክር እንደሚስተናገድበት የሚያሳይ ነው። ከእነዚህ ብሩህ ተስፋ ካላቸው ተማሪዎች ጋር ደስታውን ሲጋራ ያገኘነው ሌላው  የአራተኛ ክፍል ተማሪው  ብሩክ አበበ ነው። ብሩክ ትምህርት ቤት መከፈቱን ተከትሎ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወትና ሲስቅ ፊቱ ላይ የሚነበበው ሀሴት፣ የመጀመሪያው ቀን የትምህርት ቤት ውሎ ምን ያህል አስደሳችና ናፍቆት የተሞላበት መሆኑን ያሳብቅባታል።

ታዳጊዎቹ የነገዋን ሀገር የሚረከቡ፣ በውድድር መንፈስ እውቀትን የሚራቡ የዘመናችን ተስፋዎች ናቸው። የትምህርት መጀመርን ተከትሎ ተማሪዎች ያላቸውን ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት፣ የትምህርት ቤቶችን አቀባበል እና የዘንድሮውን የትምህርት ዘመን አጠቃላይ ገጽታ በሚመለከት የዕውቀት ፋና የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወ/ሮ አበባ ሽፈራውን አነጋግረናቸው ነበር፡፡

ርእሰ መምህሯ ትምህርት ቤቱ   ተማሪዎችን ለመቀበል በክረምቱ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። በክረምቱ ወቅት  በግቢው የበቀለውን ሳር በጨረታ በመሸጥ ገቢ ከማስገባት ባለፈ  ትምህርት ቤቱን ለመማር ማስተማሩ ምቹ የማድረግ ሥራ በስፋት መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡   ከዚህ ቀደም የነበረውን የወንበር እጥረት ለመፍታት ባለሙያ በመቅጠር 140 ዴስኮችን በራሳቸው አቅም ማስጠገናቸውን ገልጸዋል። የክፍል ውስጥ ጅብሰም ቦርዶችን ሙሉ በሙሉ ከማስቀባት ጀምሮ በየክፍሉ የተማሪዎች የክፍል ምደባ በሚዛናዊነት አከናውነዋል።

በተለይ ለሴት ተማሪዎች የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ ነው ያሉት ርዕሰ መምህርቷ- “ከልጃገረዶች ብንጀምር በወር አበባ ወቅት የሚያርፉበት ክፍል ቢኖረንም አልጋ አልነበረንም። አሁን ግን ኢየሩሳሌም ከተሰኘ በጎ አድራጎት  ድርጅት ጋር በመነጋገር አንድ ሜትር ከሃያ የሆነ ዘመናዊና ምቹ አልጋ አግኝተናል፤ በተጨማሪም ሞዴስ፣ሳሙናና ቅባት ከዚሁ ድርጅት አግኝተን አሟልተናል” በማለት የክረምት ወቅት ክንውናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ዘንድሮ የቅድመ መደበኛ (KG) ተማሪዎችን በራሱ ግቢ በማስጀመር የተማሪዎችን ቁጥር በእጥፍ አሳድጓል። ትምህርት ቤቱ  270 የቅድመ መደበኛ  ተማሪዎችን ለመቀበል  አቅዶ  311 ተማሪዎችን (117 በመቶ) መመዝገብ ተችሏል፡፡ በመደበኛውም በአጠቃላይ ከታቀደው 1 ሺህ 978 ተማሪዎች ውስጥ 1 ሺህ 915 (97 በመቶ) ተመዝግበዋል።

የመክፈቻው ቀንም (Day 1, Class 1) በአዲስ እና ነባር ተማሪዎች መካከል የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ በማድረግ፣ ችቦ በማብራት እና ርችት በመተኮስ እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ ተጀምሯል። የዕውቀት ፋና ትምህርት ቤት በውጤታማነቱ በከተማው ግንባር ቀደም ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ “በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ካሉ ትምህርት ቤቶች በምርጥ ሦስት (Top 3) ውስጥ የገባና 97 ነጥብ ያመጣ ተማሪ አለን፡፡ በተጨማሪም አምስት የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት አልፈዋል” ሲሉ ወ/ሮ አበባ በኩራት ተናግረዋል።

አምና በ8ኛ ክፍል 88 በመቶ፣ በ6ኛ ክፍል ደግሞ 89 በመቶ ተማሪዎችን ወደ ቀጣይ ክፍል ማሳለፍ የተቻለው መምህራን ቅዳሜና እሁድ ሳይሰለቹ በሰጡት የማጠናከሪያ ትምህርት መሆኑን ገልጸው፣ ዘንድሮም በተለይ አብላጫ ቁጥር ያላቸውን ሴት ተማሪዎች ውጤት ለማስቀጠል ቆርጠው መነሳታቸውን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ አልጋ በአልጋ አልነበረም የሚሉት ርእሰ ምምህርቷ፤  የመምህራን በወቅቱ አለመመደብ እና ባልሰለጠኑበት የትምህርት መስክ እንዲያስተምሩ መገደዳቸው አንዱ ተግዳሮት መሆኑን ሲገልጹ፡- “የሳይንስ መምህርት ሆና ስነ-ጥበብ ወይንም የአማርኛ  ሆና እንግሊዝኛ እንድታስተምር ትገደዳለች፤ ይሄ በትምህርት ጥራት ላይ ተጽዕኖ አለው” ይላሉ።

የመጻሕፍት እጥረት አምና ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ግን መሰረታዊ የሚባሉት መጻሕፍት በተሻለ ሁኔታ መቅረባቸውን ገልጸዋል። የትምህርት ስኬት የብዙዎች ርብርብ ውጤት መሆኑን የሚያምኑት ርዕሰ መምህርቷ፣ በቀጣይ መምህራን በክረምቱ በጄኔራል ሳይንስ፣ በእንግሊዝኛ እና በሂሳብ ለ15 ቀናት የወሰዱትን ጠቃሚ ስልጠና ወደ ተግባር በመቀየር በዕቅድና በሰዓት አክባሪነት እንዲያስተምሩ ጠይቀዋል።

በተማሪዎች በኩልም ቤተሰብን ለማገዝ ሰፊ ሰዓታቸውን ከመጠቀም ይልቅ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና በሰዓቱ ትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ርእሰ መምህርቷ አሳስበዋል።

ወላጆችም ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሳይበሉ የሚመጡበትን አጋጣሚ በመረዳት ተጠርተው ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት የልጆቻቸውን ውሎ እንዲከታተሉ ጠይቀዋል። መንግሥት በበኩሉ የመምህራን እጥረትን ከመፍታት ባለፈ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የምገባ መርሀ ግብር ትልቅ አስተዋጽኦ እበረከተ በመሆኑ በኬጂ እና አንደኛ ክፍል የተጀመረውን የዳቦና ወተት ምገባ  አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ! ብለዋል።

በትምህርት ዘመኑ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር መጨረሻ ርዕሰ መምህርቷ፤ “በትምህርት ቤቱ ጀርባና ዙሪያ ያሉ የመኪና ማቆሚያዎች (ፓርኪንጎች) ለደህንነታችን ትልቅ ስጋት ሆነዋል። መኪኖች ሲዞሩ አጥሩን ይመቱታል፤ በተለይ መኪናውን የሚነዱት ረዳቶች በመሆናቸው በልጆች ላይ አደጋ እንዳያደርሱ እንሰጋለን። መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው የሚውሉትም በተለይ ለልጃገረዶቻችን ስነ-ልቦና እጅግ ጎጂ ነው፡፡ በመሆኑም ክፍለ ከተማውና ማህበረሰቡ ትምህርት ቤቱን ከእንዲህ አይነቱ ጫና ነጻ እንዲያወጡ እንዲሁም  የሚመለከተው አካል ፈጣን መፍትሔ እንዲሰጥበት”በማለት   በጥብቅ አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የትምህርት አጀማመር መርሀ ግብርን አስመልክቶ   የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ  አቶ አስሜ ብርሌ ባስተላለፉት መልእክት፤  “ክረምቱ አልፎ ከአዲሱ ዓመት ማግስት ብርሐን ሲፈካ ለትምህርት አጀማመር ቀን በመድረሳችን ደስ ብሎኛል” በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ስኬታማ አጀማመርም በከተማ አስተዳደሩ በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በሙሉ መደረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የአብክመ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግሥቱ  የ2019 የትምህርት ዘመንን በተሳካ መልኩ ለመፈጸም በክረምት ወራት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። በተለይም አቅም ለሌላቸውና ድጋፍ ለሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው እንደ አማራ ክልል በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ወደ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡   እስከ አሁን 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገባቸውን ይፋ አድርገዋል። ቀሪ ተማሪዎችንም በአስቸኳይ መዝግቦ ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ግእዝ በአማርኛ(ተመሳሳይ ማሰሪያ ግሶች)

     ቀደሰ  ……… አመሰገነ

     ወደሰ ……… አመሰገነ

     ዘመረ ……… አመሰገነ

     አእኰተ …… አመሰገነ

     መዝገነ ……… አመሰገነ

     ለጠነ  ………. አመሰገነ

     ባረከ ………… አመሰገነ

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here